ታዋቂ ግን ደካማ ሐዲሦች እና ታሪኮች
(ክፍል አንድ)
~~~~~~~~~~~~~~~~
ባለማወቅ ወይም ባለማስተዋል ደካማ ሐዲሦችንና ታሪኮችን የምናወራበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በሰፊው ስንቀባበላቸው የነበሩ ታሪኮችና ሐዲሦች በዘርፉ ባለሙያዎች ተፈትሸው ደካማ እንደሆኑ ሲገለፁ እንደነግጣለን። እነዚህ ደካማ ዘገባዎች ከከባድ እስከ ቀላል ያሉ የተዛቡ ግንዛቤዎችን እንድንይዝ ሊያደርጉን ይችላሉ። ከፊሎቹ የጎላ አንድምታ ላይኖራቸው ይችላል። ውጤታቸው ምንም ይሁን ምን በሰፊው የምንቀባበላቸውን ዘገባዎች ደካማነት ማወቅ ጠቃሚ እንጂ ጎጂ አይደለም። በተለይም በከፊሎቹ ላይ ማወቁ ይበልጥ አንገብጋቢ ይሆናል። በመቀጠል ከነዚህ ታዋቂ ግን ደካማ ታሪኮች ለዛሬ የመረጥኳቸውን ለማቅረብ እሞክራለሁ። አብዛኞዎቹ መረጃዎች "አልመሽሁር ሚነ ዶዒፍ" ኪታብ ውስጥ ይገኛሉ።
1/ ቁረይሾች የነብዩ ﷺ አጎት አቡ ጧሊብ ዘንድ በመቅረብ ነብዩን ﷺ ወስደው እንዲገድሉ እና በሳቸው ምትክ ዑማረቱ ብኑል ወሊድን ለመስጠት እንደጠየቁ አቡ ጧሊብ ግን "ልጃችሁን እንድመግብላችሁ ልትሰጡኝ፣ የወንድሜን ልጅ ግን እንድትገድሉት ልሰጣችሁ ነው!" ብለው እንደመለሱ በሰፊው ይታወቃል። ይህ ደካማ ታሪክ ነው። [ማን ሻዐ ወለም የሥቡት ፊ ሲረቲ ነበዊያህ: 51] [ዶዒፉ ታሪኺ ጦበሪይ: 7/26]
2/ ነብዩ ﷺ ኸዲጃን ሲያገቡ 40 አመቷ ነበር የሚለው ምንም እንኳ በሰፊው የሚታወቅ ቢሆንም ከሰነድ አንፃር ግን ዶዒፍ ነው፣ ደካማ። [ማለም የሲሕ ሚነ ታሪኽ: 1/26] ከደካማ ዘገባዎች ባለፈ እድሜዋን የሚጠቁም ትክክለኛ ማስረጃ የለም።
3/ ቁረይሾች ለነብዩ ﷺ አንድ አመት የነሱን ጣኦቶች እንዲያመልኩላቸው፣ አንድ አመት ደግሞ የሳቸውን አምላክ (አላህን) ለማምለክ ጠይቀው ነበር የሚለውም እንዲሁ ደካማ ታሪክ ነው። [ማን ሻዐ ወለም የሥቡት ፊ ሲረቲ ነበዊያህ: 51] [አልኢስቲዓብ ፊ በያኒል አስባብ: 3/571]
4/ ጧሀ (ﻃﻪ) እና ያሲን (ﻳﺲ) ከነብዩ ﷺ ስሞች ውስጥ ናቸው የሚለው ዘገባ መሰረት የለውም። ኢብኑል ቀዪም እንዲህ ይላሉ:–"ያሲንና ጧሀ ከነብዩ ﷺ ስሞች ውስጥ ናቸው በማለት ተራ ሰዎች የሚጠቅሱት ትክክል አይደለም። ይሄ በሶሒሕም፣ በሐሰንም፣ በሙርሰልም ሐዲሥ አይገኝም። ከሶሐባ የተላለፈ ትውፊትም የለም። ይልቁንም እነዚህ ፊደላት የ ﺍﻟﻢ، ﺣﻢ، ﺍﻟﺮ، እና መሰል ፊደላት አምሳያ ናቸው።" [ቱሕፈቱል መውዱድ ቢዘሕካሚል መውሊድ: 165]
ሸይኽ ሙሐመድ አሚን አሺንቂጢም በሱረቱ ጧሀ ተፍሲር ላይ እንዲህ ብለዋል:– "እኔ ዘንድ በዚህ ላይ ያለው የጎላው አቋም በምእራፎች መግቢያ ላይ ከሚገኙ ፊደሎች ውስጥ መሆኑ ነው። በዚህ ምእራፍ ውስጥ የተጠቀሱት ጧእ እና ሃእ ፊደላት በመሆናቸው ላይ ውዝግብ በሌለበት በሌሎች ቦታዎች ላይ መምጣታቸው ይህንን ያመለክታል። ጧእ በአሹዐራእ (ﻃﺴﻢ)፣ በአነምል (ﻃﺲ) እና በአልቀሶስ መግቢያ ላይ መጥቷል። ሃእ ደግሞ ﻛﻬﻴﻌﺺ በሚለው የመርየም ምእራፍ መግቢያ ላይ መጥቷል።" [አድዋኡል በያን: 3/4]
ስለዚህ በሌሎች ሱራዎች መግቢያ ላይ የሚገኙት ፊደላት የነብዩ ﷺ ስሞች እንዳልሆኑት ሁሉ ጧሀ እና ያሲንም ከሳቸው ስሞች ውስጥ አይደሉም።
ብዥታ:–
አንደኛ:– "ለኔ ቁርኣን ውስጥ ሰባት (10) ስሞች አሉኝ። … ጧሀ፣ ያሲን፣ …" የሚለው በጣም ደካማ የሆነ ሐዲሥ ነው።
ሁለተኛ:– ከአንዳንድ ሰለፎችም የተጠቀሱ አሉ። ይሁን እንጂ ሰነድ አልባ ናቸው።
5/ ባለቤታቸው ኸዲጃ እና አጎታቸው አቡ ጧሊብ የሞቱበትን አመት "የሐዘን አመት (ﻋﺎﻡ ﺍﻟﺤﺰﻥ) ብለው መጥራታቸው በሶሒሕም በዶዒፍም ሐዲሥ አይታወቅም። [ማን ሻዐ ወለም የሥቡት ፊ ሲረቲ ነበዊያህ: 51]
6/ በጧኢፍ ጉዟቸው ጊዜ ከተደበደቡ በኋላ "አላህ ሆይ! የጉልበቴን መድከም፣ የብልሃቴን ማነስ፣ ከሰዎች ዘንድ መቅለሌንም፣… ወዳንተ ስሞታ አሰማለሁ" ብለዋል የሚለውም ደካማ ነው። [አዶዒፋህ: 2933] [ዶዒፉል ጃሚዕ: 1182]
7/ ነብዩ ﷺ ወደ መዲና በሚሰደዱ ጊዜ በሠውር ዋሻ ውስጥ ሳሉ እርግቦች እንቁላል ጥለዋል የሚለው ደካማ ነው። የነብዩን ስደት በማሰብ በሰፊው ቢተረክም የሸረሪቷና የእርግቦቹ ታሪክ ትክክል አይደለም ብለዋል ሸይኹል አልባኒ። [አዶዒፋህ: 2933] [አልቂሶሱል ዋሂያህ: 1/70]
8/ በዋሻው ውስጥ ሳሉ አቡበክርን እባብ ወይም ጊንጥ ነደፋቸው የሚለውም እንዲሁ መሰረተ ቢስ ነው። [አልቂሶሱል ዋሂያህ: 1/70] [አሲየር፣ ዘሀቢ: 1/313] [አልሚዛን: 2/454]
9/ ወደ መዲና ከአቡበክር ጋር እየተሰደዱ ሳሉ ሊይዛቸው መጥቶ ለነበረው ሱራቃ ብኑ ማሊክ አላህ የኪስራን አምባሮች ያለብስሃል ማለታቸውና ኋላ ላይ ዑመር አለበሱት የሚለውም እንዲሁ ደካማ ነው። ከሐሰኑል በስሪ "መራሲል" ውስጥ ነው። "ሙርሰል" ከደካማ የሐዲሥ አይነቶች ውስጥ ነው። የሐሰኑል በስሪ "ሙርሰሎች" እጅግ የወረዱ እንደሆኑ ኢማሙ ዘሀቢ ገልፀዋል። [አልሙቂዟህ: 17] [አልመሽሁር ሚነ ዶዒፍ: 329]
በሌላ በኩል ደግሞ ሐሰን ከዑመር ብለው አስተላልፈዋል። ነገር ግን ሐሰን ዑመርን አልደረሱባቸውም። ልብ በሉ! ከኪስራ አምባር ጋር የሚያያዘውን ብቻ ነው መጥቀስ የፈለግኩት። እንጂ ሌሎች የሱራቃ ታሪኮችን አይደለም።
10/ ነብዩ ﷺ ወደ መዲና ሲገቡ "ጦለዐል በድሩ ዐለይና ሚን ሠኒያቲል ወዳዕ…" እያሉ ተቀበሏቸው የሚለውም ደካማ ነው። ሰነዱ ውስጥ ሰፊ ክፍተት (ኢንቂጧዕ) አለበት። አልሓፊዙል ዒራቂ [ተኽሪጁል ኢሕያእ: 1/571] እና ኢብኑ ሐጀር [ፈትሑል ባሪ: 7/262] ሰነዱ "ሙዕዶል" እንደሆነ ገልፀዋል። "ሙዕዶል" ማለት በተከታታይ ሁለትና ከዚያ በላይ ዘጋቢ የወደቀበት ነው። ለዚያም ነው ሸይኹል አልባኒ ረሒመሁላህ ይህንን ታሪክ "ይሄ ደካማ ሰነድ ነው። ሰዎቹ ታማኞች ቢሆኑም ነገር ግን ‘ሙዕዶል’ ነው። ሶስት ወይም ከዚያ በላይ ዘጋቢዎች ከሰነዱ ላይ ወድቀዋል። ይህ (ዘጋቢው) ኢብኑ ዓኢሻህ ከ(ኢማሙ) አሕመድ ሸይኾች ውስጥ ሲሆን ኢርሳል አድርጎ ነው ቀጥታ ያወራው። … ስለዚህ ታሪኩ እንዳለ መሰረት ያለው አይደለም።" [አዶዒፋህ: 2/63]
ኢብኑል ቀዪም ደግሞ በስንኞቹ ውስጥ የተጠቀሰው "ሠኒያቱል ወዳዕ" ከመካ ወደ መዲና የሚገባ ሰው አያገኘውም። ምክንያቱም የሚገኘው በሻም በኩል ከመዲና በስተሰሜን ነውና ብለዋል። [ዛዱል መዓድ: 3/551]
ክፍል ሁለት በአላህ ፈቃድ ይቀጥላል።
Ibnu Munewor (ኢብኑ ሙነወር)
የቴሌግራም ቻናል። ይቀላቀሉ። ሌሎችንም ይጋብዙ።
https://t.me/IbnuMunewor