ተራዊህ በ20 ረከዐዎች አሀዝ የተጀመረዉ በሰይድ ዑመር ዘመን መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሰይድ ዑስማን ዘመንም ይኸዉ ልምድ አልተቋረጠም፡፡ ያን ጊዜ ተራዊህ የማሰገዱ ኃላፊነት በአብዛኛዉ የሰይድ ዐሊ እብን አቢጣሊብ እንደነበር የሚያመለክቱ ዘገባዎች ተላልፈዋል፡፡ በሰይድ ዐሊ ዘመንም የተለየ ነገር አልተዘገበም፡፡ ሰይድ ዐሊ እንዲህ ማለታቸዉ ተዘግቧል፡-
نوَّر اللهُ على عمر قبره، كما نوَّر علينا مساجدنا
‹‹ዑመር መስጊዶቻችንን እንዳበሩልን አላህ ቀብራቸዉን ያብራላቸዉ፤››[i]
ስለዚህ በሰይድ ዑስማንና በሰይድ ዐሊ ዘመን የሰይድ ዑመርን የ20 ረከዐዎች አሀዝ የሚቀይር እርምጃ መወሰዱን የሚያሳይ ሁነኛ ዘገባ ስለሌለ ሁኔታዎች በነበሩበት መልኩ እንደቀጠሉ መረዳት ይቻላል፡፡ የኢማም ቲርሚዚ (209-279 ሂ) ተከታዩ ማጠቃለያ የዚህን ድምዳሜ ትክክለኛነት ያጸናል፡-
أَكثرُ أَهل العلم على ما رُويَ عن عمر، وعليٍّ، وغيرهما من أَصحاب النبي r :عشرين ركعة وهو قول سفيان الثوري، وابن المبارك، والشافعي، وقال الشافعي: وهكذا أَدركت ببلدنا بمكة يصلُّون عشرين ركعة
‹‹ብዙሀን ዑለሞች ከዑመር፣ከዐሊና ከሌሎች ሶሀቦች ተገኘዉን 20 ረከአ የመረጡ ሲሆን፣ይህ የሱፍያነ ሰዉሪ፣የእብን ሙባረክና የሻዒም ምርጫ ነዉ፡፡ ሻፊዒ፡- ‹በሀገራችን መካ 20 ረከዐዎችን ሲሰግዱ ነዉ ያገኘኋቸዉ› ብለዋል፤››[ii]
እስካሁን የተሰጠዉ ማብራሪያ የሰይድ ዑመር ተራዊህን በአንድ ኢማም ስር በጀማዐ የማሰገድ ጥረት በአሀዝ ረገድ በ20 ረከዐዎች ተራዊህና በ3 ረከዐዎች ዊትር፣በድምሩ በ23 ረከዐዎች እንደጸና በማያሻማ ሁኔታ ግልጽ አድርጓል፡፡ ይህ አሀዝ በኹለፋኡ ራሽዲንና በሌሎች ሶሀቦች ሙሉ ስምምነት፣ያለተቃዉሞ እንደፀናም ግልጽ ሆኗል፡፡ ከላይ የተዘረዘሩት መረጃዎችና የዑለሞች ገለጻዎች 20 ረከዐ የተራዊህ ሶላት አሀዝ በብዙሀን ሶሀቦች የጸደቀ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸዉ፡፡ የኢማም አህመድ እብን ሀንበልን መዝሀብ በማደራጀቱ ረገድ ጉልህ ድርሻ ያላቸዉ ኢማም እብን ቁዳማህ ‹‹አል ሙግኒ›› በተሰኘ ኪታባቸዉ ጁ፣2 ገጽ 167 ይህ አሀዝ ለ‹‹ኢጅማዕ›› ቀረብ ያለ መሆኑን አስረግጠዉ ጽፈዋል፡፡ መራቂል ፈላህ ከተሰኘዉ የሀነፍይ መዝሀብ ኪታብ ዉስጥም ተመሳሳይ ሀሳብ ሰፍሮ እናገኛለን፡-
وهي عشرون ركعة ) بإجماع الصحابة رضي الله عنهم ( بعشر تسليمات ) كما هو المتوارث
‹‹የተራዊህ ሶላት 20 ረከዐዎች መሆኗና በአስር መሰላመቶች እንደምትጠናቀቅ በሶሀቦች ኢጅማዕ የጸደቀና ከጥንት ይዞ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ አተገባበር ነዉ፤››[iii]
አልካሳኒ (አስከ 587 ሂ) ተመሳሳይ ሀሳብ አስፍረዋል፡-
جَمَعَ عُمَرُ أَصْحَابَ رَسُول اللَّهِ صَلَّى اللَّهُ عَلَيْهِ وَسَلَّمَ فِي شَهْرِ رَمَضَانَ عَلَى أُبَيِّ بْنِ كَعْبٍ - رَضِيَ اللَّهُ تَعَالَى عَنْهُ - فَصَلَّى بِهِمْ عِشْرِينَ رَكْعَةً ، وَلَمْ يُنْكِرْ عَلَيْهِ أَحَدٌ فَيَكُونُ إِجْمَاعًا مِنْهُمْ عَلَى ذَلِكَ
‹‹ዑመር የአላህን መልዕክተኛ ሶሀቦች በወርሀ ረመዳን በኡበይ እብን ከዕብ ኢማምነት ሥር ሰብስበዉ 20 ረከዐዎችን አሰግደዋል፤ ከሶሀቦች መካከል አንዳቸዉም የዑመርን ድርጊት አለመንቀፋቸዉ ስለተረጋገጠ ይህ አሀዝ በኢጅማዕ የጸና ሆኗል፡፡››[iv]
የሀንበሊ መዝሀብ ሊቅ የሆኑት አል በሁቲ (1000-1051 ሂ) እንዲህ ደምድመዋል፡-
وهي ( عشرون ركعة في رمضان ) لما روى مالك عن يزيد بن رومان قال كان الناس يقومون في زمن عمر في رمضان بثلاث وعشرين ركعة والسر فيه أن الراتبة عشر فضوعفت في رمضان لأنه وقت جد وهذا في مظنة الشهرة بحضرة الصحابة فكان إجماعا
‹‹ተራዊህ በረመዳን ወር ዉስጥ የምትሰገድ 20 ረከዐዎች ሶላት ናት፤ ሰዎች በዑመር ዘመን በረመዳን ዉስጥ 23 ረከዐዎችን ይሰግዱ እንደነበር የዚድ እብን ሩማን መናገራቸዉን ማሊክ ዘግበዋል፤ይህ ዘገባ የአሀዙ መነሻ ነዉ፤ ተራዊህ 20 ረከዐዎች የተደረገችበት ሚስጥሩ ረዋቲብ ሱናዎች አስር ስለሆኑ የነርሱ እጥፍ ለማድረግ ታልሞ ነዉ፡፡ ምክንያቱም ረመዳን የበለጠ ትጋት ይፈልጋልና፡፡ ይህ አሀዝ ሶሀቦች በተገኙበት በአደባባይ የጸደቀ ስለሆነ በኢጅማዕ የጸና ሆኗል፤››[v]
ከሶሀቦች በኋለም ይህ የስምምነት መንፈስ ተጠብቆ መቆየቱን ሊቃዉንት ይገልጻሉ፡-
كَانَ عَلَيْهِ عَمَل الصَّحَابَةِ وَالتَّابِعِينَ
‹‹የሶሀቦችና የታቢዖች ትግበራ ይኸዉ ነበር፤››[vi]
عَلَيْهِ عَمَل النَّاسِ شَرْقًا وَغَرْبًا
‹‹ከምስራቅም እስከምዕራብ የሰዎች ትግበራ በዚሁ አሀዝ ላይ የጸና ነዉ፤››[vii]
هُوَ الَّذِي عَلَيْهِ عَمَل النَّاسِ وَاسْتَمَرَّ إِلَى زَمَانِنَا فِي سَائِرِ الأْمْصَارِ
‹‹በሌሎች ከተሞችም ዉስጥ እስካለንበት ዘመን ድረስ የጸና የሰዎች ትግበራ ነዉ፤››[viii]
የአራቱ የፊቅህ መዝሀቦች ዕይታ የሶሀቦችን ኢጅማዕ ያከበረ ነዉ፡፡ይህን የጋራ ስምምነት መድፈር የተጀመረዉ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡
ለተጨማሪ መልዕክቶች የቴሌግራም ቻነሌን ይከታተሉ፤
https://t.me/hassentaju[i] እብን ቁዳማህ፣አል ሙግኒ ፊፊቅሂል ሀንበሊ 2/167
[ii] ሱነን ቲርሚዚ
[iii] መራቂል ፈላህ ሸርህ ኑረል ኢዳህ፣ገጽ 183
[iv] በዳኢዑ ሶናኢዕ 1/288
[v] ከሻፉል ቀናዕ 1/425
[vi]ሀሽየቱ ዱሱቂ 1/315
[vii] እብን ዐቢዲን፣ረዱል ሙህታር 1/474
[viii] ሰንሁሪ፣ሸርሁ ዘርቃኒ 1/284