ባለፉት ሶስት ዓመታት የፈተና ስርቆትንና ኩረጃን ለመከላከል እንዲሁም ለረጅም ዓመታት ሲከሰት የነበረውን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶችን ለማስወገድ ጠንካራ ሥራ ተሠርቷል
ትምህርት ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን በማረጋገጥ ረገጥ ዓይነተኛ ሚና አለው፡፡ በምክንያታዊነት የሚያምን እና ልዩነቶችን ማስተናገድ የሚችል አስተሳሰብ ያለውን ትውልድ በመቅረጽ የተረጋጋ ሰላም እንዲሰፍን በማድረግ ረገድም የማይተካ ሚና ይጫወታል፡፡ በአጠቃላይ ሳይንስና ስልጣኔ፣ ቴክኖሎጂና ፈጠራ፣ መማርና መመራመር ላይ ትምህርት ጉልህ ድርሻ አለው።
በመሆኑም ሀገራችን ኢትዮጵያ በትምህርት ልማት ላይ በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ልዩ ትኩረት ሰጥታለች፡፡ በዚሁ መሠረት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በየደረጃው ባሉ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ መንግስት ለትምህርት መሠረተ ልማት፣ ለትምህርት ቤት ምገባ እና ለሌሎች ጉዳዮች ከፍተኛ ወጪ ያወጣል፡፡ በትምህርት ሴክተሩም የትምህርት አዋጅን ጨምሮ የተለያዩ ህጎች የወጡና እየተተገበሩ ያሉ ሲሆን የስርዓተ ትምህርት እና ሌሎች ሪፎርሞችም በትምህርት ሚኒስቴር እና በክልል የትምህርት ቢሮዎችም እየተደረጉ እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ ይሁን እንጂ በትምህርት ቤት ያለው የነገው ሀገር ተረካቢ ትውልድ መማሩና አለመማሩ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ሚና በአግባቡ መታየት ያለበት እዚህ ጋር እንደሆነ ይታመናል፡፡
ባለፉት ሶስት ዓመታት የፈተና ስርቆትንና ኩረጃን ለመከላከል እንዲሁም በነዚህ ምክንያቶች ለረጅም ዓመታት ሲከሰት የነበረውን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውሶችን ለማስወገድ ጠንካራ ሥራ እንደተሰራ እንገነዘባለን፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ በ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና 50% እና ከዚያ በላይ ውጤት ያስመዘገቡት ተፈታኞች በ2014 ዓ/ም 3.3%፣ በ2015 ዓ/ም 3.2% እና በ2016 ዓ/ም 5.4% ብቻ በመሆኑ ከ95% በላይ በሆኑ ተፈታኝ ተማሪዎቻችን ዝቅተኛ ውጤት በተደጋጋሚ ሲመዘገብ ሁላችንንም የሚቆጨን ጉዳይ ነው፡፡ በሪሜዲያል ፕሮግራም ለተጨማሪ ዝግጅት ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እንዲገቡ የተደረጉ ተማሪዎችም እንደገና ተመዝነው የማያልፉት ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ስለሆነም ውድቀቱ የተማሪዎቹ ብቻ ሊሆን ፈጽሞ አይችልም፡፡ ተጠያቂነትና ኃላፊነትም በየደረጃው ሊሰፍን ይገባል፡፡
በመሆኑም 95% እና በላይ ተፈታኝ ተማሪ ዝቅተኛ ውጤት እያመጣ እስከመቼ ይቀጥላል የሚለው ጥያቄ የአብዛኛው ህዝባችን ጥያቄ በመሆኑ ምላሽ ይፈልጋል፡፡ በተጨማሪም አንድም ተፈታኝ ተማሪ 50% እና ከዚያ በላይ ውጤት ያላስመዘገበባቸው ትምህርት ቤቶች ቁጥር ቀላል ካለመሆኑ በተጨማሪ በየዓመቱ በሚፈለገው ደረጃ መሻሻል አለማሳየቱ ብቻ ሳይሆን ትምህርት ቤቶቹ በብዛት የሚገኙት በገጠር፣ በአርብቶ አደር እና መሠረተ ልማት ባልተዳረሰባቸው የሀገራችን አካባቢዎች መሆናቸው የትምህርት ፍትኃዊነት ላይ ጥያቄ ያስነሳሉ፡፡ ይህም ጥራት ያለው ትምህርት ፍትኃዊ ተደራሽነት ላይ በበቂ ጥናትና ምርምር ታግዞ አፋጣኝ የተግባር እርምጃ የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡
ስለሆነም የትምህርት ልማት ሥራችን ዝቅተኛ ውጤት ያስመዘገበበትን በየደረጃው ያለው አመራርና ባለሙያው በአግባቡ በመፈተሽ ተጠያቂነትና ኃላፊነት የሰፈነበትን ሥርዓት ማረጋገጥ ይገባል፡፡ በተያያዘም የፈተናውን አወጣጥና አስተዳደርንም በሚመለከት ዘላቂ፣ አስተማማኝ፣ ደህንነቱ የተረጋገጠ እና በተሟላ ሁኔታ በቴክኖሎጂ የተደገፈ የትምህርት ምዘናና ፈተና ስርዓት እና ተቋም ከመገንባት አንጻርም ቀጣይነት ባለው መልኩ በአግባቡ እየፈተሹ ጉድለቶቹንም እያረሙ ያልተበጣጠሰ፣ የተደራጀና ጠንካራ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ስርዓት መገንባት ያስፈልጋል፡፡
በሌላው በኩል እአአ 2023 ላይ በተጠናው ሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘና ጥናት (Early Grade Reading Assessment (EGRA)) ሪፖርት መሠረት ሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች 63% ሶስተኛ ክፍል 49% ተማሪዎች አንድም ቃል ማንበብ አልቻሉም፡፡ ይህም ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ተማሪዎች መሠረታዊ የንባብ ክህሎት እንደሌላቸው ያሳያል፡፡ በመሆኑም ሳያነቡ መማርና መመራመር ከባድ በመሆኑ በቅድመ አንደኛና በታችኞቹ የክፍል ደረጃዎች ጀምሮ አሁንም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል፡፡
በሌላው በኩል እአአ ከ2000 እስከ 2023 በተጠናው ሀገር አቀፍ የትምርት ምዘና (National Learning Assessment (NLA)) መሠረት በ4ኛ ክፍል (በእንግሊዘኛ፣ በአፍ መፍቻ፣ በሒሳብ እና አካባቢ ሳይንስ የትምህርት ዓይነቶች) እና በ8ኛ ክፍል (በእንግሊዘኛ፣ በሒሳብ፣ በፊዝክስ፣ በኬሚስትሪ፣ እና በባዮሎጂ የትምህርት ዓይነቶች) ተማሪዎች ያስመዘገቡት ሀገራዊ አማካይ ውጤታቸው ሲታይ 50% በታች ነው፡፡
እንደዚሁም የ2016 ትምህርት ዘመን የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተናዎች ውጤት ሪፖርቶ ሲታዩ አጠቃላይ ሀገራዊ አማካዩ 50% ነው፡፡ በተያያዘም የዩኒቨርሲቲ መውጫ እና የድህረ ምረቃ ትምህርት መግቢያ ፈተናዎችም ላይ የማለፊያ ውጤት የማያስመዘግቡ ተፈታኞች ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
በመሆኑም በተለያዩ ጊዜያት የሚመጡ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በየደረጃው ያለው የትምህርት ምዘናም ይሁን የፈተናዎች ውጤት በዝቅተኛነት መመዝገብ ወይም የውጤት ማሽቆልቆል መሠረታዊ ተግዳሮቶቹ ብቁና በቂ መምህራን እጥረት፣ በቂ የተማሪዎች መማሪያ መጽሀፍት አለመኖር፣ በአንድ ክፍል ብዙ ተማሪዎች መኖር፣ ምቹና ሳቢ የመማር ማስተማር አከባቢ አለመኖር፣ በቂ የሆነ የተማሪ ቤተሰብ ድጋፍ አለመኖር፣ የቅድመ አንደኛ ትምህርት ተደራሽነት ጉድለት፣ የተጠያቂነትና ኃላፊነት ስርዓት በአግባቡ አለመስፈን ወዘተ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ስለሆነም የትምህርት ስርዓቱ ስብራት ባለቤቱም መፍትሔ አመንጪውም በትምህርት ስርዓቱ ውስጥ በየደረጃው ያለ አመራርና የትምህርት ማህበረሰብ ነው፡፡ ተማሪውና የተማሪ ወላጅ በትምህርት ጥራት መረጋገጥ ላይ ከፍተኛ ሚና ያላቸው ቢሆንም ብቻቸውን ወሳኝ ግን አይደሉም። በመሆኑም የችግሩ ብቸኛ ገፈት ቀማሽ የማይሆኑበትን አሠራር መፍጠር ይገባል፡፡ መምህራን በትምህርት ስርዓት ውስጥ ቁልፍ ሚና አላቸው፡፡ በመሆኑም በመምህራን ልማት፣ በመምህራን ትምህርትና ስልጠና ላይ እንዲሁም የመምህራኑን ኑሮ ማሻሻል እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቻቸውን በጋራ ሆኖ መፍታት ላይ ልዩ ርብርብ የሚጠይቅና ትኩረትም የሚሻ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ በሀገራችን ያሉ ትምህርት ቤቶች አብዛኞቹ ከደረጃ በታች በመሆናቸው የተጀመረውን ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ አጠናክሮ መቀጠልና የትምህርት ቤቶች አካባቢም ለተማሪዎች ምቹ ለማድረግ በቅንጅት መስራት የሚጠይቅ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
በመጨረሻም በየዓመቱ በትምህርት ምዘናና ፈተናዎች እየተዘጋጀ ያለው እንደዚህ ዓይነት ሁሉንም ባላድርሻ አካላትን የመሰባስብና በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲመክሩና ለችገሮቹም በጥናትና ምርምር ላይ መሠረት ያደረጉ ተግባራዊ የሚደረጉ የጋራ መፍትሔ በማስቀመጥ የሚደረጉ ጉባኤዎች ከፍተኛ ሀገራዊ ፋይዳ ያለቸው በመሆኑ ተጠናከረው ሊቀጥሉ ይገባል፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ የሥራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴም ቁጥጥር፣ ክትትልና ድጋፍ ከሚያደርጋቸው ተግባራት መካከል አንዱ በመሆኑ አስፈላጊውን እገዛ የሚያደርግ መሆኑን በቋሚ ኮሚቴውና በራሴ ስም መግለጽ እወዳለሁ፡፡
# EAES
ለጥቆማ 👉
@atc_newsbot➡️
https://t.me/atc_news