⌲የተሳቀ እንባ
ክፍል አንድ
(ፉአድ ሙና)
.
"እማ" ትላለች አፏን በደንብ ያልፈታችው ህፃን ጀርባዋን ሰጥታ ወደ ውጪ እየተመለከተች የቆመችውን እናቷን እያየች። እናቷ ከታላቅ እህቷ ጋር ያወራሉ።
እናትየው ለመውጣት የተዘጋጀች ልጃቸውን እየተመለከቱ መናገር ጀመሩ።
"እና በቃ መውጣትሽ ነው? ምሳሽን ግን በደንብ በልተሻል?"
"ኧረ በደንብ በልቻለሁ። በቃ ልሂድ ደህና ዋይ።"
"ማን ጋ ነው ግን የምትሄጂው?"
"ቤቲን ላገኛት ነው።"
የቤቱን የውጪ በር ከፍታ ወጣች። እናትየው ከኋላቸው "እማ" እያለች የምትነጫነጨው ልጃቸውን ከምንጣፉ ላይ አንስተው አቀፏት።
.
በሩን ዘግታ ከወጣች በኋላ ወደ ፊቷ የተንሸራተተባትን ሻሿን የእጅ ቦርሳዋን ወደ ብብቷ አስገብታ ይዛ አስተካከለች። የወጣትነት የመጀመሪያው የፍካት ድባብ አብቦባታል። የሚያሳሳ የሰውነት ቅርፅ ፣ ሳሙኝ ሳሙኝ የሚል ከንፈር ሌላም ሌላም ብዙ የወጣትነት ፣ የመድረስ ምልክቶች ተንቆጥቁጠውባታል። ሀያት ከህፃንነቷ አንስቶ የምትጠራበት ስም ነው። ሀዩና ፣ ሀዩ ፣ ሀዩዬ እያሉ ያቆላምጧታል። ሀያት መልኳ የቀይ ዳማ ተብሎ የሚገለፅ አይነት ነው። መልኳ የተጋነነ ውበት ባይኖረውም ለክፉ የሚሰጥ አይነት አይደለም። የተጋነነ ውበት ያላቸውን የምንሰይምበት ቃል እንቸገራለን ብለን ባንሰጋ ቆንጆ ናት ልንላት እንችል ነበር። የጠመጠመችው ሻሽ የሀብሀብ የውስጡን ቀለም ይመስላል። በእነርሱ አጠራር "ፒች" የሚባል የቀለም አይነት ያለው ነው። ቀሚሷ ከሻሿ ጋር ተመሳሳይ ቀለም አለው። ከላይ እጀ ሙሉ ሸሚዝ ለብሳለች። ዛሬ ቅዳሜ ነው። እንደ ሀያት ላሉ ከሰኞ እስከ አርብ ያለውን ጊዜ በትምህርት ለሚያሳልፉ ተማሪዎች ውድ እና ተናፋቂ የእረፍት ቀን ነው። ከቤቷ ወጥታ ጥቂት በእግሯ ከተራመደች በኋላ ተክለሀይማኖት አደባባይ ደረሰች። ከተክለሀይማኖት የሜክሲኮ ታክሲ ይዛ ቅዳሜን አብረው ፏ ሊሉ ወደተቀጣጠረቻት ጓደኛዋ ቤቲ ተስፈነጠረች።
.
ቤቲ ከሀያት ቀደም ብላ ሜክሲኮ ከተቀጣጠሩበት ካፌ ተገኝታለች። ዳለቻ ቀለም ያለው ቱታ ሱሪ ፣ በከፊል ገላዋን አሳልፎ የሚያሳይ ስስ ጥቁር ሹራብ ለብሳለች። ከላይ ደግሞ ኮፍያ ደፍታለች። ቤቲ ፈታ ለቀቅ ያለች ልጅ ናት። ደስታን የምታድን አይነት።
ሀያት ከካፌው እንደደረሰች ሰላም ተባብለው ወደ ሞቀ ጨዋታ ገቡ። ሁለቱም የአስራሁለተኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸው። የሚማሩት በከተማዋ ውስጥ ታዋቂ ከሚባሉ የግል ትምህርት ቤቶች በአንዱ ነው። ጨዋታ እየደራ ሰዓቱ እየገፋ ሲመጣ ቤቲ ለሀዩ አንድ ሀሳብ አቀረበች።
"ሀዩ ዛሬ እኮ ከኤርሚ ጋር ቀጠሮ አለን። እሱም ከጀለሱ ጋር ስለሚከሰት አብረን ብንሄድስ?"
"ኧረ አይመሽብኝም?"
"ኧረ የምን መምሸት ነው? አግኝተናቸው ትንሽ ተጨዋውተን ላሽ እንላለን።"
ሀያት በሀሳቡ ተስማማች። ቤቲ ኤርሚያስ ጋር ደውላ ያሉበትን ቦታ ነገረችው። ሰዓቱ ወደ ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ተጠግቷል።
.
ቤቲ በርካታ ጊዜ የፍቅር ጓደኛ ይዛለች። መመቻቸት ሲደባበሩ ደግሞ ላሽ መባባል የፍቅቅሮሽ ህይወቷ መመሪያ ነው። ሀዩ ከዚህ ቀደም ረቢቅ የሚባል ፍቅረኛ ነበራት። ከሱ ጋር አብረው እያሉ የአፍላነት እሳታቸው ከንፈር ለከንፈር እስከመጎራረስ አዝልቋቸዋል። የቤቲ እንኳ በርካታ ስለሆኑ እና በጉዳዩ ላይም ዘልቃ ስለሄደችበት "ለሷ" ብርቅ የሚባል አይነት አይደለም። ኤርሚ ባለጊዜዋ ነው። ጊዜ ለፍቅረኝነት የመረጠላት። ሙድ ለሙድ ገጥመዋል። ተመቻችተዋል።
.
ኤርሚ የካፌው በር ላይ ሲደርስ ደወለላቸውና ከካፌው ወጡ። የካፌው በር ላይ አንድ ብርማ ኤክስኪዩቲቭ ቆማለች። ኤርሚያስ ከጋቢና ወረደና ቤቲን እና ሀዩን ሰላም ብሏቸው ቤቲን ይዞ ከኋላ ገባ። ሀያት የነገሮች ሂደት በመራት መልኩ ጋቢና ገባች። መኪናውን የያዘው የኤርሚያስ ጓደኛ ነው። ኢስማኢል ይባላል። ነጭ ጂንስ ሱሪ እና ነጭ እጀ ሙሉ ስስ ሹራብ ለብሷል። ከላዩ ላይ እጀ ጉርድ ጃኬት ደርቦበታል። ኤርሚያስ ጂንስ ቁምጣ ለብሷል። ከላይ የደረቱን ቅርፅ አጉልቶ በሚያሳይ ጥቁር እጀ ጉርድ ቲሸርት ተወጣጥሯል።
የመኪናው ሬዲዮ መንዙማ ያጫውታል። ቤቲ የመንዙማውን አንዱን ቃል ይዛ አብራ እያለች ትጨፍራለች። ጭንቅላቷን በድቤው ሪትም ልክ እየወዘወዘች ትቀውጠዋለች። ኤርሚም አብሯት እጁን እያወዛወዘ ይጨፍራል። እስማኢል የስልኩን ካሜራ ከፍቶ ጭፈራቸውን ይቀርፃል። ሀያት እየሳቀች ትመለከታለች።
ኢስማኢል የመኪናው ሬዲዮ ላይ ጣቱን አሳርፎ መንዙማውን አሳለፈው። እንግሊዘኛ ዘፈን ላይ ሆነ። ቤቲ መቀመጫዋን ከወገቧ ጋር በስልት እያሾረች ሁለት እጆቿን ዘርግታ ትደንሳለች። ተሳሳቁ ፣ ፈገጉ።
እስማኢል እጆቹን የመኪናው መሪ ላይ እንዳደረገ ሀያትን በአይኑ ሰርቆ አያት። ከዚያም ወደ ኋላ ዞሮ ወደ ኤርሚ ተመለከተ።
"እ ኤርሚ ወዴት ልንዳው?"
"ወደ ሳር ቤት ንዳው፣ ወደ ዶዲ"
መኪናዋ ወደ ሳር ቤት ተወነጨፈች። አራት የዘመኑን እሳቶች ይዛ። ሁለት የደረሱ ፈታኝ ሴትነቶችን አንከብክባ ፣ ከዶዲ ሬስቶራንት በር ላይ ቆመች ::
ᴘᴀʀᴛ ᴛᴡᴏ ይቀጥላል....
https://t.me/HANIF_TUBE01
♡ ㅤ ❍ㅤ ⎙ㅤ ⌲
ˡᶦᵏᵉ ᶜᵒᵐᵐᵉⁿᵗ ˢᵃᵛᵉ ˢʰᵃʳᵉ
╭─────────────
╰──➤ ✎ ❤️🩹𝕙𝕒𝕟𝕚𝕗