🙏 🙏🙏
ቃና ዘገሊላ 🙏
#የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ
ወርሀ ጥር የሙሽርነት፣ ጎጆ የመውጫ ዘመን ነው፡፡ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ዘመነ መርዓዊ በመባል ከሚጠሩ ወቅቶች አንዱ ነው፡፡ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በገሊላ ቃና ሰርግ የታደመበት በዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 2 የሚገኘው ታሪክ በዚህ ቀን ይነገራል፡፡
በርካቶች የሚስቱበት በርካቶችም ለሕይወት የሚያደርጉት ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የታየበት፣ ንፁህ ውሃ ወደ ግሩም ወይን ጠጅ የተለወጠበት፣ ጌታችንም የመጀመሪያውን ተዓምራት ያሳየበት ነው፡፡ ከቅዱሳን ሐዋርያትና ከእናቱ ጋር በገሊላ ቃና ሰርግ የታደመው ኢየሱስ ክርስቶስ የወይን ጠጅ እንዳለቀ የተነገረው ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ነበር፡፡
“እርሱም አንቺ ሴት፥ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት፡፡ እናቱም ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። አይሁድም እንደሚያደርጉት የማንጻት ልማድ ስድስት የድንጋይ ጋኖች በዚያ ተቀምጠው ነበር፥ እያንዳንዳቸውም ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር። ኢየሱስም ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው።
አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደ መጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር፤ አሳዳሪው ሙሽራውን ጠርቶ" ሰው ሁሉ አስቀድሞ መልካሙን የወይን ጠጅ ያቀርባል፥ ከሰከሩም በኋላ መናኛውን፤ አንተስ መልካሙን የወይን ጠጅ እስከ አሁን አቆይተሃል አለው። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።”
ይህ “ከቁጥር 4–11” የሰፈረ ቃል የቅድስት ድንግል ማርያምን ምልጃ፣ በጎደለው ሁሉ የምታስጨምር እደሆነች ያሳያል፡፡ የዘመናችን ስሁታን “አንቺ ሴት ካንቺ ጋር ምን አለኝ?” ስላላት ክብር ይግባትና በውርደት ቃል እንደጠራት ይገልጻሉ፡፡ ይህ ግን በእስራኤላውያን ልማድ የሆነ አነጋገር ነው፡፡ “ጥያቄሽን እንዳልፈጽም የሚያደርግ ካንቺ ጋር ምን ጸብ አለኝ?” የሚል ትርጓሜም ይይዛል፡፡ ይህን ካላት በኋላ መግባባታቸውን የሚያሳየን ደግሞ “እናቱም ለአገልጋዮቹ።
የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው።” የሚለው ቃል ነው፡፡ የሰጣት ምላሽ በጎ ባይሆን ይህን ትዕዛዝ ለአገልጋዮቹ አታስተላልፍም ነበር፡፡ ከሠላሳ ዘመን በላይ አብራው የኞረችው እናቱ ናትና ንግግሩ የሚገባት ሀሳቧን የሚቀበል ነው፡፡ በዚያውስ ላይ እናትና አባትሕን አክብር ብሎ ትዕዛዝ የሰጠ አምላክ እንዴት እናቱን ዝቅ አድርጎ ተናገራት ልንል እንችላለን?
“ድንቅ ወይን ጠጅ ከንጹህ ውሃ ተገኘ፣ የሰርግ ቤቱም በደስታ ተሞላ፣ ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።” ስንል የሕይወታችንን ውሃ ንጽሕና እየጠየቅን ሊሆን ይገባል፡፡ በአባቶች ጸሎት በገዳማውያኑ ምልጃ ወደ መልካሙ ወይን ለመለወጥ በበጎ ምግባር እንሳተፍ፣ የሚለንን ሁሉ እናድርግ፡፡
ድጋፍ ለማድረግ:- ሙትአንሳ ማር ቅዱሰ ሚካኤል አንድነት ገዳም
ኢትዮጲያ ንግድ ባንክ
1000442598391
ወይም
አቢሲኒያ ባንክ
141029444
የገዳሙ ስልክ ቁጥር:-0918077957 ወይም 0938644444
🙏🙏🙏
🌴🌴🌴
https://www.facebook.com/share/p/1Af3zK1pSG/?mibextid=wwXIfr