የመጠበቄ መጠን ይሁን ሌላ ባላውቅም.............. ?
2013 ለኢትዮጵያ የወንዶች እግር ኳስ የትንሳኤ መስመር ይዞ የመጣ ነበር።የኮቪድ ወረርሺኝ በእርግማን ውስጥ ያለ ምርቃት ሆኖለት፤ የይዘት ለውጥ ባይኖረውም የውድድሩ መቼት መቀየሩና ቋሚ የቴሌቪዥን ስርጭት መኖሩ እግር ኳሳችንን ውብ መልክ ማልበስ ጀምሮ ወደዘንድሮ ሲያሻግረው ከብዙ ተስፋ ጋር ነው።
2014 ከአምና ጉድለት ተምሮ በጎነቱ ላይ ይበልጥ ጎልብቶ ይመጣል ደግሞ እኔን ጨምሮ የእግርኳሱ ቤተሰብ ጉጉት የወለደው እምነት ነበር።
ነ ገ ር ግ..........ን የሌሎቻችሁን ባላውቅም ሶስት የጨዋታ ሳምንታት ያሳለፈው አዲሱ የውድድር ዘመን ከጠበቅኩት ወርዶ ከመዘንኩት ቀልሎ አግኝቼዋለሁ። "በምን?" ያላችሁ ተከተሉኝ.......
1. የተጫዋቾች ስነምግባር
የሊጋችን የቴሌቪዥን ቋሚ ስርጭት የሚያመጣቸውን ትሩፋቶች አምና በጥቂቱም ቢሆን ታዝበናል። እንደ ብርቅ ከስንት አንድ ጊዜ ያውም ከአፍሪካ የማይሻገሩ ተጫዋቾች ስላለው የሚኮራ እግርኳስ፤ ከአንድ የውድድር ዘመን በኋላ ጥቂት የማይባሉ ተጫዋቾቹ ስማቸው ከአፍሪካ አልፎ አውሮፓ ከመሄድ ጋር ተያይዞለታል። ነገር ግን የጨዋታ ብቃት ብቻውን ትልቅ እና ተፈላጊ አያደርግም። ስነምግባር እና ተምሳሌት የሚሆን ጨዋነት መስፈርታቸው ብዙ የሆኑ መልማዮች ከሚያስቀምጧቸው ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ። በሶስቱ የጨዋታ መርሐግብሮች የተመለከትኩት ልቅነት ከአምና እና ካቻምናም ብሷል ስል በድፍረት ነው። ሜዳ ላይ ያሉ ተጫዋቾች ብቻ ሳይሆኑ ተጠባባቂ ወንበር ላይ የተቀመጡትም ጭምር የተግፃፅ ካርዶችን ለመመልከት ከልመና ያልተናነሰ አሳፋሪና ጋጠወጥ ባህሪያትን ሲያሳዩን ከማፈር ውጭ ምን ማድረግ ይቻላል? የሊጉን ህግ የሚያስከብረው አካል ለራሱና ለአገር ገፅታ፤ ከምንም በላይ ሲል የእግርኳስ ቀዳሚ መርህ የሆነውን ሰላማዊነትን ለማስከበር ሲል ልጓሙን ጠበቅ ቢያደርግ መልካም ነው።ተጫዋቾችም ጉብዝና አመለ ሸጋነትንም ያካትታልና ከእንደዚህ አይነት ጉብዝና አትጉደሉ.... አሸናፊ የሚያስብሏችሁ ክለቦቻችሁንም ይጎዳል። ይህንን ስል ግን ለጨዋነታቸው ከመቀመጫዬ ብድግ ብዬ እጅ የምነሳቸው እንዳሉ ሳልዘነጋ ነው።
2. ዳኝነት
እግርኳስ ተፈጥሯዊ ነው።ከነሚፈጠሩበት ስህተቶች ማማሩ ግልፅ ቢሆንም የእኛ እግርኳስ የሚያስተናግዳቸው ስህተቶች ከመብዛታቸው የተነሳ የትዝብት አቅም ላይ መዛል ያመጣሉ። ለአመታት የተጮኸበት እና የተጮኸለት የዳኝነት ችግራችን ቢብስበት እንጂ አልተሻለውም። በተለይ ደግሞ የመስመር ዳኝነት ችግራችን የተጫዋቾቻችንን ጥረት መና አስቀርቶ ክለቦችን የውጤት ዋጋ እያስከፈለ አምናን ተሻግሯል።ጨዋታዎችን የሚያስተላልፉት ኮሜንታተሮች ሙድ የሚይዙበት፤ ስለዳኝነት common knowledge ያላቸው ሰዎች እንኳን ያለመልሶ እይታ የሚፈርዷቸው "ቀላል" አጋጣሚዎች በስህተት ሚዛን የሚሰፈሩበት ሊጋችን፤ በዳኝነቱ ረገድ ከአምና ስህተቱ ሳይማር እና ሳያርም የ2014 ውድድር ዘመንን ጀምሯል።
የውድድሩ ባለቤት ከአዲሱ የውድድር ዘመን ጅምር አስቀድሞ የባለድርሻ አካላትን አቅም የሚያጎለብቱ ስልጠናዎች ሲሰጥ ዳኞችን መዘንጋቱ ያስተዛዝባል።በእግርኳስ ችሎት ፍትህን ከሚያሰፍኑ ዳኞች በላይ ስለእግርኳስ ሰላማዊነት ግድ የሚለው "ባለድርሻ" ያለው የኔዋ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው? አሁንም ፍርዱን ይህንን ረዥም ፅሁፍ ታግሰው ላነበቡልኝ ለእርስዎ ትቼዋለሁ።
ስለታዘዘብኳቸው በጎ ነገሮች ደግሞ በቀጣይ እመለሳለሁ።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም በክብር ትኑር !
በ Amanuel Akanaw የተፃፈ
@Bisrat_Sport_Fm @Bisrat_Sport_Fm