✨✨ፍቅር ቅብ-18✨✨
ከክሊኒኩ እንደወጣሁ ቅርብ ያለ ቤተክርስትያን ጠይቄ ላመሰግን ሄድኩ.........ከተወሰኑ ቀናት በፊት "እዚህ አካባቢ መቃብር ስፍራ ካለ ጠቁሙኝ" ያልኩ ሴትዮ ዛሬ "ቤተክርስትያን ጠቁሙኝ" እያልኩ ነው....
ጊዜ እንዲህ ነው...."የማይነጋ ለሊት ማያልፍ ቀን የለም....." የሚል የመዝሙር ስንኝ አቃጨለብኝ...."እውነትም" አልኩኝ በለሆሳስ.....ይሆናል ብለው ከነገሩን በላይ ሆኖ ስናየው እናምናለን.....እኛ እንደሀገርም ሆነ እንደ ህዝብ....እንደ አህጉርም ቢሆን እንደ አለም የሚያመሳስለን ነገር አለ.....እንደ ቶማስ ካላየን አናምንም....እንደ ኤሳው ሆዳችን ከብኩርናችን ይበልጥብናል....ፈጣሪ የሰጠንን ፀጋ ከላያችን ለመላጨት ደሊላ ትበቃናለች.....
የኢዮብን ስም የያዝን ከጂዎች.....የስምኦንን ስም የያዝን አሳቾች....የአብርሀምን ስም የያዝን ንፉጎች....የኢያሱን ስም ይዘን ለአምላካችን ግድ የሌለን ከንቱዎች ሆነናል....ሙሴ ተብሎ አሻጋሪ ጠፍቷል.....የዘመኑ ሙሴ ላሻግራችሁ ብሎ ባህር ከፋይ....ህዝብ አምኖ ከክፋዩ ውሀ መሀል ሲገባ ውሀ የሚያስበላ ነው.....
የዘመኑ ስምኦን እንደ "ስምኦን ጫማ ሰፊው" ሰው አሳትኩኝ ብሎ አይኑ ላይ ወስፌ አይሰድም....ይልቁንም ሰው ለማሳት ጫማው እስኪያልቅ ይኳትናል እንጂ...
ስማችን አይከብደንም.....ምግባራችን አንገት አያስደፋንም.....ደህና ነገር እንደሰራ ሰው እንታበያለን.....እንዳልከፋን እንስቃለን....እንዳለለት እንዘላለን.....መፍራት ያለብንን አንፈራም....መፀየፍ ካለብን ጋር እንጣበቃለን.....ስጋችንን እናምነዋለን....ስጋ ብቻ እንዳለው ሰው እንኖራለን.....
***
"ዛሬ ምሳ የምጋብዝሽ እኔ ነኝ" አልኳት ሀኒን ....የሆነ የማላውቀው መንፈስ ውስጤ አለ አምጫት አምጫት የሚለኝ....ደስታሽ ደስታዋ ነው ንገሪያት የሚለኝ.....ለምን ብቻሽን እሷ እያለችልሽ የሚለኝ መንፈስ ሲታገለኝ ነበር የደወለችልኝ....እግዜር ይስጣት።
ከተገናኘን ወር ሊያልፈን ነበር.....ለአመታት እንዳልተገናኘ ዘመድ ተቃቀፍን.....ደስ አለኝ።
የምንወደውን ምግብ አዘን ሳንጎራረስ እና ሳንተያይ በላን.....እዚህ ጋር ከመክብብ ጋር ስለነበረን የመጀመሪያ ቀን አስታወስኩ.....ትንሽ ትንሽ መደበር እንደጀመርኩ አስተውላ "ምነው.....?" አለቺኝ
"ኧረ ምንም...."....አልኩና ለምን እንደዘጋችኝ ጠየቅኳት....
"አንቺም ዘግተሽኛል እኮ....".....የሚል የሰነፍ መልስ መለሰችልኝ....
"ያንቺን አይደል የጠየቅኩሽ ለምን አትመልሺም".....አልኳት።
"ልጠላሽ አልፈለግኩም.....ትንሽ ትግል ውስጥ ነበርኩ....".....አለችኝ ድምጿ ቀዝቅዞ።
ትንሽ አርፋ ቀጠለች...."ትግል ውስጥ ነበርኩ....እየታገልኩ ነበር.....እኔ በፈለግኩት እና የፈለግኩት በሚፈልገው መሀል ያለውን ልዩነት ላጠብ ስጣጣር ነበር...አንቺን ከመክብብ ጭንቅላት ለማስወጣት እየታገልኩ ነበር...."......አለችና በልምምጥ አይነት አየችኝ......
"ተይልኝ ልልሽ አይደለም.....ምን ብለሽው እንዲህ እንደሆነልሽ ብቻ ንገሪኝ.....እኔ ለሰባት አመት የእሱን ትኩረት ለማግኘት የተጋጋጥኩትን በአንድ ቀን እንዴት ከመሬት ቀላቀልሽው.....እንዴት አርገሽ ብታይው ነው.....አሳሳቅሽ እንዴት ነበር.....ፀጉርሽን አንጨባረሺው ነበር አይደል....የዛን እለት የለበስሽው ልብስ መናኛ ነበር አይደል.....እንዴት ያለ አስተያየት እንዴት ያለ አወራር ነበረሽ.....?.....ወይስ አበላልሽ ነው....አስታውሳለሁ አካሄድሽ እስከዚም ነበር.....ጫማሽ አቧራ ጠጥቶ ነበር.....ትዝ አለሽ ቀሚስሽ ጭቃ ነክቶት ነበር.....".......አለችኝ እና ያለቀው ትሪ ላይ አፈጠጠች.....
አንጀቴ ተላወሰ......"ሀኒ ካንቺ አይበልጥም.....የምሬን ነው.....ይኧውልሽማ....."......ከማለቴ አቋረጠችኝ......እውነቱን ለመናገር "ካንቺ አይበልጥም" ያልኩትን ቃል ስሜታዊነቴ ነው ያበጃጀው.....አንዳንዴ የማናወዳድራቸው ነገሮች አሉ.....እንደ እኔ እንደ እኔ ደረጃ ከመስጠት ሁሉንም እንደ ራሱ መውደድ ይሻላል።
"እንደስምሽ ነሽ ታውቂያለሽ.....እድል አለሽ.....ምን አልባት ፈጣሪ በእሱ ሊክስሽ ይሆናል......"
"የሚክሰው በዳይ ነው.....ሰው እንጂ ፈጣሪ በድሎኝ አያውቅም.....ሀኒ....".......በድጋሚ አቋረጠችኝ.....
"ትናንት መክብብ እንዴት አድርጎ የፍቅር ጥያቄ እንደሚያቀርብልሽ ሲጨነቅ ነው ያመሸው.....ምን ትወድ ይሆን እያለ ልቤን ሲጠባ ነበር.....የምትወጂውን ሳይሆን የምወደውን ልነግረው ስንቴ ከአፌ እንደመለስኩት አታውቂም.....ስንት ጊዜ እድል ፊት እንዳለህ እያሰብክ "አፈቅርሻለሁ" በል እንዳልኩት እና በልቤ ጮክ ብዬ "እኔም አፈቅርሀለሁ" እንዳልኩት አታውቂም.....አንቺን እያሰበ ስንት ጊዜ አፈቅርሻለሁ ሲለኝ እንዳመሸ አታውቂም.....አእምሮዬ ሊፈነዳ አንድ ሀሙስ እንደቀረው አታውቂም....."......አለችና መንታ መንታ እምባ ከአይኖችዋ ተንቆሮቆሩ።
በወደድኩት በመወደዴ ደስ ባለኝ ቅፅበት እንባዋ እንደ እሳት ፈጀኝ.....ልቡ ውስጥ ለመግባት በተመኘሁት እኩል መውጣት አሰኘኝ.....አሳዘነችኝ.....
"ትዝ ይልሻል ልጅ እያለን ያየነው ሻሩክ የሚሰራበት የህንድ ፊልም......"
በህይወት ዘመኔ ያየሁት የህንድ ፊልም እሱ ብቻ ስለነበር አልረሳሁትም.....አንገቴን በአዎንታ ነቀነቅኩላት.....
"እሱ ላይ እንዳለችው እንስት ሳሳሁ.....'ለአንድ ወንድ ምነው እንደዚህ' እንዳላልኩ ለአንድ አሱ ቆዳዬ ሳሳ....".....ከቦርሳዋ ሶፍት አውጥታ አይኗን አደራረቀች።
"ሀኒ......".....አልኳት ጠረጴዛ ላይ ያዳደመችውን ያልበላችበትን እጇን ባልበላሁበት እጄ ጨብጬ.....
"ውሰጂው....."......አልኳት.....የምሬን ነበር።
"ሰው እኮ ነው እድል ኳስ አይደለም.....እንደ ኳስ በጠለዝሽው በኩል አይሄድም.....ልቡ በሚመራው መንገድ እንጂ.....ወደ እኔ ብትገፊው አይደለም ንፋስ አምጥቶ ከእኔ ጋር ቢያላትመው እንኳን ንፋሱ ሲሸሽ ይሸሻል.....ሰው ነው"......አለችኝ እና ፈገግ ነገር አለችልኝ.....
ወዲያው "ፍቅሬን ቀማሽኝ" የሚባባሉ እንስቶች እና ተባዕቶች አእምሮዬ ላይ መጡ.....ሀኒ እውነቷን ነው.....ሰው ናቸው ጆተኒ አልያም ኳስ አይደሉም.....ፈቅደው ይሄዳሉ እንጂ በተወረወሩበት እግር አቅጣጫ አይነዱም።
የሀኒ ስልክ ሲነዝር ያልበላበትን እጇን አስለቀቀችኝ.....
ጉሮሮዋን ጠራርጋ "ሄለው መኬ" ስትል አንገቴን ቀበርኩ.....
አላለቀም......
✍️ሸዊት
📢ሌሎች ቻናሎቻችንን ይቀላቀሉ፦
📔ማቆያ ➤ @Amba_Pdf_Books✅
🎭 ትረካ ➤ @Amba_Treka✅
🎓ትምህርት➤@Yetmhrt_Pdf✅
🎵 ሙዚቃ ➤ @AmbaMusic1✅