✨✨ፍቅር ቅብ-19✨✨
"ሰርፕራይዙን አበላሸሁት አይደል......".....አለቺኝ ስልኩን ከዘጋች በኃላ......
ግራ ገባኝ.....እሱን አግኝቼ እሷን ላጣት ነው....?...አንዱን አጥቶ ሌላ ማግኘት ህይወት ሊባል ይችላል....?.....ብሎልኝ ልቤን የሞላው ሰው ባሌ ከሆነ የሰርጌ እለት በግራ ባሌን አድርጌ በቀኝ የማደርጋት ስር ሚዜዬ ሀኒ ላትሆን ነው......?.....አጥንት የሚሰረስር ህመም ውስጥ ሆና ታጅበኝ ይሆን.....በሙሉ ልቧ "ይዟት በረረ....".....እያለች ትሸኘኝ ይሆን.....
ምን አለ እንዲህ ባታደርግ.....ምን አለ እንደመጀመሪያው ቀኗ ብትሆን.....ምን አለ ዛሬም እንደትናንቱ እንድታዘባት ብታደርግ.....በ"እድለኛ" ነሽ ፈንታ "መሰሪ ነሽ" ብትለኝ.....ምናል እንዲህ ባታደርግ.....አንገቷን ሰበር አድርጋ ባታለቅስ ምን አለበት.....ምናል እምባዋ እልህ ቢኖረው....ምናል አንድ ሁለት ስድብ ብትሰድበኝ...."ማን ስለሆንሽ ነው" ብትለኝስ.....
"አደራሽን ደግሞ እንዳላወቀ ሁኚ....ብዙም አትዘንጪ.....".....አለችኝ ስንሰነባበት.....ሳቅ ነገር ብትልልኝም ለፈገግታዋ መልስ አልሰጠሁም......ጭንቅላቴ ተወጥሯል....እያሰብኩ ነው.....ይሄ ነው የማልለው ከባድ ስሜት እየተጫወተብኝ ነው.....
"ስለ ባሌ የማወራው ለሀኒ እና ለንሰሀ አባቴ ብቻ ነው" የሚል መንግስት ያላፀደቀልኝ ህግ ነበረኝ....አሁን ስለመክብብ ምንድነው የምነግራት....ሌላው ቀርቶ የዛሬውን ቀን አብረን መፈንደቅ አልነበረብንም....ግማሽ ሳቅ ግማሽ ሳግ ይዤ ነው የፍቅር ጥያቄውን የምቀበለው....?
መታደልም አለመታደልም ነው ይሄ..... ዱባ እና ክትፎ ቀላቅሎ እንደመብላት ያለ ነው ይሄ....የፆም ቋንጣ እንደመስቀል ነው ይሄ.....ባንድ እግር ቤተስኪያን ቆሞ እንደማስቀደስ ባንዱ ደግሞ መሸታ ቤት ቡጊ ቡጊ እንደመጨፈር ግራ የገባው ነገር ነው.....በአንድ አይን የደስታ እምባ ባንዱ ደግሞ ዋይታ ነው ይሄ....
እሺም እምቢም ብለው ደስታ አለው....የቱ ደስታ ይበልጣል....?
***አመሻሽ ላይ ስልኬ ጠራ.......መክብብ።
"ሄለው እድሏ......"......አለኝ ፍቅር ባለበት ድምፅ....... እድሏ ብሎኝ አያውቅም.....እድሏ የምትለኝ እናቴ ብቻ ነበረች።
"አ....አቤት.....".....እንደእስከዛሬው ወዬ ማለት ሀኒን መክዳት መሰለኝ....
"የት ነሽ...."......አለኝ ወዬ አለማለቴን ከቁብ ሳይቆጥር......
"ቤት" አልኩት....ቤቴ ነበርኩ.....በቴሌቭጅን መስኮት ላይ በማያቸው በሚስቁ ሴቶች እየተደመምኩ....ይስቃሉ.....በጣም ይስቃሉ.....ይዝናናሉ.....ሰማይ ጠቀስ ህንፃዎች ውስጥ ገብተው እንደ ንግስት ይስተናገዳሉ....'ለአንድ ቀን ኖሬው ብሞትም አይቆጨኝ' የሚያስብል ኑሮ ለአንድ ቀን ይኖራሉ።
"እራት እንብላ"....አለኝ....ድምፁ ላይ መሳቀቅ ነበር......እንዳልገባው ሆኜ "ብሉ" ልለው ነበር.....ውስጤን ደስ አላለውም.... እሱ ያጠፋው አንድም ጥፋት አለመኖሩን ለማሰብ ሞከርኩ.....ስመኘው የነበረው ነገር እንደነበር አስታወስኩ.....ሰውየው መክብብ እንደሆነ አስታወስኩ...."መክብብ የወራት ክስተት ነው.....ሀኒ ግን የዘመናት......".....አለኝ ስሙን የማላውቀው የጭንቅላቴ ክፍል.....
በደስታዬ መደሰት አለመቻሌ አብከነከነኝ.....
"እና ምን አልሽኝ.....".....ጥያቄውን አስታወሰኝ።
"እሺ".....አልኩትና ወደሚያናውዘኝ ጭንቅላቴ ተመለስኩ።
***"ወድጄሻለሁ...."......አለኝና ኮፍያውን አውልቆ በራው ላይ ችፍ ያለውን ላብ በሶፍት አደራረቀ.....ፊት ለፊታችን ያስቀመጥነውን ምግብ ቆልለን.....ብዙ ዝባዝባዝንኬ እንደማልወድ የነገረችው ሀኒ መሆን አለባት....መግቢያም መንደርደሪያም የሌለው እንቅጭ ነው የነገረኝ....
የእጁን ርግብግቢት ያስተዋልኩት በእጁ የያዘው ሹካ አየር ላይ ሲውለበለብ ነበር....
"እድል" አለኝ ዝምታዬ ሲረዝምበት.....
"ወዬ".....አልኩትና አይኑ እንዳያገኘኝ ሳህኔ ላይ አፈጠጥኩ....
"ወድጄሻለሁ.....በጣም ወድጄሻለሁ....'ምን ታስቢያለሽ' ብዬ አልጠይቅሽም....ምንም ብታስቢ....ምንም ብትዪኝ እኔ ጋር የሚለወጥ ስሜት የለም....ድንገት እንደሆነብሽ እና እንዳስደነገጠሽ ይገባኛል....ምን አልባት ይሄን ለማለትም ፈጥኜ ይሆናል....ግን እድሏ ልቤ አላስቀምጥ አለኝ....መጀመሪያ ላይ እንዲሁ obsession መስሎኝ ነበር....ጭራሽ ጊዜ ሳይመርጥ ቀን እና ማታውን የማስበው ስላንቺ ሆኖ ሲያርፍ ቆም ብዬ ማሰብ ጀመርኩ....
ከልክ በላይ አሰብኩሽ....አንድ ሁለት ቀን ስለመስሪያ ቤት ሴቶች ለማሰብና አይኔ ላይ የምትጠገኚብኝን ነገር ለማደብዘዝ ሞከርኩ.....በውኔም በህልሜም በዚህ መንገድ አስቤያት ስለማላውቀው ሀኒ እራሱ ሳስብ ነበር.....ከማንም ላወዳድርሽ አልቻልኩም....አንቺን የማወቅ....አንቺን የመቅረብ ምኞቴ ከቀን ወደ ቀን እየጋለ ሄደ....".....አለኝና ፊት ለፊቱ ከተቀመጠው ውሀ አንድ ጉንጭ ጠጣለት።
"አይኔን የሳምከኝ እለት የሆንኩትን መሆን አስታውሳለሁ.... እረፍትም ፍርሀትም....ሳቅም ደስታም....ለቅፅበት የመኖር ፍላጎቴ ሲንር ይታወቀኝ ነበር....ላውቅህ እፈልጋለሁ.....በደንብ ላውቅህ....ሁልጊዜ እንባ ያቦዘዛቸውን አይኖቼን እንድትስም እፈልጋለሁ.....ባንተ መታቀፍ አለም ነው.....ስታዳምጠኝ ልብህን እስከ ጥግ ከፍተህ ነው....አንተን አለመውደድ አይቻልም"......ያለው ልቤ ነው......
ጎንበስ ብዬ ሳህኔ ላይ ያለችውን የሞተች ዶሮ ሬሳዋን በሹካ እየወጋሁ አላስተኛ እያልኳት ነው.....ላቤ ጀርባዬ ላይ ይንቆረቆራል....እንደ እሱ በራ ብሆን አናቴ ላይ ያለው ላብ ጎርፍ ሆኖ ይወስደው እና እኔም ከዚ አጣብቂኝ እገላገል ነበር......
"እድሏ......".....ጠራኝና 'መልስሽን እየጠበቅኩ' ነው አስተያየት አየኝ።
አላለቀም.....
✍️ሸዊት
📢ሌሎች ቻናሎቻችንን ይቀላቀሉ፦
📔ማቆያ ➤ @Amba_Pdf_Books✅
🎭 ትረካ ➤ @Amba_Treka✅
🎓ትምህርት➤@Yetmhrt_Pdf✅
🎵 ሙዚቃ ➤ @AmbaMusic1✅