ስለ ኡድህያ መታወቅ ያለባቸው 30 ነጥቦች
በዒድ ቀን ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል አንዱ ደግሞ ኡድሒያን ማረድ ነው፡፡ ስለሆነም ስለ ኡድሒያ ጥቂት እንተዋወስ፡-
1. ‹ኡድሒያ› ማለት በዒድ አል-አድሓ ቀንወደ አላህ (ሱ.ወ.) ለመቃረብና ትዕዛዙን ለመፈጸም ተብሎ የሚታረድ እንሰሳ ነው፡፡ በዱሓ ወቅት ማለትም ረፋድ ላይ ስለሚታረድ ስያሜውን ‹ዱሓ› ከሚለው አገኘ ያሉም አሉ፡፡
2. ኡድሒያ ሸሪዓዊ ድንጋጌ ያለው ጉዳይ ነው፡፡ አላህ (ሱ.ወ.) ‹ለጌታህ ስገድ፤ (በስሙ) ሰዋም፡፡› (አልከውሠር፡2) ኢብኑ ዐባስ (ረ.ዐ.) እንዳሉት መስዋእት የተባለው ‹በዒድ አልአድሓ ቀን የሚፈጸም እርድ ነው፡፡›
3. በአነስ (ረ.ዐ.) ዘገባ የአላህ መልዕክተኛ (ሰ.ዐ.ወ.) ሁለት ቀንዳም የሆኑ በጎችን በማረድ አንዱ ለርሳቸውና ለቤተሰባቸው ሌላኛው ለተከታዮቻቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
4. ኢብኑ ዑመር (ረ.ዐ.) እንዳሉት ነቢዩ (ሰ.ዐ.ወ.) በመዲና ሳሉ አሥር አመት ሙሉ ኡድሒያ አርደዋል፡፡
5. ብያኔው ላይ የተለያዩ አስተያየቶች የተሰጡ ሲሆን አብዛኞቹ ዑለሞች ‹ሱና ሙአከዳ/ አጽንኦትና ክብደት የተሰጠው ሱና› ያሉ ሲሆን እነ ኢማም አቡ ሐኒፋና ኢብኑ ተይሚያ ደግሞ ‹ግዴታ ነው› ብለዋል፡፡
6. ኡድሒያ ለማረድ ኒያ ያለው ሰው አሥሩ የዚልሒጃ ቀናት ከገቡ በኋላ ፀጉሩንም ሆነ ጥፍሩን መቆረጥ የለበትም፡፡
7. ኡድሒያ ለማረድ ያሰበ ሰው እንሰሳውን ሲገዛም ሆነ ሲያርድ ኒያውን ማስገኘት ይኖርበታል፡፡
8. ኡድሒያ የሚታረደው ከዒድ ከሶላት በኋላ ነው፡፡ ከዒድ በኋላ ባሉት ሶስቱ ቀናት ውስጥም ማረድ ይቻላል፡፡ በላጩ ግን መልካምን ነገር ቶሎ ለመፈፀም መሽቀዳደም ነው፡፡
9. የዒድ አልድሓ ቀን ሳይበሉ መውጣት እንዲሁም ከሶላት ከተመለሱ በኋላ ካረዱት እንሰሳ መመገብ ሱና ነው፡፡
10. ለኡድሒያ የሚታረደው እንሰሳ ምርጥና ውድ፣ ሲያዩት የሚያምርና የሰባ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ሶሓቦች ለኡድሒያ የሚያርዱትን እንሰሳት በመቀለብ እስከ መታረጃው ቀን ድረስ ያሰቡ ነበር፡፡
11. ኡድሒያ ከእስልምና ምልክቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ የእስልምናን ምልክቶችን መገለጫዎች ማክበር አላህን የመፍራት ምልክት ነው፡፡
12. ለኡድሒያ የታረደውን እንሰሳ ሶስት ቦታ በመክፈል አንድ ሶስተኛውን መብላት፣ አንደ ሶስተኛውን ሀዲያ/ስጦታ መላክ እንዲሁም አንድ ሶስተኛውን ለድሆች መመጽወት ያስፈልጋል፡፡
13. ለኡድሒያ የሚታረዱ እንሰሳት በዋናነት በግ፣ ፍየል፣ ከብት እና ግመል ናቸው፡፡ ዶሮ ሆነ ሌሎች የሚበሊ እንሰሶች ለኡድሒያ አይበቁም፡፡
14. ለኡድሒያ የሚታረደው እንሰሳ በግ ከሆነ ስድስት ወር፣ ፍየል አንድ አመት፣ ከብት ሁለት አመት፣ ግመል አምስት አመት የሞላው መሆን ይኖርበታል፡፡
15. ግመልና ከብትን ለሰባት ሆኖ ማረድ ይቻላል፡፡
16. ለኡድሒያ የሚታረድ እንሰሳ ምንም ዓይነት እንከንን ነውር የሌለበት መሆን ይኖርበታል፡፡ ነውርና እንከን ሲባል ዐይኑ የጠፋ፣ የታመመ፣ የሚያነክስ፣ የከሳ፣ ያረጀ፣ ላቱ፣ ጆሮው ወይም ከአካል ከፍሉ አንዳች ነገር የተቆረጠና የመሳሰለውን ነው፡፡
17. ለኡድሒያ የሚታረድ እንሰሳ ቆዳው መሸጥ የለበትም፡፡ በአግልግሎት ክፍያ መልክም ለአራጅ መስጠት አይቻልም፡፡
18. የኡድሒያ ባለቤት ኡድሒያውን በራሱ እጅ ቢያርድ፣ በራሱ እጅም ቢያከፋፍል መልካም ነው፡፡ የአምልኮ ተግባር ነውና፡፡
19. በሚያርድበት ጊዜም ‹ቢስሚላህ አላሁ አክበር› በማለት ቀጥሎም ‹አልላሁም ሃዛ ዐንኒ ወዐን አህሊ በይቲ፡፡ አልላሁምመ ተቀብበል ሚንኒ/አላህ ሆይ! ይህ ከኔ እና ከቤተሰቤ ነው፡፡ አላህ ሆይ ተቀበለኝ› ማለት ይኖርበታል፡፡
20. ቤተሰቡ የበዛ ቢሆንም እንኳን ለሙሉ ቤተሰብ አንድ ኡድሒያ በቂ ነው፡፡
21. የሚታረደው እንሰሳ የራስ ንብረት መሆን አለበት፡፡ ያለባለቤቱ ፈቃድ፣ ሰርቆም ሆነ ነጥቆ ማረድ ተቀባይነት የለውም፡፡ በንጹህ እንጂ በውሸት ገንዘብ ወደ አላህ (ሱ.ወ.) አይቀረብምና፡፡
22. ለኡድሒያ ታስቦ አንድ ሰው አንድን በግ ወይም ፍየል መጋራት አይችልም፡፡ ከሰባት በላይ በሆነ ሰውም አንድን ከብት ማረድ አይበቃም፡፡
23. ኡድሒያን ከሰላት በፊት ማረድ አይቻልም፡፡ ከጊዜው በፊትም ሆነ ከጊዜው በኋላ ማረድ እንደማንኛውም ሥጋ እንጂ ኡድሒያ አትሆንም፡፡
24. አራጅ የእርድ ሥነሥርኣትን መጠበቅ አለበት፡፡ የሚታረደውን እንሰሳ ወደ ቂብላ ማዞር፣ የአላህን ሥም ማውሳት፣ አንደኛውን እንሰሳ ሌላኛው ፊት አለማረድ፣ የሚያርዱበትን ቢላዋ በሚገባ መሳልና ቶሎ ማሰረፍ ጥቂቶች ናቸው፡፡
25. ኡድሒያ ማረድ ለማይችል ሰው እሱን ነግሮና አስፈቅዶ ለሱ አስቦ ማረድ ይቻላል፡፡
26. ድሃ ሰው የተላከለትን የኡድሒያ ሥጋ መሸጥም ሆነ ሌላ የፈለገውን ነገር ማድረግ ይችላል፡፡
27. ኡድሒያን ሰው ወክሎ ማሳረድ ይቻላል፡፡ የሚታረደለት ሰውም ጸጉሩን ጥፍሩን ከመንካት መቆጠብ ይኖርበታል፡፡
28. ዑለማኦች ኡድሒያን ማረድ ያልቻሉ ሰዎች ሀሳብ ሊገባቸው እንደማይገባ ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም ነቢያችን (ሰ.ዐ.ወ.) ሁለት በጎችን በሚያርዱበት ወቅት አንዱን አቅም ለሌላቸው ህዝቦቻቸው አርደዋልና፡፡
29. ኡድሒያ የአላህን ትዕዛዝ ለመፈጸም ወደሱ መቃረቢያ ተግባር ከመሆኑም በላይ የመተዛዘንና የመተሳሰብ ተምሳሌት ነው፡፡ በዕለቱ ድሆች ጠግበው ይውላሉ፡፡ ሥጋ አያምራቸውም፡፡
30. የኡድሒያ ቀን አላህን ማውሳት የሚጎላበት ነው፡፡ ፀጋውንም ደጋግመን እናመሰግንበታለን፡፡ ቅኑንና ተወዳጁን ነቢይ ኢብራሂምን (ዐ.ሰ.) እና ልጃቸውን ኢስማዒልን እናስታውስበታለን፡፡
ወላሁ አዕለም፡፡
ነጃሺ የዕውቀት ማዕድ!
ኢዱን አላህን በማመስገን እና በማላቅ ትዕዛዛቱን በመፈፀም ታላቅ አጅር የምናገኝበት አላህ ያድረግልን!!
አሚን!!
አሚን!!
ይህን መልዕክት ሼር በማድረግም ላልደረሳቸው እናዳርስ
۩○◙◙○◙◙○◙◙○◙◙○۩
قال ابن القيم✅
من طلب العلم ليحيي به الإسلام
فهو من الصديقين ودرجته بعد درجة النبوة
مفتاح دار السعادة(1/121)
المدير
══❁[↶قـــــنـــــاة↷]❁══
↓ للإشتراك 📩
https://t.me/abuhasenat📚📚Eilme ሰው በሀቅ ያመዘናል እንጂ ሀቅ በሰው አያመዘንም 📚📚