ዐሹራ (عاشوراء)
.
➊ አሹራ ሚባለው ምን ቀን ነው?
.
➪ አብዛኛዎቹ ኡለሞች ባሉበት አቋም መሰረት አሹራ የሚባለው ከሙሀረም አስረኛው ቀን ነው። አሹራም የተባለበት ምክንያት አስረኛው ቀን ለማለት ተፈልጎበት ነው።ልክ እንደዚሁ ዘጠናኛው ቀን ታሱአ ይባላል።
.
➦አንዳንድ ኡለሞች የሙሀረምን ዘጠነኛው ቀን ነው አሹራ ሚባለው ቢሉም ከቋንቋ አንፃር እንኳን ስናየው ትክክል አለመሆኑን እንረዳለን።
.🏷 የዘንድሮ የዐሹራ ቀን (ሙሐረም 10) ነገ እሁድ 9 ሲሆን ሰኞ 10 ነው በመሆኑም ዓሹራእ ሰኞ ስለሆነ እሁድና ሰኞን መፆሙ የተወደደ ነው አላህ ይወፍቀን ።አሏህ በሰላም ያድርሰን።
.
❷ አሹራ ሚፆመው ለምንድነው?
.
➪ የአሹራ ቀን የሚፆምበት ዋነኛ ምክንያት አላህ ሙሳን እና በኒ ኢስራኢሎችን ከፊርአው ነፃ ያወጣበት ቀን ስለሆነ ነው።
.
▩ ማስረጃው
.
ኢብን አባስ እንዲህ ይላል
(( የአላህ መልእክተኛ ﷺ መዲና ሲገቡ አይሁዶች የአሹራን ቀን ሲፆሙ አዯቸውና
"ይህ ምንድነው?" ብለው ጠየቋቸው
ከዛም የሁዶች ሲመልሱ
" ይህ ደግ ቀን ነው አላህ በኒ ኢስራኢሎችን ከጠላታቸው ነፃ ያወጣበት ቀን ነው። ሙሳ ለምስጋና ፆሞታል" አሉ
የአላህ መልእክተኛም ﷺ
"እኔ በሙሳ ከናንተ ይበልጥ ተገቢ ነኝ" አሉና ፆሙት በመፆምም አዘዙ
📚(ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል)
.
❸ የአላህ መልእክተኛ ﷺ ፆመውታል?
.
➩ አዎ የአላህ መልእክተኛ ﷺ የአሹራ ፆምን ይፆሙት ነበር
.
▩ ማስረጃው
.
አኢሻ እንዲህ ትላለች
(የአሹራ ቀን ቁረይሾች በጃሂሊያ ግዜ ይፆሙት ነበር የአላህ መልእክተኛም ﷺ ይፆሙት ነበር...)
📚ቡኻሪና ሙስሊም ዘግበውታል
.
❹ ከሙስሊሞች ውጪ ይህን ቀን ሚፆሙት አሉ?
.
➪ አዎ ከሙስሊሞች ውጪም ይህን ቀን ሚፆሙት ነበሩ እነሱም
.
➀ ሙሽሪኮች ፦ማስረጃው ከላይ በተራ ቁጥር ❸ ላይ ያሳለፍነው የአኢሻ ሀዲስ ነው
.
➁ አይሁዶች ፦ማስረጃው ከላይ በተራ ቁጥር ❷ ላይ ያሳለፍነው የኢብን አባስ ሀዲስ ነው
❺ ግዴታ ነው ወይስ ሱና?
.
➪ ረመዳን ከመደንገጉ በፊት የአሹራ ፆም ሙስሊሞች ላይ በግዴታነት መልኩ ተደንግጎ እንደነበር የሚጠቁሙ ሀደሶች አሉ ከነዛህ መሀከል ኢማም ቡኻሪ የዘገቡት የሰለማ ቢን አውከአ ሀዲስ አንዱ ነው። በዛ ሀዲስ ላይ መልእክተኛው ﷺ ሳያቅ ጠዋቱን የበላ ሰው የተቀረውን የቀን ክፍለ ግዜ እንዲፆም አዘዋል።
.
➪ ይህ የግዴታነት ትእዛዝ ግን በሗላ ላይ ተሽሮ በበርካታ ሀዲሶች ላይ እንደመጣው የአላህ መልእክተኛ ﷺ የፈለገ ሰው ይፁም ብለው ተናግረዋል።
.
▩ በመሆኑም የአሹራ ፆም የጠነከረ ሱና እንጂ ግዴታ አደለም።
.
❻ አስረኛው ቀን ብቻ ነው ሚፆመው?
.
➪ የአሹራን ቀን ብቻውን ነጥሎ ከመፆም ይልቅ ከሱ በፊት አንድን ቀን አስቀድሞ ፆሞ የአሹራንም ቀን አንድ ላይ መፆሙ የተወደደ ነው።
.
➦ ይህ ማለት ዘጠነኛውንና አስረኛውን ቀን ማለት ነው።
.
➦ ወይ ደግሞ አስራ አንደኛውንም ቀን አስከትሎ መፆሙ ይወደዳል።
.
▩ ማስረጃውም
.
አብደላህ ኢብን አባስ ባወራው ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ እንዲህ ብለዋል
"አላህ ካለ የሚመጣው አመት ዘጠነኛውን ቀን እንፆማለን"
ነገር ግን የሚቀጥለው አመት ሳይመጣ መልእክተኛው ሞቱ
📚 ሙስሊም ዘግቦታል
.
▤ አንድ ቀን አስቀድሞ ወይም ደግሞ አንድ ቀን አስከትሎ መፆሙ የተደነገገበት ምክንያትን ኡለሞች ሲያብራሩ ብዙ የሚጠቅሷቸው ነገሮች ቢኖሩም በዋነኝነት ግን ከአህለል ኪታቦች ለመለየት ሲባል የሚለው ይበልጥ ሚዛን ይደፍል።ምክንያቱም የአላህ መልእክተኛ ሚቀጥለው አመት ብደርስ ዘጠነኛውን ቀን ጨምሬ እፆማለው ያሉት አስረኛውን ቀን አህለል ኪታቦች እንደሚያልቁት ሲነገራቸው ነው።
.
➪ አንዳንድ ኡለሞች አስረኛውን ቀን ብቻ ነጥሎ መፆሙ የተጠላ እንደሆነ ይገልፃሉ።
.
➦ ነገር ግን ሸይኹል ኢስላም ዘጠነኛውን ወይም አስራ አንደኛውም መፆም ላልቻለ ሰው አስረኛውን ብቻ ቢፆምም እንደማይጠላ ይገልፃል። የሚችል ሰው ግን አስረኛውን ብቻ መነጠሉ ተገቢ እንዳልሆነ ይጠቅሳል።
.
❼ የሚወደደው አፇፇም
.
➪ የሚወደደው አፇፇም በቅደም ተከተል ሲቀመጥ
.
⓵ ዘጠነኛውን አስረኛውንና አስራ አንደኛውን ቀን ሶስቱን በተከታታይ መፆም (3 ቀኖች)
.
⓶ ዘጠነኛውንና አስረኛውን መፆም (2 ቀኖች)
.
⓷ አስረኛውን ቀን ብቻ መፆም (1 ቀን)
.
📚ይህንን ቅደም ተከተል ኢብኑል ቀይም ዛደል መአድ ላይ እንዲሁም ኢብን ሀጀር ፈትሀል ባሪ ላይ መርጠውታል። ኢብን ተይሚያም ኢቅቲዳ ኪታቡ ላይ ከኢማም አህመድ የዚህን አምሳያ ጠቅሷል።
.
➦ በርግጥ ሌሎች ኡለሞች የመረጣቸው ሌሎች ቅደም ተከተሎች ቢኖሩም ከመጡ ሀዲሶች አንፃር ከላይ የጠቀስነው ቅደም ተከተል ይበልጥ አመዛኙ አቋም ነው።
.
❽ የአሹራ ፆም ያለው ትሩፍት
.
➪ ኢማሙ ነሳኢ በዘገቡት ሀዲስ የአላህ መልእክተኛ የአሹራ ፆም ያለፈውን አመት ወንጀል ያስምራል ብለዋል።
.
✍🏾 ኻሊድ ሙሀመድ (አቡ ሱለይማን)
#ሼር
¶
https://t.me/alfiqhulmuyser ¶