ርክበ ካህናት
=========
ግንቦት ፳፩ ይህቺ ዕለት በቤተ ክርስቲያን "ርክበ ካህናት" : "ዕለተ ጥብርያዶስ" በመባል ትታወቃለች:: "ዳግሚት ዕለተ አግብኦተ ግብር" የሚሏትም አሉ::
ርክበ ካህናት በቁሙ "የካህናት ኖሎት (እረኞች) መገናኘትን" የሚመለከት ቃል ነው:: የክብር ባለቤት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጐ ከተነሳ በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ በየጸጋቸው መጠን እየተገለጠ ያጽናናቸው ያጸናቸው ፣ያስተምራቸው ፣ ይባርካቸውም ነበር::
እስከ ዕርገቱ ባሉ ፵ ቀናትም መጽሐፈ ኪዳንን ፣ ትምህርተ ኅቡዓትን ፣ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን አስተምሯቸዋል:: በልቡናቸውም አሳድሮባቸዋል::
በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተጻፈ ደግሞ ከዕርገቱ አስቀድሞ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ፫ ጊዜ በጉባኤ ተገልጧል::
፩.የትንሳኤ (ዮሐ ፳:፲፱)
፪.የአግብኦተ ግብር /ዳግም ትንሳኤ(ዮሐ፳:፳፮)
፫.ዕለተ ጥብርያዶስ (ዮሐ. ፳፩፣፩-፯)
በተረፈው ግን ለድንግል ማርያም ሁሉን ዕለታት መገለጡን አበው ያስተምራሉ::
በዚህች ዕለት በቅዱስ ዼጥሮስ መሪነት ሐዋርያቱ ወደ ጥብርያዶስ ሔዱ:: አሶችን ሊያጠምዱም በብዙ ደከሙ:: ነገር ግን ጌታችን በረድኤት አብሯቸው አልነበረምና አንዳች አሣ በመረባቸው ሊገባ አልቻለም::
ማጥመድ (አስተምሮ ከክህደት ወደ ሃይማኖት : ከኃጢአት ወደ ጽድቅ መመለስ) የሚቻለው በረድኤተ እግዚአብሔር እንጂ በእውቀት ብዛት ወይም በአንደበተ ርቱዕነት ብቻ አይደለምና::
ሐዋርያት ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ ለማጥመድ ሲለፋ አድረው ፣ሲነጋ ግን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቅዱሳን ደቀ መዛሙርቱ መጣ:: በጥብርያዶስ ባሕር ዳርቻም ቆሞ ታያቸው:: ከሚወደው ደቀ መዝሙሩ ከዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ በቀር ያወቀው ግን አልነበረም::
ቸሩ አባት "ልጆቼ! አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁ?" ሲል ጠየቀ:: "ጌታ ሆይ! የለም" አሉት:: "የለንም" ብሎ የሌለንን ነገር በጌታ ፊት ማመኑ እጅግ መልካም ነው:: ምክንያቱም ያጣነውን ነገር ያን ጊዜ ሊጠቁመን ቸርነቱ
ብዙ ነውና::
ያን ጊዜ ሐዋርያቱን መረባቸውን በመርከብ ቀኝ እንዲጥሉ አዘዛቸው:: እነርሱም በደስታ ጣሉ:: በአግራሞት እስኪሞሉ ድረስ : መረባቸውም ሊቀደድ እስኪደርስ ድረስ
፻፶፫ ዓሦች ተያዙላቸው::
ያን ጊዜም የሚወደው ደቀ መዝሙሩ ቅዱስ ዮሐንስ ምስጢር አወጣ:: ለቅዱስ ዼጥሮስ "ጌታ እኮ ነው" አለው::
ሽማግሌው ቅዱስ ግን ራቁቱን ነበርና ወደ ባሕሩ ተወረወረ::
ከአፍታ በሁዋላም ጌታችን ከሐዋርያቱ ጋር በድጋሚ (ለ2ኛ ጊዜ) ለምሳ ተቀመጠ:: ባርኮ ሰጥቶ : ልባቸውን ሊያጸና አብሯቸው በላ::
በዚያች ሰዓት ቅዱስ ዼጥሮስን ፫ ጊዜ "ትወደኛለህን?" ሲል ጠየቀው:: ቅዱሱ አረጋዊም እየደጋገመ "ለሊከ ተአምር ከመ አነ አፈቅረከ (እንድወድህ አንተ ታውቃለህ)"
ሲል መለሰ::
ጌታም በበጐች ሐዋርያት (ካህናት) : በጠቦቶች አርድእት (ዲያቆናት) : በአባግዕት ፴፮ቱ ቅዱሳት አንስት (ምዕመናን ወምዕመናት) ላይ ሁሉ እረኛ እንዲሆን ሾመው::
ቀጥሎም የሰማዕትነቱን ምስጢር ገልጦለት
"ተከተለኝ" (ለጊዜው በእግር : በሁዋላ ግን በግብር ምሰለኝ) ብሎታል:: ወልደ ነጐድጉዋድ ወፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስም ሞትን እንደማይቀምስ እንዲሁ
ተናግሮለታል::
ይህች ዕለትም እነዚህ ሁሉ ተግባራት የተከናወኑባት ናትና በእጅጉ ትከበራለች::
ቤተክርስቲያናችንም ይህንን አብነት አድርጋ ሁሌ የጳጳሳትን ጉባዔ(ቅዱስ ሲኖዶስ) ከትንሳኤ በ፳፬ኛው ቀን ጀምሮ ታደርጋለች፡፡አባቶቻችን ዻዻሳትም ከጌታና ከደቀ መዛሙርቱ አብነትን ነስተው በዚህች ቀን ፪ኛውን ታላቅ ሲኖዶስ ያደርጋሉ:: መንፈስ ቅዱስ እየተራዳቸው ለቤተ ክርስቲያንና ለኛ ለልጆቿ የሚጠቅም መመሪያን ያወጣሉ ብለን እንጠብቃለን::
በተለይ ደግሞ በአምናው ርክበ ካህናት ስለ
፳፰ ቱ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት የሚባለውን ሁሉ ተስፋ አድርገን ነበር፣ ከቅዱሳን ሰማዕታት ጋር ዜናቸውን ለመደመር (ለመመስከር) እጅጉን ናፍቀንም ነበር:: ዘንድሮም አዲስ ነገር ካለ ብንሰማ ደስ ይለናል::
በተለይ በዚህ ዓመት ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን የወረራት የጠላትን ጦር የሚሰብር ፣ምክራቸውን የሚመክት ፣ ክፋታቸውን የሚያኮላሽ የሲኖዶስ ውሳኔ ከአባቶቻችን እንጠብቃለን። መንጋው ባዝኗልና፣ እረኝነት የተሰጣቸው አባቶቻችን እንዲነቁልንም ከተስፋ ጋር እንማጸናለን።
የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መንፈሱ ከአባቶቻችንና ከእኛ ከኃጥአኑ ጋር በረድኤት ይኑር::
@Tinsae_ze_ethiopia