ሸይኽ ኢብራሂም አልሙሐይሚድ እና ሰሞንኛው ግርግር
~
ሸይኽ ኢብራሂም አልሙሐይሚድ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሃገራት በመዘዋወር በየገጠሩ በመግባት ደዕዋ በማድረግ፣ አቅመ ደካማ ሙስሊሞችን በመርዳት፣ መስጂዶችን በመገንባት የሚታወቁ ሸይኽ ናቸው። ሸይኽ ኢብራሂም ሰሞኑን ቂም ባረገዙ አካላት እየተብጠለጠሉ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ በኢኽዋንና በኸ -ዋሪጅ ቡድን ቀድሞ የተያዘው ቂም በመኖሩ ነው። ያሁኑ መነሻ ሰበብ ብቻ ነው። ሸይኹ በሁለቱ አንጃዎች ላይ በጣም ከባድ ናቸው። በዚህ ዘመን በጂሃድ ስም የሚፈፀመውን የኸዋ -ሪጅ እንቅስቃሴ እርቃን ያስቀሩባቸው ኪታቦቻቸው ለዚህ ምስክር ናቸው።
ሰሞኑን ከሸይኽ ሳሊም አጦዊል ጋር ተገናኝተው ባስተማሩበት መድረክ ላይ ለቀረበላቸው አንድ ጥያቄ ምላሽ የሰጡበትን ቆርጠው በማቅረብ እያብጠለጠሏቸው ነው። በዚህ ውንጀላ ከታዋቂ ሰዎች እስከ ተራ ሰዎች ተካፍለውበታል። "የውመል ቂያማህ ስለሽንት ትጠየቃለህ። ሽንት ነጃሳ ስለመሆኑ፣ ነጃሳው ቢነካህ ስለማጽዳትህ ትጠየቃለህ። ስለፈለስጢን ግን አላህ በፍጹም አይጠይቅህም እያሉ ደዕዋ ያደርጋሉ" እያሉ በቡድንተኝነት ፈርጀዋቸዋል።
እነዚህ አካላት ራሳቸው በቡድንተኝነት የተለከፉ ናቸው። ለውንጀላ ያላቸው ጥማትም ነው ንግግር እየቆረጡ ያለ አውዱ እስከመተርጎም ያደረሳቸው። የሆነ ዓሊም "የጦሀራ ርዕስ በፊቅህ ኪታቦች መጀመሪያ ላይ እየተደረገ፣ የጂሃድ ርእስ መጨረሻ ላይ የሚደረገው ለምንድነው?" ተብሎ ሲጠየቅ ጦሀራ አስተካክሎ የማያደርገው ሁሉ እየተነሳ ስለ ጂሃድ እንዳይናገር ነው አለ። ዛሬም እያየን ያለነው ተጨባጭ ይህንኑ ነው። ይሄ ነው የሚባል ግንዛቤ የሌለው ጥራዝ ነጠቅ ሁሉ እየተነሳ ከሚዲያ በለቃቀመው እንቶ ፈንቶ ላይ ተመርኩዞ የሱና ዑለማኦችን ይዘረጥጣል። መሰረታዊ የዐቂዳ ጉዳይ ላይ የረባ ግንዛቤም ጥረትም የለውም። እንደ አሕ.ባሽ፣ ኢኽዋን፣ ተብሊግ፣ ተክ.ፊር፣ ሺ0 ያሉ አጥማሚ አንጃዎችን ጥሎ ሁሌ በሱና እንቅስቃሴ ላይ ነጥሎ አቃቂር በማውጣት ላይ የተጠመደበት ምክንያት ቢያንስ ከከፊሎቹ ጋር የሚጋራው በሽታ ስላለው ነው።
ሸይኽ ኢብራሂም "የጦሀራ እና ከሽንት የመጥራራትን ህግጋትን ካልተማርክ ቀብርህ ውስጥ ትቀጣለህ። ፈለስጢን ውስጥ የተከሰተውን ባታውቅ ግን አትቀጣም" ብለዋል። ጥያቄው ምን ነበር? በፍልስጤም ጉዳይ ቀድሞ በተከሰቱ ነገሮች ሳይማር አሁንም መስመር ስለለቀቀ ሰው ምን ትላላችሁ የሚል ነው። ንግግራቸው ዘለግ ያለ ነው። የጠላትን ዝርዝር ሴራ ማወቅ በጥያቄው የተጠቀሱ አይነት ሰዎች ላይ ግዴታ እንዳልሆነ ነው ያወሱት።
በዚህ ንግግር ውስጥ ምንድነው ስህተቱ? በስርአት ከሽንት የማይጥራራ ሰው በቀብር እንደሚቀጣ ግልፅ ሐዲሥ የመጣበት ጉዳይ ነው። ይሄ እያንዳንዱን ሙስሊም የሚመለከት ግዴታ ነው። የጠላትን ሴራ ማወቅስ በሁሉም ሙስሊም ላይ የነፍስ ወከፍ ግዴታ ነው ወይ? በስሜት ከመጮህ ውጭ ማንም በዚህ ላይ መረጃ ማምጣት አይችልም። በፍልስጤምም ይሁን በሌሎች ሙስሊሞች ላይ ስለሚደርሰውና ስለ ጠላት ዝርዝር ሴራ በነፍስ ወከፍ ደረጃ ሳይሆን ከሙስሊሞች ውስጥ ጉዳዩ በሚመለከታቸው ላይ ብቻ ነው ግዴታ የሚሆነው። ስለ መሰረታዊ የተክሊፍ ህግጋት የሚያውቅ ሰው ይሄ አይሰወረውም። የፖለቲካ ጉዳይ የሁሉም ሙስሊም ግዴታ እንዳልሆነ ሲበዛ ግልፅ ነው። "አይ በሁሉም ላይ ግዴታ ነው" የሚል ካለ የድፍን ዓለም ሙስሊሞችን ወንጀለኛ እያደረገ ነው። ማንም ስለሁሉም ሊያውቅ አይችልምና።
አንድ ሰው በሆነ የዓለም ክፍል ሙስሊሞች ላይ የሚደርሰውን ባለማወቁ ይቀጣል የሚል ካለ በድፍን ዓለም ሙስሊሞች ላይ እየደረሱ ያሉ በደሎችን ሁሉ ማወቅ ዋጂብ ነው እያለ ነው። ይሄ ከየት የመጣ ሙግት ነው? በቻይና የኢጉር ሙስሊሞች ላይ፣ በኢራን ሱኒዮች ላይ፣ ጋዛ ውስጥ በሐማስ ስለተጨፈጨፉ ሙስሊሞች፣ ወዘተ ምን ያህል ሰው ያውቃል? ይህንን ያላወቀ ሁሉ በቀብር ውስጥ ይቀጣል ልትሉ ነው? በኛ ሃገር ሙስሊሞች ላይ ስለሚደርሱ በደሎች የሌሎች ሃገራት ሙስሊሞች፣ ዑለማኦች ጭምር የሚያውቁ ቢኖሩ ከጥቂትም ያነሱ ናቸው። ይህንን ስላላወቁ ወንጀለኞች ናቸው ልትሉ ነው?
የነዚህ አካላት ተንኮል ግልፅ ነው። ፍላጎታቸው ሸይኽ ኢብራሂም የሙስሊሞችን ደም ጉዳይ ከጦሀራ ጉዳይ በታች አድርገው አራክሰዋል ለማለት ነው። ንግግራቸውን ቆርጠው ያቀረቡትም ሆነ ብለው እንዲህ አይነት ይዘት እንዲይዝ ነው። ሆነ ብለው ሙስሊሞችን ከመርዳት ግዴታ ጋር በማያያዝ ሸይኹ መርዳት አያስፈልግም እንዳሉ አድርገው እያቀረቡ ነው። ሙስሊሞችን መርዳት ዋጂብ ነው። ግን በማን ላይ? በሚችል ላይ እንጂ በእያንዳንዱ ሙስሊም ላይ አይደለም። እነዚህ ከሳሾች ራሳቸው ለፍልስጤም ሙስሊሞች ያደረጉት እርዳታ የለምኮ። እያደረጉ ያሉት በደማቸው መቆመር ነው። እንጂ ሸይኽ ኢብራሂም ሙስሊሞችን መርዳት አያስፈልግም አላሉም። ሙስሊሞችን ለመርዳትኮ ነው በሃገራችን በጉራጌ፣ እስከ ሞያሌ ጫፍ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ ወሎ፣ ዐፋር ጨምሮ በብዙ የአፍሪካ ሃገራት የሚንከራተቱት። እንዲያውም እዚያው ምላሽ ላይ ኢስላምን በንግግርም ቢሆን እርዳ ብለዋል። እንዲያውም እዚያው ቦታ ላይ በፍልስጤም ሙስሊሞች ላይ በሚደርሰው የሚደሰት ካለ ኢማኑን ይፈትሽ ብለዋል።
ምናልባት በሌላ ተያያዥ ነጥብ ልመለስ እችላለሁ፣ ኢንሻአላህ።
=
የቴሌግራም ቻናል፡-
https://t.me/IbnuMunewor