☄️....የ8ኛ ክፍል ተማሪዎች እንደነበርን ነው...
አንድ ቀን የሆነ አስተማሪያችን ቀረ....በዛ ክፍት ክፍለጊዜ ሁላችንም ደስ ያለንን ስንሠራ ነበር
አብዛኞቻችን ወሬና መንጫጫት ላይ ነበርን።
...አንድ ምስጋናው የሚባል የክፍላችን ልጅ ብላክቦርድ ላይ በወዳደቀ ቾክ ሁለት ሰወችን ሳለ።
ሥዕል ስላችሁ ይሄ ዝም ብሎ የልጅ ሥዕል አይደለም፣ ባስታወስኩት ቁጥር የሚገርመኝ የግንባራቸው መስመር፣ ፊታቸው ላይ ያረፈው ጥላ ልብሳቸው ላይ ያለው ፓተርን ሳይቀር ፎቶ የሚመሳስሉ ፖርትሬቶች...
...ደግሞ የሳለው ምንም እያየ አልነበረም።
...እማሆይ ቴሬሳ ሁለት እጆቻቸውን እንደህንዶች ሰላምታ አገናኝተው ግንባራቸውን እንዳስነኩ እጃቸው መሀል መቁጠሪያ ተንጠልጥሎ፣ እንዲሁም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከነ ንጉሳዊ ልብሳቸው ወደጎን ዞር ብለው።
ሁላችንም በምስጋናው የሥዕል ችሎታ ተገረምን ተደነቅን።
ቀጣዮ ክፍለግዜ ጅኦግራፊ ነበር...
ኮስታራው አስተማሪያችን ገባና ሥዕሎቹን ዓየት አድርጎ "ማነው የሳለው?" አለ ።
በአንድ አፍ "ምስጋናው" አልን በአድናቆት ጭምር።
መምህሩ ወደምስጋናው ወንበር ተራምዶ የያዘው ልምጭ ተሰባብሮ እስከሚያልቅ ምስጋናውን ቀጠቀጠው።
እና በቁጣ "ይሄ የተከበረ የትምህርት ገበታ ነው ! ማንም እየተነሳ የሚፀዳዳበት አይደለም ደደብ" ብሎ ደነፋ።
ዳስተሩን አንስቶ አንዴ እጁን ሲያስወነጭፈው ኃይለስላሴን ለሁለት እማሆይ ቴሬሳን አናታቸውን ገመሳቸው።
አጠፋፍቶ ማስተማሩን ቀጠለ። ምስጋናው ከዛ በኋላ እንኳን ሰሌዳ ላይ ወረቀት ላይ ሲስል አላስታውስም።
...ብዙ ዓመታት አለፉ።
አንድ ቀን አዲስ አበባ ፒያሳ መርከብ የምትባል ምግብ ቤት ምሳ በልተን ስንወጣ በር ላይ አንድ የጎዳና ተዳዳሪ በፌስታል ፍርፋሪ ሲበላ ዓየሁ ምስጋናው ነበር።
ቢጎሳቆልም አልጠፋኝም ነበር።
ዛሬ በምን አስታወስኩት? አንድ አሜሪካዊ ህፃን ሰሌዳ ላይ በቾክ የሳለው ስዕል በአስተማሪዎቹ እና በትምህርት ቤቷ ርዕሰ መምህር ስለተደነቀ በቀስታ ሰሌዳውን አንስተው አንድ ቢሮ ግድግዳ ላይ እንደሰቀሉት አነበብኩ።
ሥዕሉ ለዓመታት እንዲቆይ የሆነ ነገር እናስደርጋለን ብላለች ርዕሰ መምህርቷ።
ሀገር ባከበረቻቸው ትከብራለች ባከሸፈቻቸው ትከሽፋለች።
(wegoch)
(በአሌክስ አብርሃም) 👉በየቀኑ ጠቃሚ መልእክቶችን፣ መጽሐፍት ፒዲኤፍ፣ በነፃ የምታገኟቸው አሪፍ የኮምፒውተር ሶፍትዌሮች፣ የቢዝነስ ሃሳቦች እና የገንዘብና የተለያዩ ሽልማቶችን ለማግኘት ገጾቻችንን ይቀላቀሉ።
📱ቴሌግራም👉
@Beleqe_boostup📱ፌስቡክ ገጽ👉
https://www.facebook.com/SuperBoostUpዌብሳይት 👉
https://superboostup.com/📱ቲክቶክ👉 tiktok.com/@superboostup