"አሁን ቀለለኝ"
ሱመያ ሱልጣን
"ላወራሽ ፈልጌ ነበር ደውይልኝ!" ።በቃ ይሄን ነው ያለችኝ። ንግግሯን ቀለል አደራረጓ " እኔ ምልሽ ሻይ መቼ እንጠጣ?" የሚልን እንጂ ተራራን አንድሸከምላት" አደራ" የምትል አይመስልም ነበር። ቀለል አድርጋ " ላወራሽ ፈልጌ ነበር።"ብቻ
ስልኬን አንስቼ ስደውል ያነሳችበት ፍጥነት ጥሪውን ይቀድማል። በሳግ በታፈነ ድምፅ
"ሱም"
"ወዬ ምነው በአላህ አፈነሸ እንዴ ድምፅሽ?አየሩ ነው ሳይነስ?" ዘባረቅኩ። ሳቂታ እሷን እንዴት በ እንባ ልጠርጥራት?
" አንድ ጥያቄ መልሺልኝ" ልቤ እየፈራ እንድትቀጥል ስል ዝም አልኩ።
" የምትሳሺለት ብርጭቆሽ ሊወድቅ አየር ላይ ተንሳፎ ቢሆን እና እጅሽ ደግሞ ሌሎች ብዙ እቃዎች ሲወድቁ በስብርባሪው ጉዳት የቆሳሰለ ቢሆን ያን ብርጭቆ በቆሳሰለ እጅሽ ለመያዝ ትሞክሪያለሽ ወይስ እንዲወድቅ ትተይዋለሽ? ልጆችሽ ድምፅ እንዳያስደንግጣቸው ስትይ የቆሰል እጅሽን ለ ብርጭቆው ትልኪያለሽ ወይስ "ቢደነግጡ ለ ደቂቃ ነው" ብለሽ ለማገገም የሚቆየውን ቁስል ታስቀድሚያለሽ?" ከ እንባዋ ጋር ስትታገል እንደምንም ጨረሰች።
ጉዳዩ ስለ ብርጭቆ እንዳልሆነ ቢገባኝም ያቺ ከውጭ ስትታይ ሙሉ የምትመስለው ሴት ላይ "ምን ክፍተት አለ ብዬ ልገምት?"።
" ሱም መልሺልኝ"
"ምን ተፈጥሮ ነው? በአላህ አስጨነቅሽኝ"
"መልሺልኝ"
"የኔ ቆንጆ በአላህ ተጨነቅኩ"
ከቀድሞ እጅግ በበረታ ድምፅ ያለችውን መስማት እስኪያቅተኝ ድረስ እያለቀሰች
"ሱም ትዳሬ ትዳሬ" ለቅሶዋ የምትለውን ጨርሶ አያሰማም
"ትዳርሽ ምን ሆነ?"
"ብርጭቆው ሆነ" ለጭንቅላቴ ከባድ ነበር።
የሆነችውን የከፈለችውን የተደረገችውን የተሰማትን ሁሉ ጣልቃ ሳልገባባት በለቅሶዋ አጅባ አወራችኝ። እሷ ያን ስታወራ ረጅም ጊዜ ሳላያት ቆይቼ "እንዴት ናት ግን?" ብዬ ስጠይቅ "አምሮባታል ቢስሚላህ። ከቤት ስለማትወጣ ያ ቅላት ብሶበት አረብ መስላ" የተባልኩት በጭንቅላቴ መጣብኝ። አለች እየተባለች ስለጠፋችው ነፍስ ልቤ ቆሰለች።
አስተውያለሁ። እያወራችው እንባዋ ሲቀንስ። ጭንቀቷ ሲረጋጋ። ሸክሟ ከሷ ላይቀንስ ለኔ ስትደርበው። አይቻለሁ እየተረጋጋች ነበር።
"እንደ እድሜሽ አይደለሽም ብዬ ነው ማማክርሽ። ወይም ለትዳር እንዳትቸኩይ ከኔ እንድትማሪም ይሆናል። ብቻ አላቅም ይቅለለኝ ብዬም ይሆናል። ሱሚዬ ወላሂ ስለተነፈስኩ ይሁን አላቅም ተረጋጋሁ። አመሰግናለሁ የኔ እናት በኔ የደረሰ እንዳይደርስብሽ ዱዓ በማድረግ ነው ምክፍልሽ። በይ ቻው እሱ መጣብኝ" ብላ ዘጋችው።
በደሏ ከኔነቴ አጣላኝ። ሰው ሸሽቼ በጀመዓ እና በቢዚነት ተደበቅኩ። ያሸከመችኝ ቁስል "ቀለል አለኝ አሁን" ብላ እንዳለችው በቀላሉ የሚረጋጋ አልነበረም። በኔ እድሜ ሊደረግላት የሚችል እገዛ ባጣ ይሄን የሚያምር ትግስት ላለበሳት ጌታ ሰጥቼ ለራሴም ጤንነት ዱዓዬን አድረስኩ። ወዶ አይደለም ለካ ሰው የሚፈዘው🥹
ታሪኩ እውነተኛ ነው። አንዳንድ ቃላቶችን ከመቀየር ውጪ ያልተደባለቀበት። የነገረችኝን መጻፍ ፍቃድ ስላልጠየቅኩ ዘልዬዋለሁ
@sumeyasu@sumeyaabot