በትናንትናው እለት ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ሲጓዝ የነበረ አውቶቡስ ተጓዦች ታገቱ‼️
🗣መሠረት ሚድያ
- በተከፈተ የተኩስ እሩምታ የሞቱ መንገደኞችም እንዳሉም ታውቋል
ከባህር ዳር ከተማ ተነስተው በትናንትናው እለት ወደ አዲስ አበባ ሲጓዙ የነበሩ የአንድ አውቶቡስ ተሳፋሪ መንገደኞች በመንገዳቸው መሀል እንደታገቱ ታውቋል።
ለመሠረት ሚድያ የደረሰው መረጃ እንደሚጠቁመው እገታው የተፈፀመው በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ጎሀፂዮን ከተማ አቅራቢያ ነው። ታጣቂዎቹ የተኩስ እሩምታ አውቶቡሱ ላይ በመክፈታቸው የተገደሉ መንገደኞች እንዳለ የታወቀ ሲሆን የተረፉትን ይዘው ወደ ጫካ መግባታቸው ታውቋል።
"ከእገታው ያመለጡ የተወሰኑ ሰዎች አሉ፣ የፌደራል ፖሊስ ደርሶ ከታጣቂዎች ጋር እየተታኳሱ ነው" በማለት አንድ የአካባቢው ምንጭ ለመሠረት ሚድያ ተናግሯል።
ድርጊቱ መፈፀሙን 'የሹፌሮች አንደበት' የተባለው ገፅ ያረጋገጠ ሲሆን "ከጎሀፂዮን እና ቱሉ ሚሊክ ማዕከል አንድ አውቶብስ ሙሉ ሰው ታፍነው መወሰዳቸውን እና በተተኮሰ ጥይት የተሳፋሪ ህይወት ማለፉ ተሰምቷል" ብሏል።
በተመሳሳይ ከሁለት ሳምንት በፊት በፍቼ እና ጎሀፂዮን ከተሞች መሀል 58 ዜጎች መታገታቸው ይታወሳል። እነዚህን መንገደኞች ለመልቀቅ መንግስት 'ኦነግ ሸኔ' ብሎ የሚጠራቸው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላት ለአንድ ታጋች እስከ 1.5 ሚልዮን ብር እየጠየቁ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።
መጋቢት 8 ቀን የተፈፀመው ይህ እገታ በመንግስት ሚድያዎችም ሆነ በባለስልጣናት ምንም ቃል ያልተተነፈሰበት መሆኑ እጅጉን እንዳሳዘናቸው የታጋች ቤተሰቦች ገልፀው አሁን ላይ የቻሉትን ለመሰብሰብ የየቤቱ እየዞሩ እየለመኑ እንዲሁም በሶሻል ሚድያ ለህዝብ የእርዳታ ጥሪ እያቀረቡ መሆኑን ጠቁመው ነበር።
በዚህ መስመር ከዚህ በተደጋጋሚ እገታዎች የሚፈፀሙ ሲሆን በአካባቢው የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት አባላት በስፋት እንደሚንቀሳቀሱበት ይታወቃል።
@Esat_tv1@Esat_tv1