የደቡቧ ኮከብ ብርብር ማርያም= የኦሪትና የሀዲስ ኪዳን ማህተም
~~~~~~~
የደቡቧ የአጥቢያ ኮከብ በመባል የምትታወቀው ብርብር ደብረ ማርያም ገዳም የምትገኘው በጋሞ ዞን በምዕራብ ዓባያ ወረዳ ቦላ ሔራ ቀበሌ ልዩ ስሙ ደጋ ብርብር እየተባለ በሚጠራው ከፍተኛ ቦታ ላይ ነው፡፡
ደብረ ማርያም ብርብር ገዳም ቀደም ሲል በኦሪት ቤተ መቅደስ የተተከለችው ከጌታችንና መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ ልደት 400 ዓመት አካባቢ ነበር።
በሀገራችን ኢትዮጵያ መሥዋዕተ ኦሪት ከሚሰዋባቸው ትምህርተ ብሉይ ከሚሰጥባቸው አክሱም ጽዮን፣ ተድባብ ማርያም፣ መርጡለ ማርያምና ጣና ቂርቆስ አብያተ መቃድስ ጋር በኦሪቱ ሥርዓትና በምኩራብ በአይሁድ ደንብ ትተዳደር ነበር።
በዘመነ ሐዲስ በአምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ ደግሞ የቤተ መቅደስዋን የጥንት ታሪክና ዝና የሚያውቁት አጼ ገብረ መስቀል ብርብር በተባለችው ቤተ መቅደስ ሥርዓት ሐዲስ ዘመንን የሚመለከት ታቦት ገብቶ ሊወደስባትና ሊቀደስባት እንደሚገባ አስበው በታቦተ ማርያም ስም ቅዱስ ያሬድ እና ጻድቁ አቡነ አረጋዊን ታቦተ ማርያምን አስይዘው በአያሌ ሠራዊት ታጅበው ከአክሱም ጽዮን በብዙ ጉዞና ድካም ወደ ቦታው ደረሱ።
ግንቦት 21 ቀን ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ቤተ መቅደሱን በሜሮን አክብረው ታቦተ ማርያምን አስገብተው ቅዳሴ ቤቷን አከበሩ።
በዚህ መሠረት አገልግሎቷን ከኦሪት እስከ ሐዲስ ኪዳን ስትቀጥል የደቡብ ኢትዮጵያ የሃይማኖት ማዕከል
በመባል የምትገለጸው ጥንታዊቷ ደብረ ማርያም ብርብር ገዳም በየዘመኑ የቤተክርስቲያናችን ላይ የሚነሱ አጽራረ አብያተ _ ክርስቲያናት ታሪኳን ለማጥፋት ቢጥሩም በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ድንቅ ተዓምራትን በማድረግ ለዚህ ትውልድ ደርሳለች።
አናኒያንና አዛሪያን የሚባሉ ሊቃነ ካህናት ታቦተ ጽላቱን ከኢየሩሳሌም ቀይ ባህርን አሻግረው ከአክሱም ታቦተ ፅዮን ጋር እንዳመጧት ይነገራል፡፡
ብርብር ማርያም በምትባለው የታሪክ የእውነት የመመረጥ እና የበረከት ዶሴ ውስጥ በምኩራብ ስርዓት በዘመነ ኦሪት ከነበሩት ከሊቃ ካህኑ ሳዶቅ ልጅ ካህኑ አዛርያስ እስከ ጉባኤ ኒቂያ አዘጋጅ ከሆነው የንግስት እሌኒ ልጅ ንጉስ ቆስጢንጢኖስ ድረስ በድምቀት ጎልተው ይነበባሉ።
በኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ታሪክ የመጀመርያው ሊቀጻጳስ ከሆኑት ከአቡነ ከሳቴ ብርሃን (ፍሬምናጦስ ) እስከ ከሳቱ ቅዱሳን አካል ከሆኑት አቡነ አረጋዊ ድረስ በእዚህች ገዳም በረከት አፈስው ሱባኤ ይዘው ፀሎትና ቡራኪያቸውን አስቀምጠው ለትውልድ አልፈዋል።
የዜማው ሊቅ ስውሩ አባታችን ቅዱስ ያሬድ በመላእክት ጣዑመ ዜማ በሰማያውያን ለዛ በእዚህች ገዳም የምስጋና መሰዋት ዘርግቶ አልፎባታል።
በእዚህች ገዳምን ፃዲቁ አባታችን አቡነተክለሐይማኖት መንበረ አድርገዋት የወንጌል ዘርን በደቡብ ኢትዮጽያ ውስጥ ዘርተዋል።
ከኢዛና ሳይዛና እስከ አፄ ልብነድንግል፤ከአፄ ገብረመስቀል እስከ አፄ ዘርያዕቆብ ፤ ከአፄ ምኒልክ እስከ ጃንሆዬ ድረስ እጅ መንሻ እና መባ ለደቡቧ ኮከብ ለሆነችው ለብርብር ማርያም ሰጥተዋታል በረከት አፍሰውባታል።
በሀገር ላይ መከራ እና ወረራ ተከስቶ ጠላቶች በተነሱበት ጊዜ ከታቦተ ጽዮን እስከ ግማደ መስቀል በእዚህች ገዳም ሰንብተው ህዝቡን ባርከው ምድሯን ቀድሰው አልፈዋል።
እንግዲህ የእዚህች ገዳም ስም የደቡቧ ኮከብ ርዕሰ አድባራት ወገዳማት ሰማያዊት ጽዮን ብርብር ማርያም ትባላለች።
በህገ ኦሪት ከክርስቶስ ልደት 800 ዓመት በፊት በደብተረ ደንኳን በሊቀ ካህኑ ሳዶቅ ልጅ ካህኑ አዛርያስ ህገ እግዚአብሔር ተዘርግቶባታል።
በ1440 ዓ.ም አፄ ዘርዓ-ያዕቆብ ከትግራይ፣በ530 ዓ.ም አፄ ልብነ-ድንግል እንዲሁም በ1961 ዓ.ም ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ወደ ቤተ-ክርስቲያኗ በመምጣት መሳለማቸውና ድጋፍ እንዲሆን የሰጧቸው የተለያዩ ንዋዬ ቅድሳትን በገዳሟ ይገኛሉ።
የብርብር _ ማርያም ገዳም ከጋሞ ዞን ርዕሰ ከተማ አርባምንጭ 67 ኪ.ሜ ርቀት እንዲሁም ከምዕራብ አባያ ወረዳ ከተማ ብርብር 82 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች፡፡
ከተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች የሚጡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታይ ምዕመናን አዘውትረው ፀሎት የሚያደርሱበት ስፍራ ነው፡፡
ጥንታዊና ታሪካዊ የሆኑ በርካታ ንዋየ ቅድሳትና መንፈሳዊ ቅርሶች ያቀፈች ገዳም ናት።
በዚህች ገዳም በርካታ ሀገርንና ህዝብን ሊጠቅሙ የሚችሉ የባህልና የቅርስ ማስረጃዎች ይገኛሉ።
ይህንንም ከግምት በማስገባት የኢፌድሪ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን በሀገር ቅርስነት መዝግቦ በተለያዩ ጊዜያቶች እየተንከባከባትም ይገኛል።
የገዳሟ የቅርስ ይዘትን ስንመለከት ፦ በርካታ የብራና መፃህፍት፣ ከነገሥታት የተበረከቱ ጥንታዊ መፅሐፍት ፣ የቅዳሴ መስቀሎችና ሌሎች ቅርሶች ይገኛሉ።
የዚህችን ገዳም ታሪካዊነት ከሚያሳዩ የቁም ማስረጃዎች ዋና ዋናዎቹ ገዳሟ በአካባቢው የጋሞ ቤት አሰራር መሠረት የተሰራ ሲሆን የህንጻው ባህላዊ የቤት አሰራርም ጥበብ አሁን ላይ ይዘቱን እንደጠበቀ ይገኛል፡፡
የብርብር ማርያም ገዳም በአሁኑ ወቅት በጥሩ ሁኔታ ላይ ብትሆንም ቅርሶቹ የሚገኙበት ሁኔታ ካላት ውድ ዘመን ተሻጋሪ ሀብት አንጻር ለአደጋ የተጋለጠ በመሆኑ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ዘመናዊ ቤተ-መዘክር ሊገነባለት ይገባል።
አክሱም ጽዮንን ተሳልመው ይሆናል፤ጣና ቂርቆስን ረግጠው ሊሆን ይችላል፤ከተድባባ እና መርጦለማርያምንም በረከት ቢያፍሱም መልካም ነው።
ነገር ግን ብርብር ማርያም የምትባል አንድ ደቡቧዊር የህገ ኦሪትና ህገ ወንጌል ግምጃ ቤት በጋሞዎች መንደር አለች።
እሷ ትቀራችዋለች። ይሳለሟት፤ይርገጧት። በረከትና ቃልኪዷኗ ነፍስን አንጽቶ ስጋን የሚያከብር ነው።
@EotcLibilery @EotcLibilery @EotcLibilery