በአቃቂ ቃሊቲ ቤቶችን በማኅበር የተቀበሉ ነዋሪዎች ከሕግ አግባብ ውጭ ታግደናል ሲሉ ቅሬታቸውን አቀረቡ! በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በሕጋዊ መንገድ በማኅበር ተደራጅተው የመሬት ባለንብረት መሆን የቻሉ ማኅበራት ከ4 ዓመታት ወዲህ በክፍለ ከተማውና በከተማ አስተዳደሩ 'የኦዲት ግኝት ችግር ያሉባቸው ማኅበራት አሉ' በማለት፤ ማንኛውንም አይነት እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳይችሉ ያለአግባብ መታገዳቸውን ለአሐዱ ባቀረቡት ቅሬታ ገልጸዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ 1997 ዓ.ም ሕጋዊ አሠራሩን በጠበቀ መልኩ በመደራጀት የቤት ባለንብረት መሆን መቻላቸውን ጠቁመው፤ አንድ ማኅበር ውስጥ 12 አባወራ አባላት መኖራቸውን ተናግረዋል።ሁሉም አባላት 94 ካሬ መሬት ይዞታ እንዳላቸውና ሕጋዊ ሰነድ ያሟሉ መሆናቸውን የገለጹም ሲሆን፤ "ነገር ግን በወቅቱ የተለያዩ ግርግሮች በመፈጠራቸው ምክንያት ይህንን አጋጣሚ ተገን በማድረግ 'በሕገወጥ መንገድ ባለንብረት የሆኑ ግለሰቦች አሉ' ተብሎ እግዱ ተጥሎብናል" ብለዋል።
አክለውም ለጉዳያቸው መፍትሔ ፍለጋ ወደሚመለከታቸው ተቋማት ቢሄዱም፤ መፍትሔ ማግኘት እንዳልቻሉ ጠቁመዋል።በዚህም "ቤቶችን መሸጥ መለወጥ እንዳችል እንዲሁም ግብር እንዳንከፍል አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ታግደናል" ብለዋል።ለተጠቀሱት ችግሮች ባለፉት 4 ዓመታት እልባት እንዳልተሰጣቸው የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ በዚህም ምክንያት ለአላስፈላጊ ወጪ እና ለእንግልት መዳረጋቸውን አብራርተዋል።
አሐዱ የቅሬታ አቅራቢዎችን አቤቱታ በማድመጥ ምላሽ ለማግኘት በጉዳዩ ዙሪያ የከተማ አስተዳዳሩን አነጋግሯል።የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮምኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ እናትአለም መለሰ በሰሰጡት ምላሽ ከተማ አስተዳደሩ ከክፍለ ከተማ የሚመጡ ችግሮችን እልባት በመስጠት መልሶ ወደ ክፍለ ከተማ እንደሚልክ አንስተው፤ ጉዳዩን በዋናነት ክፍለ ከተማውን እንደሚመለከት ገልጸዋል፡፡
አሐዱም የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ሚጀናን አነጋግሯል። ሥራ አስኪያጁም በምላሻቸው ማህበራቱ እንደታገዱ አምነው፤ የኦዲት ችግር ያለባቸው በመኖራቸው የማጣራት ሥራው ብዙ ጊዜ እንደሚፈጅ ተናግረዋል።
አያይዘውም በሕገ-ወጥ መንገድ ሕጋዊነት ያላቸው የሚመስሉ የመሬት ይዞታ ማረጋገጫዎች የሚሰጡ ግለሰቦች በመኖራቸው ምክንያት የማጣራት ሥራው አጽንኦት ተሰጥቶት እየተሰራበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡አክለውም ከ900 በላይ ማህበራት በመኖራቸው ምክንያት የማጣራት ጊዜው መጓተቱን አስረድተው፤ "ምላሹን በቅርቡ ለመስጠት እየተሠራ ይገኛል" ሲሉ ገልጸዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎች እንደገለጹት በተለያዩ ጊዜያት ወደ ከተማ አስተዳደሩ እና ክፍለ ከተማ በሚሄዱበት ወቅት የሚሰጣቸው ምላሽ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ለችግሩ እልባት እንደሚሰጥ ነው።ነገር ግን ላለፉት 4 ዓመታት ምላሻ እንዳላገኙ አሳስበዋል።የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በተለያዩ ጊዜያት ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ አቤቱታዎችን ሲያሰሙ ይደመጣል።
Via Ahadu
@YeneTube @FikerAssefa