🔈 #የሹፌሮችድምጽ
“ የጸጥታ አካላት ጥበቃ ባለማድረጋቸው ለአጃቢ እስከ 2,000 ብር ለመክፈል ተገደናል። በቀናት ብቻ ከ12 በላይ ሹፌሮች ታግተዋል ” - ማኀበሩ
የጸጥታ መደፍረስ በሹፌሮችና ተሳፋሪዎች ግድያና እገታ ማስከተሉን፣ የጸጥታ አካላት ጥበቃ ባለማድረጋቸው አሽከርካሪዎች ለአጃቢ 2,000 ለመክፈል መገደዳቸውን ጣና የአሽከርካሪዎች ማኀበር ለቲክቫህ ኢትዮጵያ ገለጸ።
“ የጸጥታ አካላት ጥበቃ ባለማድረጋቸው ለአጃቢ እስከ 2,000 ብር ለመክፈል ተገደናል። በቀናት ብቻ ከ12 በላይ ሹፌሮች ታግተዋል ” ሲልም በሁነቱ ተማሯል።
በአማራ ክልል ከገንዳውሃ ወደ ጎንደር ባለው መንገድ ረቡዕ ጥር 28 ቀን 2017 ዓ/ም አንድ ሰው ተገድሎ፣ ሁለቱ ደግሞ መቁሰላቸውን ገልጿል።
“ በአስር ቀናት ደቡብ ጎንደር 3 ሹፌሮች፣ በደባርቅ ዙሪያ 2 ረዳቶችና 6 ሹፌሮች፣ ገንዳውሃ 2 ሹፌሮች፣ አብርሃጀራ አንድ ሹፌር በታጠቁ አካላት ታግተዋል። በአብርሃጅራ ሹፌር ተተኩሶበት አምልጧል፤ ሁለት ቦቴዎችን ወቅንና ገደብዬ መካከል አግተዋቸዋል ” ነው ያለው።
ማኀበሩ ለቲክቫህ ኢትዮጵያ በሰጠው ቃል በዝርዝር ምን አለ ?
“ ከአሸሬ እስከ ሶረቃ የሚያስፈራ ቦታ አለ። በፈቃድ ለታጠቁ የአካባቢው ሰዎች 2,000 ብር እየከፈልን ነው የምናልፈው። በቅርቡ አንድ አጃቢ አጋች መትቷል ሹፌር ሊያግት ሲል ወርዶ ተኮሰበት።
ጨንቆን ነው እንጂ ይሄ ሂደት ደግሞ መጥፎ ነው። ህግ ባለመከበሩ ምክንያት ለሹፌሮች እለታዊ መፍትሄ ሆኗል። ግን የአጃቢነት ስራ እየሰሩ ያሉ ሰዎች እንዴት ነው የአካባቢ ሰላም እንዲመለስ የሚፈልጉት?
ስለዚህ እገታ ያለባቸው ቦታዎች ይታወቃሉ። በአርማጭሆ በኩል ከከተማው አፍንጫ ስር ከ10 ጊዜ በላይ እገታ ተፈጽሞበት ቦታው ላይ የጸጥታ አካል አይቀመጥም።
የጸጥታ ዘርፉ ትኩረት ቢሰጥ ችግሩን መቆጣጠር ይችላል። ምክንያቱም በአንድ አጃቢ ከፍለን የምናልፈው አካባቢ ነው። መዝረፊያ በሮች የሚታወቁ ናቸው” ብሏል።
ለአጃቢ ከመክፈል በተጨማሪ ሹፌሮች ከጸጥታ ስጋት አንጻር በ100ዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮችን ዙሪያ ጥምጥም እንዲጓዙ እየተገደዱ መሆኑም ተገልጿል።
ማኀበሩ በመንገዱ ዙሪያ ምን አለ ?“ በደባርቅ በኩል ባለው መንገድ ከደብረ ታቦር ጋይንት መንገዱ ችግር ትልቅ አለበት። መንገዱ አማራ ክልል ከጅቡቲ የሚገናኝበት ነው። ማደበሪያ የሚገባው በጋይንት ነው። በሚሌ፣ ጭፍራ፣ ሃራ፣ ወልዲያ አድርጎ በደብረ ታቦር አድርጎ ይመጣል።
ግን ማዳበሪያ የሚጭኑ ተሽከሪካሪዎች በዚህ አመት በጸጥታው ችግር ምክንያት ተጨማሪ መንገድ እየተጓዙ በአዲስ አበባ በኩል ለመምጣት ተገደዋል። ከደጀን በእጀባ ነው የሚመጡት ወደ ጎጃምና ጎንደር ጭምር።
በጸጥታው ችግር ተሽከርካሪዎች ከ500 ኪሎ ሜትር በላይ ተጨማሪ መንገድ ለመሄድ ተገደዋል። ይህ ለአርሶ አደሩም ጉዳት አለው። 1,950 ብር ነው አንድ ኩንታል ማዳበሪያ ከጅቡቲ የሚመጣው። ትራንስፓርት ኮስቱ 1,900 ብር ሲሆን፣ የማዳበሪያው ዋጋ ይንራል።
በጋይንት ቦቴዎች ይሄዳሉ። ጭነው ይመጡና በጸጥታው ችግር መመለሻ ሲያጡ በደባርቅ፣ ዛሪማ፣ በሽሬ፣ ከሽሬ መቀሌ፣ ከመቀሌ አብዓላ አድርገው በአፍዴራ ይወጣሉ። ይሄ ማለት ከ600 በላይ ተጨማሪ ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ።
በጎንደር መተማ መንገድ በመተማ በኩል ነው ኢምፖርት ኤክስፖርት የሚገባው። የመተማ ጎንደርን መንገድ የጸጥታ ችግሩን በመፍራት አሽከርካሪዎች በአብርሃጅራ ዙረው እየገቡ ነው።
180 ኪሎ ሜትር ሲጓዙ የነበሩ አሽከርካሪዎች 140 ኪሎ ሜትር በመጨመር 320 ኪሎ ሜትር ይጓዛሉ ” ብሏል።
(ስለጉዳዩ ለጸጥታ አካላት ጥያቄ የምናቀርብ ይሆናል)
#TikvahEthiopiaFamilyAA
@tikvahethiopia