የሚዲያን ጉልበት አለመረዳት
~
በኢስላምና በሙስሊሞች ላይ የሚደርሱ በደሎችንና ሴራዎችን በመቃወም ላይ መረባረብ አንዳንዶች እንደሚያስቡት ረብ የለሽ የቁራ ጩኸት ሳይሆን በዳዮችን እርቃን የሚያስቀር ትልቅ ስራ ነው። ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት ስራዎች ስር እየተከተሉ “ወሬ በቃን” “አታልቅሱብን”፣... የሚሉ ባላሰቡት በኩል ለጠላት በነፃ የሚያገለግሉ አካላት አሉ። አማራጭ ሃሳብ ካላቸው በቁም ነገር ሃሳባቸውን እንደማቅረብ በሌሎች ስራ ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ይቸልሳሉ። ፀረ ኢስላሙ አካል ያገር መግለጫ የሚያግተለትለው፣ ዶኩመንታሪ የሚለቀው፣ በዜና አውታሮቹ የተዛነፉ ዘገባዎችን የሚደርተው አላማው በጉዳዩ ላይ የህዝቡን ግንዛቤ መሬት ላይ ባለው መልኩ ሳይሆን፣ እርሱ በሚፈልገው መልኩ ለመቅረፅ ነው።
በኛ በኩል እነሱን የምንገዳደርበት በቂ የሚዲያ አውታር የለንም። ያሉትም ሊከፈትባቸው የሚችለውን ማጠልሸት በመስጋት በሚፈለገው መልኩ አይሰሩም። ክፍተቶቻችንን ለመድፈን ያለን አማራጭ ማህበራዊ ሚዲያ ነው። ማህበራዊ ሚዲያው ደግሞ ርብርብ ካልተደረገ ተፅእኖው ብዙም አይሆንም። ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሁሉ መረጃ አያገኝም። ሁሉ ሰው ጠንካራ ሃሳብ መፃፍ አይችልም። ሁሉ ሰው ደፍሮ አይጋፈጥም። በዚያ ላይ በርከት ያለ ተከታይ ያለው ወይም ተፅእኖ ማሳደር የሚችለው ጥቂት ነው። ስለዚህ ትርጉም ያለው ስራ ለመስራት ብዙዎችን የሚያሳትፍ ርብርብ ይጠይቃል። በመፃፍ፣ ላይክ በማድረግ፣ በማሰራጨት፣ ወዘተ።
የተለየ መልካም አማራጭ ያለው ደግሞ በጥንቃቄ ይሂድበት። ሁሉ ሰው በአንድ ቦይ እንዲፈስ አይጠበቅም። ችግሩ የሚመጣው ያለ ተጨባጭ ምክንያትና፣ ያለ ምንም አማራጭ የሌሎችን ጥረት ማጣጣል ሲመጣ ነው። የማያዛልቁ አማራጮች ካሉ ስሜትን መግታት ያስፈልጋል። መድረክ ላይ ወጥተው ሞቅ ሲላቸው የመጣላቸውን የሚናገሩ ሰዎች ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል። በፕሮፓጋንዳው ጦርነት የሚይዘውን ያጣው ሃፍረተ ቢሱ አካል የሚያራግበውን አጀንዳ ልናቀብለው አይገባም።
ወደተነሳሁበት ነጥብ ስመለስ የማህበራዊ ዘመቻዎችን ሚና ልናናንቅ አይገባም። ማድረግ ያለብን ቀዳዳዎች ካሉ መድፈን፣ ስህተቶች ካሉ ማረም፣ የጎን ለጎን አማራጮ ካሉ እነሱን ማየት ነው።
=
https://t.me/IbnuMunewor