የሴቶች ምዕራፍ ትንታኔ ክፍል ሶስት፥ አንቀፅ ቁጥር ⑥ትናንት ለሰፊሆች ብር መስጠት ተገቢነት እንደሌለውና እኛ ልንጠብቅላቸው እንደሚገባ ተነጋግረናል ።
ታዲያ እስከመቼ ነው የሰፊኾችን ገንዘብ እኛ እየጠበቅን ፣ እኛ እያለማን ፣ እኛ እየተንከባከብን እኛ ወጭ እየሰጠናቸው የምንኖረው? ቢባል ፤ ነፍሳቸውን አውቀው ገንዘባቸውን ማስተዳደር የሚችሉበት አቅም ላይ እስከሚደርሱ ነው ። ለዚህ ብሎ ምን አለ ፦ «ወብተሉል የታማ/የቲሞችን ፈትኗቸው» ማለት ብቃታቸውን ከዚህ በኋላ ብሩ ቢሰጠው ማስተዳደር ይችላል ወይስ አይችሉም? የሚለውን ማለት ነው።
"ሀታ ኢዛ በለጙ ኒካህ" ጋብቻ እስከሚደርሱ ድረስ» በሸርዕ ደረጃ የተቀመጡ መስፈርቶች አሉ ፣ እነዛ ሲሟሉ ህፃን ከሚለው ወጥቷል ። ነገር ግን አንዳንዴ አካለ መጠን ደርሰውም የአእምሮ ብስለቱ ገና የሆነ ይኖራል ። ስለዚህ ምን አለ፦
"
ፈኢን አነስቱም ሚንሁነ ሩሽደን/ ከፈተናው በኋላ ነፍስ ማወቅን ከታዘባችሁ ፣ ከተገነዘባችሁ «ፈድፈዑ ኢለይሂም አምዋለሁም/ገንዘቦቻቸውን ወደነሱ አስጠጉ»። "
ሩሽድ" የሚለው
በዲናቸው ላይ ጥሩ መሆናቸውንና
በገንዘብ ጥበቃም ላይ ጥንቁቅ መሆናቸውን ስታውቁ ለማለት ነው ። አንዳንዴ ጎረምሳ ሆኖ ገንዘብ ሲሰጠው ወዳልሆነ አቅጣጫ የሚሄድ አለ .. ይሄ ሰው አይሰጠውም። ምክንያቱም አካሉ በስሏል አምሮው አልበሰለም።
ቀደም ብሎ ባለው አያ ላይ “አምዋለኩም/ገንዘባችሁ” እያለ ነበር አሁን ደግሞ “አምዋለሁም/ገንዘባቸው” ይለናል ፣
ያኔ እንደዛ ያለው ከብክነት ለመታደግ ነው ፣ ዛሬ ደግሞ ሰዎቹ ራሳቸውን ስለቻሉ የነሱ ብር ተብሎ ወደ ባለቤቱ ይመለስ በሚል አገላለፅ ገለፀው - የቁርአን አገላለጽ ሁሌም ድንቅ ነው።
ለካ አካለ መጠን ሲደርሱ ገንዘባቸው ወደነሱ ይመለሳል። ያ ቀን ሳይደርስ በፊት ለምን ዛሬ ቀንጨብ ፣ ቀንጨብ አላደርግም የሚል ዟሊም እንዳይኖር ደግሞ "
ወላ ተዕኩሉሃ ኢስራፈን" አለ በማባከን መልኩ ገንዘባቸውን እንዳትበሉ።
"ወቢዳረን አን የክበሩ" ነገ አድጎ ከእጄ ከመውጣቱ በፊት ዛሬ አትበሉ ። እናንተ ባለ አደራ እንጅ ባለ ገንዘብ አይደላችሁም ።
እንበልና ገንዘቡን ስንረከብ ልጁ የአንድ አመት ቢሆን አስራ አምሰት አመት በእኔ እጅ ነው ይሄ ገንዘብ ያለው ፣ ብሩን ማልማት አለብኝ ። አሁን ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ ፦
በሱ ገንዘብ ላይ ጉልበቴን ፣ ጊዜዬን ..ሳባክን የራሴን ኑሮ ትቼ እንዴት ነው የሚሆነው? የሚል ጥያቄ እንደሚመጣ ስለሚያውቅ ምን አለ « ወመን ካነ ጘኒየን ፈልየስተዕፊፍ» የየቲም ገንዘብ የሚንከባከብ ሰው ከዛ ከየቲሙ ገንዘብ ውጭ የራሱ የሆነ ገቢ ኖሮት የተብቃቃ የሆነ ሰው ለአሏህ ብሎ ይስራ .. ክፍያ ሳይጠይቅ ። ከዚህ ነገር ይጠንቀቅ ወይም ይራቅ ።
ድሃ ከሆነሳ? የየቲሞችን ገንዘብ የሚያለማ ከሆነ የራሱ ስራ ሊቀር ነው ፣ የነሱን ትቶ ወደ ራሱ ስራ ከሄደ የዚህ የየቲም ገንዘብ ሊባክን ነው። እህ ምን ይሁን ታዲያ ? ... ደመወዝ ይመደብለት! «ወመን ካነ ፈቂረን ፈልየእኩል ቢልመዕሩፍ»
የሚፈልገውን ያህል ሳይሆን የሚገባውን ያህል ደመወዝ ይመደብለት! ማነው የሚመድብለት? ከተባለ ያው ቤተዘመድ አለ ፣ ፍርድ ቤት ይኖራል ይህን በማስተዳደርህ ይሄ ይገባሀል ብሎ ይመድብለታል ። በዛ መልኩ መጠቀም ይችላል ። አሁንም ሌላ ጥያቄ ፦ ደሃ የሆነ የየቲም አሳዳጊ ይህን የየቲም ብር በደመወዝ መልኩ ከበላ በኋላ ሲያገኝ
ይመልሳል ወይስ
አይመልስም? በዚህ ላይ ፉቀሃወች ሁለት ቀውል አላቸው።
የመጀመሪያው .. አነስ ያለ መጠን የችግሩን ያህል ይመገብ
መመለስ አይጠበቅበትም። የላቡ ስለሆነ ሌላ ቦታ ቢሰራ ሊያገኝ የሚችለውን ነው ያገኘው ችግር የለውም የሚሉ አሉ (ሻፊኢያዎች) ምክንያታቸው ደግሞ አያው «ፈልየእኩል ቢልመዕሩፍ» ሲል "ይመልስ" አላለምና ይላሉ ።
ሁለተኛው ቀውል ደግሞ
የየቲም ገንዘብ በመሰረቱ ክልክል ነውና ለችግር ቢፈቀድለትም ሲያገኝ የመመለስ ግዴታ አለበት ያሉ ኡለሞችም አሉ ።
ገንዘባቸውን አስረክቡ ካለ በኋላ አሁን ደግሞ ሲያስረክቡ ሞግዚቶች እንዳይበደሉ
መስፈርት አስቀመጠ።ምን አለ «ፈኢዛ ደፈዕቱም ኢለይሂም አምዋለሁም» እናንተ አሳዳጊዎች የቲሞቹ አካለ መጠን ደርሰው
ገንዘባቸውን ስታስረክቧቸው ዝም ብላችሁ ጠርታችሁ ና ውሰድ ሳይሆን «
ፈአሽሂዱ አለይሂም/አስመስክሩባቸው » አለ ..ገንዘብ ያጨቃጭቃል ፣ የሚያናቁረውም የሚያፋቅረውም እሱ ነው ። ሙሲባ ነው ። ደግሞ ከሱ መብቃቃትም አይቻልም ። ስለዚህ የየቲሞቹን ዘመዶች አስቀምጦ ፦
የተረከብኩት ይሄ ይሄ ነበር ፣ ይህን ያህል ወጭ በማሳደግ ሂደት አውጥቻለሁ ፣ ይሄን ያህል ልማት ለምቷል ፣ በጥቅሉ ዛሬ የቀረለት ደግሞ ይሄ ነው ብሎ በምስክር ፊት ያስረክብ ይላል ። 🛑
ምስክር ከሌለ በኋላ የቲሙ ሊከዳ ይችላል ..ገንዘቤን ሲበላ ኖሮ መጨረሻ ላይ የቀረችውን እንኳ ሳያስረክበኝ ቀረ ሊል ይችላል ።
አልያም አሳዳጊው ትንሽ ነገር ወርወር አድርጎ ሌላውን ለራሱ ሊያስቀር ይችላል። ሲረከብም ምስክር መኖር እንዳለበት ሁሉ ወጭዎችም በትክክል መመዝገብ አለባቸው ፣ ሲያስረክብም በምስክር ፊት ቆጥሮ ማስረከብ ይጠበቅበታል።ይሄ ህግ ነው ።
በዚህ ህግ የሚኖር ማህበረሰብ ሚጨቃጨቅበት ምንም ሰበብ የለም!! ተቋጥሯል፣ ተደንግጎለታል ።
አስመስክረናል ብሎ ደግሞ የሆኑ የሆኑ ነገሮችን ደብቆ ፣ አታሎ የሚሰራ ካለ ደግሞ አብሽር ፣
የሰው ምስክር ባይኖርህ እኔ አለሁ እያለ ነው (ወከፋ ቢሏሂ ሀሲባ /ሂሳብ አድራጊ በአሏህ ይብቃ) ማንኛውንም ነገር አሏህ በመዝገቡ ላይ አስቀምጦታል ስለዚህ ዛሬ አማና ያልተወጣ ሰው ነገ ረቡል አለሚን ይተሳሰበዋል። ከምስክር ሁሉ በላይ ነው አሏህ ..
ይሄ ስሜት ልቡ ውስጥ ያለ ሰው ለማጭበርበር ፣ አኼራን ለመሸጥ አይጋለጥም .. ለህጉ ያህል ነገ ላለመጠየቅ ምስክሮችን ያስቀምጣል ፣ ረቡል አለሚን ፊት ደግሞ ላለመጠየቅ የራሱን ጥንቃቄ ያደርጋል ። ተቅዋ ካለ ፣ ህግ ካለ በደል የለም ።
በመሰረቱ የየቲም ገንዘብን ወደማስተዳደር ሰፍ ብሎ መግባት አደጋ ነው ፣ እንደውም አፊያ የፈለገ ሰው ከመጀመሪያው ይሄ ነገር ይቅርብኝ ቢል ይሻላል ። እሱ ካልገባ ይጠፋባቸዋል ብሎ ካልሰጋ በስተቀር ..ረሱል ﷺ ለአቡዘር «ኢኒ አራከ ዶዒፋ/ አቡዘር ሆይ እንደው ሳይህ ደከም ያልክ ሰው ነህ (ገራገር ነበሩ) ፣ እኔ ደግሞ ላንተ ለራሴ የምወደውን እወድልሃለሁ (ለራሴ የምመክረውን እመክርሃለሁ እንደማለት ነው) ፦ በሁለት ሰው መካከል አሚር እንዳትሆን (ስልጣንን ሽሻት ማለት ነው)
የየቲም ገንዘብ ላይም እንዳትሾም» ብለውታል ፤ መወጣቱ ከባድ ስለሆነ ማለት ነው ።
https://t.me/+VUDQfAORZa43NDM0