🌺 ሒጃብ ለምን አስፈለገሽ ?🌺
ሴት ልጅ የተሟላ ሂጃብ በመልበስዋ ወንዶች እርሷን አይተው ከመፈተን ትጠበቃለች፤ መከላከያ ትሆናለችም።
እንዲህ በማድረጓ አይናቸውን ሰበር ለሚያደርጉ ብርቅዬዎች ብቻ ሳይሆን ላይ ታቹን ለሚቀላውጡትም አደብ ታስገዛበታለች፡፡
ምክንያቱም ውበቷ ፣ መስህቧ ስለተደበቀ ምንም ቢቁለጨለጩ የሚያገኙት ነገር የለምና ነው፡፡
ነገር ግን በተቃራኒው ማራኪ ገፅታዋ የሚታይ የምትገላለጥ ከሆነ ፈታኙ የጥፋት በር በማይዘጋ መልኩ ይበረገዳል፡፡
በዘመናችን ያለውን ሁኔታ ላስተዋለ አላህ በእዝነቱ የጠበቃት ካልሆነች በስተቀር ሴት ልጅ በገዛ እጇ ክብሯን አሽቀንጥራ እንደ ወረወረች ግሃድ ይሆንለታል፡፡
በዚህም ሰበብ ለስሜታቸው ላደሩት መቀለጂያና መጠቋቆሚያ ሆናለች።
እኒህ አይነቶቹ ቂሎች ለራሳቸው ተጃጅለው እሷንም ለማደንዘዝ አይንሽ፣ ከንፈርሽ፣ ዳሌሽ ውብ ነው ቅብርጥሴ እያሉ በማማለል ለማይረግበው ስሜታቸው ማርኪያ ሎሌ አድርገዋታል፡፡
እርሷም እነዚህ መርዘኛ ቃላቶች ባሳደሩባት ተፅዕኖና ባሳረፉባት ጠባሳዎች ተደንቃ ውብ መሆኗ የተነገረላት እስኪመስላት በሐሴት ተሞልታ እነሱ ለፈለጓት አላማ በማደር የወሲብ መግነጢሳቸው ሰለባ ሆናለች።
ይባስ ብላም አሁን አሁን ለዚህ አባዜያቸው የህይወት መስዋዕትነትም እየከፈለችበት ይገኛል፡፡
እንደምን ይሆን ብትሉኝ ለዚሁ ከንቱ አላማ ስትል ባላት ውበትና መስህብ አልብቃቃ ብላ ከሜካፕ ተሻግራ የአካል ለውጥ ለማድረግ አፍንጫዋን፣ አይኗን ፣ከንፈሯንና ቅርፅዋን ለማሳመር በሚልም ሆድና የመሳሰሉትን አካላቷን በቀዶ ጥገና መዘልዘልን ተያይዛዋለች።
የሚገርመው ነገር ይህ አምሮና ሸንቅጦ መቅረብ ላገባችው ባል ወይም በቁምነገር ለጋብቻ ላጫት ወንድ ሳይሆን ለተመልካችና ለሌሎች ፈላጊዎች ለውድድር ለመቅረብ ነው።
ለውበቷ ስትል ህይወቷን መስዋእት ለማድረጓም ይህ ሩጫዋ በቂ ምስክር ነው፡፡
ይህን መሰል ከምእራቡ አለም የመጣው አባዜ ሙስሊሙንም አለም እየናጠው ይገኛል፡፡
እነዚያስ ስለ ኣኺራቸው ስለማያስቡ ፣ ለዱንያ ላይ ክብርና ስብእና የሚሰጡት ትርጓሜ የላሸቀ በመሆኑ ለዚህ ተዳርገዋል። የኛዎቹን ግን ምን ነካቸው?
በተጨማሪም ልታውቂው ሚገባው ነገር ምእራቡም ሆነ ተከታዮቹ ምስራቁ አለም ዘንድ ልብስን ሲለብሱ ለጌጥነት እንጂ ለመሰተርያነት እንደማይውል ነው፡፡
አንዲት ዘመነኛ ነኝ የምትል ሴት ከመልበሷ በፊት የምታስበው ያምርብኛል ? ይስባል ? የሚሉትን ተራ ግብ ይዛ ነው ምትነሳው።
ሙስሊሞች ዘንድ ግን የዚህ ተቃራኒ ነው ፡፡
ልብስ ሲባል በቅድሚያ መሰረታዊ አላማው ሀፍረተ ገላን መሸፈኛ ነው።
ማራኪና መስህብነት ያላቸውን ጌጦቿን ሁሉ መደበቂያ ነው፡:
የሴት ልጅ አካል ደግሞ ሁሉም ሳቢና ማራኪ ነው።
አይደለም የሚዳሰስና የሚታየው ቀርቶ አረማመዷ፣ አነጋገሯና አስተያየቷ እንዲሁም ከጅልባብ ስር የምትለብሳቸው ልብሶች እንኳን ልብን ይረብሻሉ ፤ በሽታውንም ይቀሰቅሳሉ።
ለዚህም ነው አላህ አዝዘ ወጀልለ ከመልእክተኛው ሰለላሁ አለይሂ ወሰለም ባለቤቶች ጋር አያይዞ ሴቶችን ሲመክር እንዲህ ያለው:
”... إِنِ اتَّقَيْتُنَّ فَلَا تَخْضَعْنَ بِالْقَوْلِ فَيَطْمَعَ الَّذِي فِي قَلْبِهِ مَرَضٌ وَقُلْنَ قَوْلًا مَّعْرُوفًا.“
الأحزاب ﴿٣٢﴾
« … ያ በልቡ ውስጥ በሽታ ያለበት እንዳይከጅል በንግግር አትለስልሱም፡፡ መልካምንም ንግግር ተናገሩ፡፡
አል አህዛብ (32)
የልብስን ዋነኛ ፈኢዳና ግብንም እንደሚከተለው ገልፇል:-
” يَا بَنِي آدَمَ قَدْ أَنزَلْنَا عَلَيْكُمْ لِبَاسًا يُوَارِي سَوْآتِكُمْ وَرِيشًا ۖ وَلِبَاسُ التَّقْوَىٰ ذَٰلِكَ خَيْرٌ ۚ ذَٰلِكَ مِنْ آيَاتِ اللَّـهِ لَعَلَّهُمْ يَذَّكَّرُونَ “
الأعراف ﴿٢٦﴾
« የአዳም ልጆች ሆይ ! ኀፍረተ ገላችሁን የሚሸሽግን ልብስ ጌጥንም በእርግጥ በናንተ ላይ አወረድን፡፡ አላህን የመፍራትም ልብስ ይህ የተሻለ ነው፡፡ ይህ ከአላህ ታምራቶች ነው፡፡ ይገሠፁ ዘንድ (አወረደላቸው)፡፡ »
አል አዕራፍ (26)
ከተፈቀዱላት የወንድ አይነቶች በስተቀር ሴት ልጅ ሂጃብ እንድታደርግና እንዳትገላለጥላቸው ትእዛዝ ተላልፏል፡፡
ለዚህም የሚረዳውና አላህም በቅድሚያ የሚፈልገው የተቅዋ ልብስን ነው። ምክንያቱም አላህን የፈራች ሴት የታዘዘችውን የአለባበስ ስርኣት ለመተግበር አይከብዳትምና።
አላህ ያላወቅነውን መልካም እውቀት ያሳውቀን። ባወቅነውም እንድንሰራበት ይወፍቀን።
@eross