ፆምና ህመም
~
ህመምተኞች ከፆም አንፃር ለአራት ይከፈላሉ።
1ኛ አይነት፦ በህመሙ ምክንያት በቋሚነት መፆም የማይችል ሰው
ህመሙ ይድናል ተብሎ ተስፋ የማይጣልበት ቋሚ ህመም ያለበት ሰው ልክ መፆም እንደማይችል ትልክ ሽማግሌ ሲሆን በኢጅማዕ ማፍጠር ይችላል። የፆም ግዴታ የለበትም። አላህ እንዲህ ብሏል
(لَا يُكَلِّفُ اللَّهُ نَفْسًا إِلَّا وُسْعَهَاَ)
"አላህ ነፍስን ከችሎታዋ በላይ አያስገድዳትም፡፡" [አልበቀረህ፡ 286]
ሚስኪን የማብላት ግዴታም የለበትም። ግዴታ እንደሆነ የሚያሳይ የቁርኣንም፣ የሐዲሥም፣ የኢጅማዕም አስገዳጅ ማስረጃ የለምና። ኢብኑ ሐዝምና ኢብኑ ዐብዲልበር ይህንን አበክረው ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ለእያንዳንዱ ቀን አንድ ሚስኪን ቢያበላ የተወደደ ነው። ምክንያቱም:-
1ኛ:- ከተለያዩ ሶሐቦች ተገኝቷልና። የብዙ ዑለማኦችም ምርጫ ነው።
2ኛ፦ ይህንን ሲፈፅም ራስን ከውዝግብም ያወጣል።
ይሄ እንግዲህ ማብላት ለሚችል ሰው ነው። ያልቻለ ምንም የለበትም።
* የምግቡ አይነት እቤቱ ከሚመገበው መካከለኛ ደረጃ ያለው ነው።
2ኛው አይነት ህመምተኛ፦ ህመም ቢኖርበትም መፆም የሚችል ነገር ግን በመፆሙ ህመሙ የሚባባስበት የሆነ ሰው ነው። ለዚህ አይነቱ ማፍጠር ግዴታ ነው። አላህ እንዲህ ብሏል:-
(وَلَا تُلْقُوا بِأَيْدِيكُمْ إِلَى التَّهْلُكَةَِ)
"በእጆቻችሁም (ነፍሶቻችሁን) ወደ ጥፋት አትጣሉ፡፡" [አልበቀራ: 195]
★ ባይሆን ሲሻለው ቀዷእ ያወጣል (በምትኩ ይፆማል።) አላህ እንዲህ ብሏል:-
{فَمَن كَانَ مِنكُم مَّرِیضًا أَوۡ عَلَىٰ سَفَرࣲ فَعِدَّةࣱ مِّنۡ أَیَّامٍ أُخَرَۚ}
"ከእናንተም ውሰጥ ህመምተኛ ወይም በጉዞ ላይ የሆነ ሰው ከሌሎች ቀኖች ቁጥሮችን መፆም አለበት።" [አልበቀረህ: 184]
3ኛው አይነት ህመምተኛ፦ መፆም የሚችል ሆኖ መፆሙ የሚያስከትልበት ጉዳት ባይኖርም ነገር ግን በህመሙ ምክንያት ፆም የሚከብደው ሰው
እንዲህ አይነቱ ማፍጠር ለሱ ግዴታ ባይሆንም በላጭ ነው። ኋላ ግን ቀዷእ ያወጣል።
4ኛው አይነት ህመምተኛ:- ቀላል ህመም ያለበት ሰው ወይም መፆሙ የማይከብደው እና ህመሙን የማያባብስበት የሆነ ሰው ሊያፈጥር ማለትም ፆሙን ሊፈታ አይፈቅድለትም። ለማፍጠር በቂ ምክንያት መኖር አለበት።
ማሳሰቢያ: –
* ህመምተኛ ህመሙን ችሎ ቢፆም ፆሙ በኢጅማዕ ይቆጠርለታል።
والله أعلم
=
* ቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor