ፍቅር እንዳማረበት እንዲዘልቅ የሚያደርጉ 10 መንገዶች
#Share (ላገባም ላላገባም የሚሰራ ነው።)
__
የፍቅር ተፈጥሮአዊ አካሄድ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡ የፍቅር ግንኙነቱ ሲጀመር የነበረው ፍቅር በሂደት እየቀነሰ የነበረው እንዳልነበረ ሊሆን ሁሉ ይችላል፡፡ በመሰረቱ ካልታረመ፣ ካልተኮተኮተ፣ በጥቅሉ አስፈላጊው እንክብካቤ ካልተደረገለት ዝም ብሎ ማበቡን እና መልካም ፍሬ ማፍራቱን የሚቀጥል ምንም ነገር የለም፡፡ ያልተሰራበት ግንኙነት እጣ ፈንታው ደስታ አልባ መሆን ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ እጅግ በጣም ጥሩ የሚባሉ፣ ለብዙዎች ምሳሌ ሆነው የሚቀርቡ የፍቅር ግንኙነቶች እንኳን ፍፃሜያቸው የማታ ማታ መራራቅ አልፎ ተርፎም መለያየት ሊሆን ይችላል፡፡ ትልቁ የፍቅር ሕይወት ፈተና ሲጀመር የነበረው ፍቅር እንዳማረበት እንዲዘልቅ ማድረግ ነው፡፡
ምንም እንኳን ፍቅርን ለመመስረት ሁለት ሰዎች አስፈላጊ ቢሆኑም እንዲፀና እና ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ለማድረግ ግን አንድ ሰውም በቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ኃላፊነቱን ግን አስቀድሞ መውሰድ ይጠይቃል፡፡ የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ነው የሚያድረው፡፡ ክፍቱን የተተወ ቤት ውስጥ ብዙ ነገር ገብቶ ይወጣል፤ ብዙ ነገር እንዳልነበረ ይሆናል፡፡ ያለመጠባበቅ የቻልነውን ያህል ለማድረግ ጥረት ማድረግ አስፈላጊ የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ውጤቱ ላይ ትኩረት ማድረግ ጥሩ ነው፡፡ ዋናው ነገር ከእሷ ወይንም ደግሞ ከእሱ መምጣቱ ሳይሆን ዞሮ ዘሮ የሁለቱ የፍቅር ግንኙነት ጣፋጭ እና ፅኑ መሆኑ ነው፡፡ ፍቅራችሁ የሚፀናበት ይበልጥ የፈካ እና የደመቀ፣ ዘመናትን የተሻገረ መሆን የሚችለው ያለመጠባበቅ ኃላፊነት ወስዳችሁ መስራት ያለባችሁን መስራት ስትችሉ ነው፡፡ ምንም ተባለ ምንም አንድ ሰው ሁልጊዜም ኃላፊነቱን መወጣት መጀመር አለበት፡፡ በራሱ ሊንቀሳቀስ እና ሊለወጥ የሚችል ምንም ነገር የለም፡፡ የትዳር ግንኙነት ሲሆን ደግሞ ለማደስ ጥረት ካልተደረገ ወደ መፍረሱም ሊያቀና ይችላል፡፡
ቀጥሎ የትዳር ህጎች ከሚል መጽሐፍ ውስጥ ያገኘናቸውን 10 ፍቅር እንዳማረበት እንዲዘልቅ ያደርጋሉ የሚባሉ ህጎችን አለፍ አለፍ ብለን እናስቃኛችሁ፡፡ እነዚህ ተግባራት ላገቡ ብቻ ሳይሆን ላላገቡና በፍቅር ግንኙነት ላሉም የሚጠቅሙ ተግባራት ናቸው ፡፡
1✍ስሜትን የሚያነቃቁ ነገሮችን ማድረግ
መቼም አብሮ ሲኖር የሚያጋጭ፣ የሚያቀያይም፣ ቅሬታ የሚፈጥር ወዘተ ብዙ ነገር ይኖራል፡፡ ስሜት ይህንን ተከትሎ ይቀዘቅዛል፡፡ ፍቅር ስሜትም ነው በአንድ ጎኑ፡፡ በመሆኑም ስሜትን የሚያነቃቃ ደስታ የሚፈጥር ነገር ማድረግ የአድናቆት አስተያየት መስጠት ለአብነት ያህል አስፈላጊ ነው፡፡ ስራዬ ብላችሁ ማድነቅን ተለማመዱ፡፡ “ትላንት ማታ ጓደኛዬ ቤት በጣም ተጫዋች ሆነህ ነበር ያመሸኸው፤ ደስ ብሎኛል”፣ “አምሮብሻል” ወዘተ ዓይነት አድናቆት ሊሆን ይችላል፡፡ ከትችታችን ይልቅ አድናቆታችን በጣም መብለጥ ይኖርበታል፡፡
2✍ትችትን መቀነስና አድናቆት መጨመር
በአንፃሩ ትችት ትዳር ሲመሰረት አካባቢ አስፈላጊ ነው ይላሉ ብዙ ሰዎች፡፡ ጊዜ በነጎደ ቁጥር ግን ሰዎች ለትችት አለርጂክ መሆን ይጀምራሉ፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ትችትን መቀነስ አንድ አንድ ነገሮችን አይቶ እንዳላዩ ማለፍም ያስፈልጋል፡፡ መነገር አለበት የምንለው ነገር ካለም ከሁለት እና ሶስት አረፍተ ነገር ባልበለጠ እርዝማኔ መገልፅ ይመከራል፡፡ እርግጥ ነው ለትዳርና ፍቅር መጽናት አስፈላጊ የሆኑ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች ከሆኑ፤ ግንኝነቱን በማይጎዳ መልኩ መነጋገሩ አስፈላጊ ነው፤ ምክኒያቱም አለባብሰው ቢያርሱ በአፈር ይመለሱ እንዳይሆን፡፡ ስለዚህ ትችቱ ለፍቅር ግንኝነቱ ሲባል እንጂ እጸጽን ነቅሶ ለማውጣትና የእራስን ትክክለኝነት ለማጉላት መሆን የለበትም፡፡ ትችት በምንሰጥበት ጊዜ ከጥሩ ጀምረን መሀል ላይ ትችታችንን ገልጸን ከዛም በአድናቆት ወይም በበጎ ነገር መደምደም ይመከራል (ሳንድዊች እስታይል እንደሚባለው)፡፡
3✍አዳማጭ ሁኑ
ማደመጥ ለፍቅረኛችን ወይንም ለትዳር አጋራችን የምንሰጠው ትልቁ ስጦታ ነው፡፡ ትርጉም መስጠታችሁን፣ ተሳሳተ የምትሉትን መረጃ ማስተካከላችሁን ጥላችሁ በሙሉ ልባችሁ ማዳመጥ ጠቃሚ ነው፡፡
4✍ራሳችሁ ላይ ትኩረት አድርጉ
ለራሳችሁ፣ ጓደኞቻችሁ፣ ቤተሰባችሁ ወዘተ ከትዳራችሁ በተጨማሪ ጊዜ መስጠት ጥሩ ነው፡፡ የግላችሁ ጊዜ ማሳለፊያ ልምድ ይኑራችሁ፡፡ በራሳችሁ እና በራሳችሁ ጉዳይ ላይ ምንም ትኩረት የማታደርጉ ይልቁንም ሙሉ ትኩረታችሁ የትዳር አጋራችሁ ላይ ከሆነ ተቺዎች ወይንም ደግሞ ጭንቀታሞች ትሆናላችሁ፡፡ እያንዳንዷን እዚህ ግባም የማትባል ጉዳይ እያነሳችሁ ስትጥሉ አሰልቺ እና አፋኝ ዓይነት ግንኙነት እንዲኖራችሁ ታደርጋላችሁ፡፡
5✍ይቅርታ ጠይቁ
ምንም እንኳን ለተፈጠረው ችግር የእናንተ እጅ ድርሻ ትንሽ እንደሆነ ብታስቡም “እኔ ይኼ ችግር እንዲፈጠር ለተጫወትኩት ሚና ይቅርታ ይደረግልኝ” ማለትን ተለማመዱ፡፡
6✍ይቅርታ ካልተጠየኩኝ ሞቼ እገኛለሁ አትበሉ
አንድ አንድ ጊዜ ይቅርታ ሳይጠይቁ ሰዎች መተዋቸውን፣ ለውጥ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው በተለያየ መንገድ ሊገልፁ ይችላሉ፡፡ይቅርታ ካልተጠየኩ ሞቼ እገኛለሁ ማለት ግን አላስፈላጊ ተደራራቢ ችግር ይፈጥራል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ተፈላጊው ለውጥ መምጣቱ ነው፡፡
7✍ዘወትር ፈላጊዎች አትሁኑ
በስሜት የራቀ የሚመስል ሰው ጫና ሲደረግበት ይበልጥ ይርቃል፡፡ መተንፈሻ አየር መስጠት፣ ራስ ላይ ትኩረት ማድረግ በአንፃሩ የራቀንም ያቀርባል፡፡ የት ወጣች የት ገባች ውጤታማ አይደለም፡፡
8✍ሀሳባችሁን አጭር እና ለስላስ በሆነ መንገድ ግለፁ
ደጅ ደጁን የሚል ሰው አንድ አንድ ጊዜ ህመም የሚፍጥረበትን የቃላት ልውውጥ ሽሽት ውስጥ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ሀሳብን አጠር አድርጎ፣ በተለሳለሰ መንገድ መግለፅ ጥሩ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ድምፅንም ጭምር ዝቅ አድርጎ መናገር ተገቢ ነው፡፡ ከጣራ በላይ ድምፅን ከፍ አድርጎ መናገር ቁጣ ይመስላል፤ ከሆነም በዛ መልኩ መግለፁ አስፈላጊ አይደለም፤ ከመፍትሄነት ይልቅ የባሰ ችግር ፈጣሪነቱ ይጎላል፡፡
9✍ሁሉን መስዋዕት አታድርጉ
ተለዋወጭ ሰው መሆን አስፈላጊ ባይሆንም ሁሉንም ነገር ለእርስ በእርስ ግንኙነቱ ሲባል መስዋዕት ማድረግ ግን አይመከርም፡፡ ጫና እየተደረገባችሁ ሁሉንም እምነታችሁን፣ ምርጫችሁን እና መንገዳችሁን ገደል አትክተቱ፡፡
10✍በመጠኑም ቢሆን ሁለታችሁም የግልጊዜ ይኑራችሁ
ሰዎች በባህሪያቸው የሚሳቡት ከእርስ በእርስ ግንኙነቱ ውጪ ሌሎች ተጨማሪ የሚወዳቸው የራሱ ነገሮች ወዳሉት ሰው ነው፡፡ የመጽሐፍት ክበብ፣ በጎ ፍቃድ፣ ዋና ወዘተ ሊሆን ይችላል ባላችሁ ትርፍ ጊዜያችሁ መሞከሩ ይመከራል፡፡ ለብቻችሁ የሚኖራችሁ ጊዜ በጋራ ለሚኖራችሁ ጥሩ ቆይታ አስተዋፅዖ ያደርጋል፡፡ሁሌ አብሮ መሆን መዛዛግና መሰለቻቸት ሊፈጥር ይችላል ፡፡
በነጋሽ አበበ
የስብዕና ልህቀት
@Human_Intelligence