#ከገሊላ_ወደ_ዮርዳኖስ
የሔሮድስ ከተማ ገሊላ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድም የስብከትም አገሩ ናት።
ከገሊላ ነቢይ አይነሣም ዮሐ. 7፥52 የሚል አባባል በአይሁድ ዘንድ የተለመደ ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁድ በማያውቁት መንገድ በገሊላ መምህር ሆኖ ተነሣ።
ሔሮድስ አስጨንቆ ለሚገዛው ሕዝብ “በጨለማ የሚኖር ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ በሞት ጥላ አገር ለሚኖሩትም ታላቅ ብርሃን ወጣላቸው” ማቴ. 4፥16 የተባለው ቃል ሊፈጸምላቸው አይገባምን?
የአይሑድ ሊቃውንት በመሠዊያው አጠገብ ስለሚኖሩ የእግዚአብሔር ማዳን ቀድማ እንደምትደረግላቸው ያስቡ ነበር እንጅ እሱስ የማዳን ሥራውን የጀመረው በገሊላ ነበር። የማዳን ሥራውን ለሕዝቡ መስጠት የሚጀምረው ”መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” ብሎ ማስተማር በጀመረበት ጊዜ ነውና ይህንን የመንግሥተ ሰማያት ምሥጢር ማሰማት የሚጀምርባትን ገሊላ ዛሬ ግን ትቷት ወደ ዮርዳኖስ ምድረ በዳ እየሄደ ነው።
በዚያ ቦታ የቆየ ቃል አለውና ያንን ሊፈጽም ይጓዛል።
በኢያሱ ጊዜ በዮርዳኖስ ውኃ ዳር ድንቅ ነገርን እንደሚያደርግ ተናግሮ ነበር ኢያ. 3፥5
ያንን ድንቅ ነገር ሊያሳየን ዛሬ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ሄደ።
ኢያሱ “ሕያው አምላክ በመካከላችሁ እንዳለ....በዚህ ታውቃላችሁ” ብሎ ነበር።
ከልደቱ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችን ሲኖር በጉባኤ፣ በዐዋጅ ነጋሪ ቃል ተለይቶ አልታወቀልንም ነበር፤ ከዛሬ ጀምሮ ግን በመካከላችን የሚኖር እግዚአብሔር እሱ መሆኑን የሚያስረዱ ብዙ ምስክሮች ያሉን ስለሆነ አይተነዋል፤ እናውቀውማለን።
ዐዋጅ ነጋሪው ዮሐንስ “ከእኔ በፊት ነበረ ከእኔም በኋላ ይመጣል” ዮሐ. 1፥30 ብሎ ሲነግረን አብም በደመና ሆኖ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ የባሕርይ ልጁ መሆኑን ሲያስረዳን፣ መንፈስ ቅዱስም በራሱ ላይ ሆኖ ሲገለጥልን በእርግጥም ሕያው አምላክ በመካከላችን መሆኑን ወደ ዮርዳኖስ ብንወርድ ዛሬ እናውቃለን።
የተስፋይቱን ምድር ሊወርስ የተጠራው ሕዝብ እየመጣ ያለው በዚህ በኩል ነውና ኢየሱስ ክርስቶስ ሊቀበላቸው ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ወጣ።
አባቶቻችንን “በዮርዳኖስ ውስጥ ቁሙ” ብሎ በቀጠረበት ቦታ ለመገኘት ወደ ዮርዳኖስ ሄደ። በደረሰ ጊዜ “ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገርን ያደርጋልና ተቀደሱ” ኢያ. 3፥5 ብሎ ኢያሱ የቀጠራቸውን ሕዝቦች ቅዱስ ዮሐንስ “ለንስሐ የሚገባ ፍሬን አድርጉ” ማቴ. 3፥8 እያለ ለቅድስና የሚያበቃውን ትምህርት ሲያስተምራቸው አገኘው።
የኢያሱ ጉባኤ መምህሩ ተቀይሮ ትምህርቱ ተገልጦ አገኘው።
ኢያሱ “ተቀደሱ” ብቻ ብሏል እንጅ ምን ቢያደርጉ እንደሚቀደሱ አልነገራቸውም ነበር የቀረውን ትምህርት ደግሞ ዮሐንስ ገልጦ ንስሐ መሆኑን ነገራቸው።
የመቀደስ ዘመን ስላልደረሰ ሰውን የምትቀድስ የንስሐ ጥምቀትም በሰው ፊት ሳትገለጥ ቆይታ ነበርና ዮሐንስ ዛሬ ገለጣት።
አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዮርዳኖስ ሂዶ ከመላእክት ጉባኤ የተጨመረ እንዳይመስላችሁ፤ ቀራጮችና ጭፍሮች ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ ሊጠመቁ ወደ ተሰበሰቡበት ጉባኤ ገባ።
ሕያው ወደ ሙታን ጉባኤ በፈቃዱ ይገባልን? ጻድቁስ በኃጥአን መካከል ቢኖር መልካም ነውን? አወ በከተማ ካሉት ኃጢታቸውን አምነው ከማይናዘዙ ሙታን ይልቅ ኃጢአታቸውን አምነው የሚናዘዙ ኃጥአንን ይወዳልና እነሱ ወዳሉበት መጣ።
የጨረቃ በጨለማ መካከል መውጣት ለሰው ብርሃንን እንደሚሰጥ የክርስቶስም በኃጥአን መካከል መገኘቱ ለኃጥአን ተስፋን ይሰጣል።
ከዮሐንስ በቀር ማንም ሳያውቀው በዚህ ጉባኤ መካከል አደረ።
ቤተ ክርስቲያናችንም ዛሬ ታቦታቱን ከቤተ መቅደስ ይዛ በመውጣት የጌታችንን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ ያደረገውን ጉዞ ታስታውሳለች።
ገዳም ሲሄድ ተከትላው ገዳም የገባች ቤተ ክርስቲያን ወደ መጠመቂያው ስፍራ ሲገባም ተከትላው እንደምትገባ የታመነች መሆኗን ታሳያለች።
ኢያሱ ታቦቱን የተሸከሙ ካህናት በሰፈር ባለፉ ጊዜ ሕዝቡ እንዲከተል እንዳዘዘ ዛሬ ታቦታችንን ተከትለን እንወጣለን። ወደ መጠመቂያው ስፍራ ደርሰን በድንኳን በተቀመጥን ጊዜ ለመጠመቅ ተራውን ሲጠብቅ ያደረውን ክርስቶስን በዐይነ ሕሊናችን እንመለከተዋለን።
ክርስቲያኖች ሆይ! “ኑ ተከተሉኝ” ብሎ አብረነው እንድንጓዝ ሰለፈቀደልን የምናደርገው ጉዞ መሆኑን እያሰብን እንጓዝ።
ከቤተ መቅደስ ተነሥተን ጉዞ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ ከፊት ከፊታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እያየን ልንጓዝ ይገባናል እንጅ በሳቅና በጨዋታ በዘፈንና በእስክስታ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይገባናል።
እንኳን ኢየሱስ ክርስቶስን ተከትለን ይቅርና ኤልያስን የተከተለው ደቀ መዝሙር ዕጥፍ ድርብ ጸጋ የተቀበለው በዚህ አሁን ኢየሱስ ክርስቶስ በሄደበት መንገድ አይደለምን?
የእኛማ እንዴታ!
ጸጋ የምናገኝበት በዓል ያድርግልን፤
#ስምዐኮነ_መልአከ
#ይኽ_ትምህርት_ለሁሉም_የተዳረሰ_ይሆን_ዘንድ_ሼር_ላይክ_ኮመንት_እናድርገዉ_ቻናሉንም_ለብዙዎች_ተደራሽ_እያደረግን_የሚሰጡ_ትምህርቶችን_በማዳረስ_ሐዋርያዊ_አገልግሎት_እንስጥ!
አምኀ ተዋሕዶ ዘክርስቶስ በYoutube Sador Sisay on YoutubeSador Sisay on InstagramSador Sisay on FacebookSador Sisay on Tiktok#You_tube #Instagram #Facebook_pages subscribe እና share እያደረጋችሁ አገልግሎታችንን ተደራሽ በማድረግ አግዙ🙏🙏🙏