ዶናልድ ትራምፕ በቲክቶክ ላይ የተላለፈው ውሳኔ እንዲዘገይ ጠየቁ
++++++++
ተመራጩ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ቲክቶክ ለአሜሪካ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ነው በሚል እንዲሸጥ ካልሆነም እንዲዘጋ የተላለፈው ውሳኔ እንዲዘገይ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን መጠየቃቸው ተሰማ።
የአሜሪካ መንግስት የቲክቶክ እናት ኩባንያ የሆነውን ባይትዳንስ እስከ ፈረንጆቹ ጥር 19 ቀን 2025 ድረስ መተግበሪያውን እንዲሸጥ ካልሆነም እንዲዘጋ በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ ተላልፎበት ነበር።
ኩባንያው የአሜሪካ መንግስት ውሳኔ የመናገር ነጻነትን ይጥሳል በሚል እየተከራከረ እንደነበርም አይዘነጋም፡፡
በአሁኑ ወቅት በቲክቶክ መተግበሪያ ላይ 14 ሚሊየን ተከታይ ያፈሩት ትራምፕ ከዚህ ቀደም ቲክቶክ "ለሀገራችን ብሔራዊ ደህንነት ስጋት ነው" ቢሉም በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የወጣት አሜሪካዊያንን ድጋፍ እንዲያገኙ አግዟቸዋል ተብሏል።
መተግበሪያው ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት ሊኖረው እንደሚችል እንደሚያምኑ ነገር ግን ጉዳዩን ነጩ ቤተ መንግስት ከገቡ በኋላ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንደሚፈልጉለት ለፍርድ ቤት አመልክተዋል።
ከ170 ሚሊየን በላይ አሜሪካዊያን ቲክቶክን የሚጠቀሙ ሲሆን÷ መንግስታቸው መተግበሪያው የተጠቃሚዎችን መረጃ ለቻይና መንግስት አሳልፎ ይሰጣል ከሚል ክስ በተጨማሪ ኩባንያው የቻይና መንግስት የሚፈልገውን ይዘት በአሜሪካ እንዲያሰራጭ ያደርጋል በሚል እንዲዘጋ በፍርድ ቤት ተወስኖበታል።
በርካታ አሜሪካዊያን በሀገራቸው ካሉ የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች በተሻለ ቲክቶክ ለሚሰሯቸው የንግድ ስራዎች እያገዛቸው እንደሆነ መግለጻቸውን ዋሽንግተን ታይምስ ዘግቧል።
FMC
@zena_ethiopia24@zena_ethiopia24