╔═══════════╗
የአሊሟ ሴት ገጠመኝ
╚═══════════╝
የሸይኽ ሰኢድ ኢብኑ ሙሰዪብን የዕውቀት ገበታን ያዘወትራል። በረሀውን አቆራርጦ በብርድ በቁሩ፣ በሙቀት በግለቱ አንገቱን ሰበር አድርጎ ጆሮውን ቀስሮ ከማዕዱ ይቋደሳል። አቡ ወዳአ ሲሉም ይጠሩታል።
የጀነቱ ጨፌ ከሚቀጠፍበት ሥፍራ ለሁለት ወራት ከራቀ በኋላ ወደ ዒልም ገበታው ዳግም ተመለሰ።
ሰላምታን ከኡስታዙ ጋር ተለዋወጠና የናፈቀውን ትምህርት መከታተል ጀመረ። ደርሱ እንዳበቃ በምን ምክንያት እንደቀረ ለምንስ ሳይናገር እንደጠፋሁ ሸይኹ ጠየቁ። ባለቤቴ ሞታብኝ ሀዘን ላይ መቆየቱን አብራርቶ አስረዳቸው።
ሰው ከበዛበት ቦታ ገለል አድርገው ወሰዱትና እንዲህ በማለት ጠየቁት፦
"አዲስ ሚስት ለማግባት አላሰብክምን?!"
"ለኔ አይነቱ የቲም ሆኖ ላደገ፣ ድሃ ሆኖ ለኖረ ልጁን የሚድር ማን አለ?! ወላሒ አሁን ከሁለት ዲርሃም ሀብትም ሆነ ንብረት የለኝም" በማለት መለሰላቸው።
"ልጄን እድርልሀለው" አሉት።
ታላለቅ ባለስልጣናት ልጃቸውን ጠይቀው አልድርም ማለታቸውን ያውቃልና ይህን ቃል ሲሰማ ምላሱ ተኮላተፈ። ተንተባተበ።
"የችግር ህይወቴን አውቀው ልጅዎን ሊድሩኝኝ?" በማለት በተደናገጠና በተቆራረጠ ድምፅ ጠየቀ።
"አዎ! ልጄን እድርልሃለው ኃይማኖቱና ሥነምግባሩ ያማረ ሰው ካገኘን ልጃችንን እንድንድር እስልምና ያዘናልና አንተ ደግሞ በሥነ ምግባርህ ትሁትን አደብ ያለህ መልካም ሰው ነህ" በማለት መለሱለት።
ለምስክርነት የሚሆኑ ሁለት ሰዎችን ጠሩና ያለችውን ሁለት ዲርሀም መህር አድርገው ኒካሁ ታሰረ።
ከድንጋጤና ከደስታው ብዛት የተነሳ የሚናገረውን ማወቅ ተሳነው። ከተቀመጠበት ብድግ አለ። ቀኑን ፆመኛ ስለነበር መስጂድ ገብቶ የመግሪብ ሰላት ሰገደና ወደ ቤቱ አቀና። ልጅቱን ሳያውቃትና ሳያያት መቀበሉ ገርሞት አንገቱን ነቀነቀ።
ትርክቱን ለባለታሪኩ እንተውለት
"ቤት እንደገባሁ ፋኖሴን አብርቼ የማፈጥርበትን ዘይትና ዳቦ አቀረብኩ። አንድ ሁለት እንደጎረስኩ የቤቴ በር ተንኳኳ። "ማነው?" በማለት ከበሩ ኋላ የቆመውን ሰው ማንነት ለማጣራት ጠየቅኩ። "ሰዒድ" የሚል ምላሽ ሰማሁ። በአላህ እምላለሁ!ሰዒድ በሚል መጠሪያ የማውቃቸውን ሰዎች ሁሉ ሳስብ ኡስታዜ ሰዒድ ኢብኑ ሙሰዪብ ይሆናል ብዬ ፈፅሞ አላሰብኩም። አርባ ዓመታትን ሙሉ ቤቱ ወይም መስጂድ እንጂ ሌላ ቦታ ታይቶ አይታወቅም። አወለሰፍ እንጂ የሰውን ጀርባ እያየ ሰግዶ አያውቅም። በሩን ከፈትኩ ከፊት ለፊቴ ኡስታዜ ቆሟል። ደነገጥኩ። "ልጁን ለኔ አይነቱ መናጢ ድሃ በመዳሩ ተፀፅቶ ሀሳቡን ሊቀይር ነው የመጣው ብዬ አሰብኩ "ያ አባ ሙሐመድ! እዚህ ድረስ በመምጣት ለምን ደከምከ ሰው ልከህ ብታስጠራኝ እመጣ ነበር" አልኩትና ወደ ቤት እንዲገባ ጋበዝኩት።
"ዛሬ መምጣት ያለብኝ እኔ ነኝ። የመጣሁትም ልጄ ሚስትህ ሆናለችና እሷ አባቷ ቤት ብቻዋን አንተም በቤትህ ያለ አጫዋች ስለሷ እያሰብክ ብቻህን መሆንህን ጠልቼ ይዣት መጥቻለሁ" አለና ከጎኑ ወፈቆመችው መልከ መልካም እንስት ዞሮ "ልጄ ሆይ! በአላህ ስምና ረድኤት ወደ ባልሽ ቤት ግቢ" በማለት የአባትነት ትዕዛዙን አስተላለፈ። ከሐያእዋ የተነሳ ወደኔ ስትራመድ ቀሚሷ አደናቅፏት ልትወድቅ ተቃረበች።
አባቷን አንኳ በስርአት ሳልሰናበት እየተጣደፍኩ ወደ ውስጥ ዘለቅኩ። ድህነቴ ስላሳፈረኝ የፋኖሱን ብርሃን አደብዝዤ ዳቦና ዘይቱን አልጋ ስር ደበቅኩት።
የቤቴ ጣራ ላይ ወጥቼ "ሰዒድ ኢብኑል ሙሰዪብ ልጁን ዳረኝ ቤቴ ድረስም ይዞልኝ መጣ" ብዬ ከፍ ባለ ድምፅ አዋጅ አልኩ። ከጎረቤቶቼ መካከል አንዲት አሮጊት በመስኮት በኩል አንገቷን ብቅ አርጋ እንዲህ አለችን፦
"አንተ ሰው! ለመሆኑ የምትናገረውን ታውቃለህ? ሰዒድ ልጁን ድሮህ ከቶውንም ቤትህ ድረስ ይዞልህ ሊመጣ? እሷ እንኳን ላንተ ለድሃው ለታላቁ መሪ ልጅ ወሊድ ቢን አብዱልመሊክ እምቢ ተብላለች ውበቷስ ቢሆን ላንተ ለደሃውማ አትገባም"
"ግቡ ቤቴ ናት ያለችው ተመልከቷት እውነተኛነቴን ታረጋግጣላችሁ" አልኳት።
ከአዲሷ ሚስቴ ጋር የጫጉላ ቆይታዬን ጨርሼ ወደ ቀድሞው የዕውቀት ገበታ ዒልምን ለመቋደስ ስነሳ "አንተ የዓይኔ ማረፊያ የቤቴ ሙሶሶ ባሌ ሆይ! አባቴ ጋር ያለው እውቀት ሁሉ እኔም ጋር አለና ቁጭ ብለህ ቅራ" በማለት በጆሮዬ ሹክ አለችኝ።
ቁርአንን በቃሎ የሸመደደች። የረሱልን ﷺ ሐዲስ የሐፈዘች የጌታዋን ቃል አክባሪ፣ የተማረችውን ዕውቀት ተግባሪ፣ አላህን ፈሪ የባሏን ሀቅ ጠባቂ መልከ መልካምና እጅግ ቆንጆ እንስት ሆና አገኘኋት።
አሚን በሉ ልመርቃችሁ!
የእስልምና አኽላቅን የተላበሰች፣ ልጆቻችሁን በጀግንነት አሳድጋ ለቆራጥ አላማ የምታዘጋጅ እንስትን አላህ ይወፍቃችሁ።
ሴቶችዬ በኢማን የበለፀገ በተግባር የጎለበተ እንደ ሰላሐዲነል አዩቢ አባት ልጆቻችሁን የሚያንፅ ባል ይስጣችሁ።
═════════════════
ይህ የዩቱዩብ አድራሻችን ነው ሰብስክራይብ ያድርጉ
👇👇👇👇
https://youtube.com/channel/UCPgxFIQ_qZ2XHM1di_y_xoA═════════════════
ለሌሎችም ሼር በማድረግ ተደራሽነቱን እናስፋ
╔═══════════════╗
http://t.me/sehkaliderashid http://t.me/sehkaliderashid╚═══════════════╝