ሩሲያ ወደ ዩክሬን የተኮሰችው “ኦሬሽኒክ” የተሰኘው ሚሳኤል በርካታ የአውሮፓ ሀገራትን በ20 ደቂቃ ውስጥ መምታት የሚችል ነው ተባለ
በሰዓት ከ12 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ ይጓዛል የተባለው ይህ አዲስ ሚሳኤል ለመምታት አስቸጋሪ እንደሆነም ተገልጿል ሩሲያ ወደ ዩክሬን የተኮሰችው “ኦሬሽኒክ” የተሰኘው ሚሳኤል በርካታ የአውሮፓ ሀገራትን በ20 ደቂቃ ውስጥ መምታት የሚችል ነው ተብሏል።፡
አሜሪካ እና ሌሎች የኔቶ አባል ሀገራት ለዩክሬን የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎችን መስጠታቸውን ተከትሎ ኪቭ ሞስኮን ከሰሞኑ አጥቅታለች፡፡ ይህን ተከትሎ ሩሲያ “ኦሬሽኒክ” በተሰኘ አዲስ አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ዩክሬንን መታለች፡፡
እንደ ሩሲያ መከላከያ መግለጫ ከሆነ ወደ ዩክሬን የተተኮሰው “ኦሬሽኒክ” ሚሳኤል በዲንፒሮ የሚገኘውን የሚሳኤል ማምረቻ እና የጦር መሳሪያ መጋዝንን አጥቅቷል፡፡ የአሜሪካ ጦር በዚህ ሚሳኤል ዙሪያ እንደገለጸው ሚሳኤሉ አዲስ እና አህጉር አቋራጭ፣ የኑክሌር አረር መሸከም የሚችል ነው ብሏል፡፡
ሩሲያ ሚሳኤሉን የተኮሰችው ለሙከራ ጭምር እንደሆነ ያሳወቀው የአሜሪካ ጦር ሚሳኤሉ በቀጣይ የመሻሻል አቅም እንዳለው እና ሞስኮ ይህንን ሚሳኤል በብዛት ሊኖራት እንደሚችልም ገልጿል ሩሲያ ወደ ዩክሬን አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል መተኮሷ የተነገረው የብሪታንያ ጦር በበኩሉ የሩሲያ አዲሱ ሚሳኤል አውሮፓን ኢላማ ለማድረግ ተብሎ የተሰራ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ከደቡባዊ ሩሲያ ወደ ዩክሬን የተተኮሰው ይህ ሚሳኤል ብሪታንያ ለመድረስ 19 ደቂቃ፣ ጀርመን ለመድረስ 14 እንዲሁም ፖላንድ ለመድረስ 8 ደቂቃዎች በቂ መሆናቸውን አርቲ ዘግቧል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በ40 ደቂቃዎች ውስጥ በአሜሪካ ያሉ ኢላማዎችን መምታት እንደሚችልም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
@Addis_Mereja