የማስተካከል ድንቅ ጥበብ
በመጀመሪያ ለሕይወታችን እቅድ እንሰራለታለን፡፡ አንደኛ እቅድ ትምህርት፣ ስራ፣ የፍቅር ሕይወት፣ ቤተሰብ እያልን እናድጋለን፡፡ ከዚያም ወደ ሕይወት ግቦቻችን እንደርሳለን። በእርግጥ እንደዚያ እንደማይሰራ እንደምታውቅ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ሕይወታችን ማባሪያ በሌለው ብጥብጥና ግርግር ውስጥ ታልፋለች፡፡ የሕይወታችን አብዛኛውን ጊዜያችንን የምናጠፋውም ባላየናቸው የሕይወት ውጣ ውረዶች የሚመጡብንን ፈተናዎች በመታገል ነው፡፡
በህይወት ውስጥ ወሳኙ ነገር መነሻው ሳይሆን ከመነሻው በኋላ የሚመጡት የማስተካከያ ጥበቦች መሆናቸውን ተምሬያለሁ። ከብዙ ቢሊዮን ዓመታት በኋላ ተፈጥሮም ይህን - የተማረች ትመስላለች። ህዋሳት በተከፈሉ ቁጥር የመቅዳት ሂደት ስህተቶች (copying errors) ቀጣይነት ባለው መልኩ በዘረመላዊ ቁሶች ውስጥ እየተፈጠሩ ይሄዳሉ፡፡ ስለሆነም በእያንዳንዱ ህዋስ ውስጥ እነዚህን ስህተቶች ወደኋላ ተመልሰው የሚያስተካክሉ ሞለኪዮሎች አሉ። የዲ ኤን ኤ ጥገና ባይኖር ኖሮ ልክ እንደተወለድን በሰዓታት ውስጥ በካንሰር አማካይነት መሞታችን አይቀርም ነበር፡፡ የበሽታ መቋቋም ሥርዓታችን የሚሰራውም በተመሳሳይ መልኩ ነው። ችግሮች ቀድመው የማይታዩ በመሆናቸው ምክንያት ቀድሞ የተዘጋጀ ማስተር ፕላን የለም፡፡ ቫይረሶችና ባክቴሪያዎች በየጊዜው እየመጡ ሰውነታችንን ያጠቃሉ። የመከላከል ሥርዓታችንም ሁልጊዜ ይሄንን በማስተካከል ይሰራል።
ስለዚህ ወደፊት ሁለት በጣም የማይጣጣሙ ጥንዶች መካከል የሰመረ ትዳር መመስረቱን ስትሰማ ብዙ አትደነቅ፡፡ ይህ የስሪትን (set up) አጋኖ የማየት አይነተኛ ምሳሌ ነው፡፡ በግልጽ ካወራን የትኛውም ሰው ለትንሽ ሰዓት በግንኙነት ውስጥ ከቆየ ያለማስተካከያና ያለማሻሻያ ግንኙነቱ መቀጠል የማይችል መሆኑን ይረዳል። የትኞቹም ጓደኝነቶች ማደግ አለባቸው፡፡
ብዙውን ጊዜ ከማያቸው የተሳሳቱ አረዳዶች መካከል አንዱ ‹ጥሩ ሕይወት ማለት የተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ መኖር ማለት ነው› የሚለው ድምዳሜ ነው፡፡ ይህ ስህተት ነው፡፡ ጥሩ ሕይወት . የሚመጣው ቀጣይነት ባላቸው የዘወትር ማሻሻያዎች ውስጥ በማለፍ ነው፡፡
እና እኛ ለማስተካከልና ለመሻሻል የምናቅማማው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እያንዳንዷን የማስተካከያ ስራ የምንረዳት በመስመራችን ላይ እንደተገኘ ድክመት ስለሆነ ነው፡፡ በእርግጠኝነት እቅዳችን እየሰራ አለመሆኑን እንናገራለን፡፡ በዚህም የውርደት ስሜት ይሰማናል፡፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ እቅድ እንደወረደ ሰርቶ አያውቅም፡፡ ድንገት ያለምንም እንከን ሰርቶ የሚያውቅ ከሆነም እንኳን ሁኔታው ፍፁም አጋጣሚ ነው፡፡
ታዋቂው የአሜሪካ ጀኔራልና በኋላም ፕሬዝደንት) ዋይት ኤዘንሃወር እንዳለው “እቅዶች ምንም አይደሉም፧ ማቀድ ግን ሁሉ ነገር ነው፡፡” ነገሩ ወጥ የሆነ ፅኑ እቅድ ስለመያዝ አይደለም፤ በተደጋጋሚ እና ሁልጊዜ የሚኖር የማቀድና የማሻሻል ሂደት እንጂ።
“ወታደሮችህ ልክ የጠላትን ጦር ሲያገኙ” ይላል ኤዘንሃወር “የትኛውም እቅድ ጥቅም አልባ ይሆናል፡፡
ህገ መንግስታት ሁሉም ህጎች የሚያርፉባቸውን መሰረቶች የሚጥሉ የበላይ ሰነዶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉም ህገ መንግስታት በመሻሻል ሂደት ውስጥ ያልፋሉ። ለምሳሌ በ1787 የፀደቀው የአሜሪካ ህገ መንግስት እስካሁን ባለው ዘመኑ 27 ጊዜ ተሻሽሏል። የስዊዘርላንድ ህገ መንግስትም ከ1848 በኋላ ሁለት ትልልቅ ማሻሻያዎችን (revisions) እና በርካታ ጥቃቅን ማስተካከያዎችን አስተናግዷል፡፡ የጀርመኑ የ1949 ህገ መንግስት በበኩሉ 60 ያህል ማሻሻያዎች አይቷል፡፡
ይህ ውርደት ወይም ድክመት አይደለም፡፡ ትርጉም የሚሰጥ ሂደት እንጂ። የማስተካከል አቅም የየትኛውም
ዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ መሰረት ነው፡፡ ዴሞክራሲ የሚገነባው በማስተካከያ ስርዓቶች ውስጥ ነው፡፡ በወጉ የሚስራው ብቸኛው የመንግስት አይነትም ይሄ ነው፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ በሌሎች ሁኔታዎች ላይ ያላን የማስተካከል ፍላጎት ደግሞ ዝቅ ያለ ነው፡፡ የትምህርት ስርዓታችንን
መጥቀስ ይቻላል። የትምህርት ስርዓታችን በእውነታ እውቀት እና በሰርተፍኬት (ስሪት) ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ በዲግሪ እና በስራ ቦታ ውጤታማነት መካከል ያለው ክፍተት ግን ብዙ ነው። ይሄንን እያስተካከልን አይደለም፡፡
በባህሪ እድገታችንም ውስጥ ተመሳሳይ ነገር አለ፡፡ አንድ ብልህና አስተዋይ የምትለው ሰው እንደሚኖርህ እርግጠኛ ነኝ፡፡ የዚህ ሰው አስተዋይ መሆን ዋና ምክንያቱ ምን ይመስልሃል? ስሪቱ? .
(ትክክለኛ ዘር፣ ጥሩ አስተዳደግ፣ ጥራት ያለው ትምህርት) ወይስ የማስተካከል ልምዱ? (በሕይወቱ የሚያያቸውን ክፍተቶችን በየጊዜው እያስተካከለ የመሄድ ችሎታው?)
ሲጠቃለል; ለማስተካከል ያለንን መጥፎ አተያይ ማስወገድ አለብን። ትክክለኛውን - ህግ እንከተላለን ብለው እየታገሉ እድሜያቸውን ከሚያቃጥሉ ሰዎች ይልቅ በጊዜ ራሳቸውን ማስተካከል የጀመሩ ሰዎች የበለጠ ተጠቃሚ ናቸው። ፍፁም የሚባል ልምምድ እና ህግ የለም። የሕይወት ግቦችም ከአንድ በላይ ናቸው። ፍፁም የቢዝነስ ስትራቴጂ የሚባል ነገርም የለም። ትክክለኛ የሚባል አንድ ስራ ብቻም እንዲሁ።
ሁሉም ተረቶች ናቸው። እውነታው ይሄ ነው። በአንድ እርምጃ ትጀምራለህ፤ በየደረጃው እያስተካከልክ ትጓዛለህ፡፡ አለም የበለጠ ውስብስብ እየሆነች በሄደች ቁጥር መነሻ ነጥብህ ጠቃሚነቱን እያጣ ይሄዳል። ስለዚህ “በፍፁም ስሪትህ” ላይ ኃይልህን አታባክን፤ በስራም ቢሆን፣ በግል ሕይወትም ቢሆን፡፡ ከዚያ ይልቅ በአግባቡ እየሰሩ ያልሆኑ ነገሮችን ማስተካከልን ተማር፤ ተለማመድ። ይህንንም በፍጥነት እና ያለ ምንም የጥፋተኝነት ስሜት አድርገው፡፡
✍️ሮልፍ ዶብሊ
📚The art of clearly thinking
#share
@Human_intelligence