ዳጉ-ጆርናል/Dagu-Journal


Channel's geo and language: Ethiopia, Amharic


The best fiction is far more true than any journalism
📢 ተዓማኒ የመረጃ ምንጭ ፤ ለሙያው ስነምግባር ተገዢ በሆኑ ጋዜጠኞች ብቻ
👉 በፌስቡክ ገፆቻችን https://www.facebook.com/simon.dereje.56
👉 https://www.facebook.com/mik0Man

Related channels  |  Similar channels

Channel's geo and language
Ethiopia, Amharic
Statistics
Posts filter


በኢሊባቡር ዞን የአስገድዶ መድፈር ጥቃት የፈፀመዉ ግለሰብ በእስራት ተቀጣ

የኢሊባቡር ዞን ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ለማ ቦይዶ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት ተከሳሽ እሸቱ ጉዲና የተባለዉ ግለሰብ ድምፅ አልባ በሆነ ስለታም ጩቤ መሳሪያ በማስፈራራት የ15 አመቷ ልጅ ላይ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት መፈፀሙ ተገልጿል ።

ተከሳሹ ጥቃቱን የፈፀመዉ በኢሊባቡር ዞን ሱጴ ሶዶ ወረዳ ዉስጥ ታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም ሲሆን ተጠቂዋ ለቤተሰቦቻ የደረሰባትን ጥቃት በማሳወቋ ወዲያውኑ ፖሊስ ተከሳሹን በቁጥጥር ስር ሊያዉለዉ ችሏል ። ፖሊስም ታዳጊዋን ወደ ህክምና ተቋም ወስዶ ካስመረመረ በኋላ የምርመራ መዝገቡን በተጠቂዋ ቃል በማደራጀት ለአቃቤ ህግ ልኳል ።

አቃቤ ህግም መዝገቡን በመመልከት በወንጀል ህግ ቁጥር 620 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ተጎጂዋ መከላከል በማትችልበት መንገድ በኃይልና በመሳሪያ በማስፈራራት የመድፈር ጥቃት በመፈፀም ክስ መስርቶበታል ። ክሱን ሲከታተል የቆየዉ የኢሊባቡር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተከሳሹ የፈፀመው ድርጊት በአቃቤ ህግ ማስረጃ ጥፋተኛነቱ በመረጋገጡ የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለዉ ችሎት በ6 አመት እስራት እንዲቀጣ የተወሰነበት መሆኑን ምክትል ኢንስፔክተር ለማ ቦይዶ ጨምረዉ ለብስራት ተናግረዋል፡፡

በመባ ወርቅነህ
#ዳጉ_ጆርናል


Video is unavailable for watching
Show in Telegram
በትግራይ ክልል አዲ ጉዶም ዛሬ🕊🕊🕊

#ዳጉ_ጆርናል


የትግራይ ነዋሪዎች ስላለዉ ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይላሉ....

ቢቢሲ ከክልሉ ማዕከላዊ እና ምሥራቃዊ ዞኖች አንዲሁም ከመቀለ ከተማ አስተዳደር በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታ በማስመልከት ያነጋገራቸው ግለሰቦች መሪዎቹ ወደ ጦርነት እየጎተቱ እንዳያስገቧቸው እንደሚሰጉ ይገልጻሉ።

በአዲግራት፣ በመቀለ እና በሌሎች አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች የፍጆታ ዕቃዎች ዋጋ መጨመር፣ በገፍ መሸመት እና የመረበሽ ሁኔታ እንደሚታይባቸው ይናገራሉ።

ይህ ስጋት ከክልሉ የሚወጡ ሰዎች ቁጥር እንዲጨምር ማድረጉንም አመልክተዋል።

አብርሃም የተባለ የአዲግራት ከተማ ነዋሪ፣ "አርሚ 15፣ ሚሊሻ እና ተፈናቃዮች የሚገኙባቸው አካላት የከንቲባውን ጽህፈት ተቆጣጥረዋል" ብሏል።

በከተማዋ ሙሉ በሙሉ ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳለ በመግለጽም "የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ነው የሚመስለው። ከትናንት [ሰኞ] ጀምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አለ" ብሏል።

ይህ ሁኔታ ሰላማዊ ዜጎች ላይ መረበሽ እንደፈጠረ በመግለጽ በሁለቱም አካላት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች የፕሪቶሪያ ስምምነት በውል የሚያፈርሱ መሆናቸውን እንደሚያምን ይናገራል።

"ይህንን ተከትሎ የፌደራል መንግሥት የፈለገውን ዓይነት እምርጃ ሊወስድ ይችላል። በትግራይ ድሮኖች ሲያንዣብቡ ሰንብተዋል። ይህ ከኤርትራ ጋር ያለው ነገር ያመጣው ሲመስለን ቆይቷል። ሆኖም አሁን ባለው ወቅታዊ ሁኔታ የትግራይ የፀጥታ ሁኔታን መንግሥት እየተከታተለ አንደነበር ነው የሚሰማኝ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

በማዕከላዊ ዞን የሚኖረው አርሶ አደር ካህሳይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰተ ያለው ሁኔታ "አለመረጋጋት" እንደፈጠረበት ይናገራል።

"ይህም ተመልሰን ወደ ጦርነት እንገባ ይሆን? የሚል ፍርሀት አሳድሮብኛል። ከዚህ በፊት ያለፈው አሰቃቂ ነው። በሰው ዕድሜ ማየት የሚገባንን አይተናል። ይህ አልፎ የተገኘው አንጻራዊ ሰላም ሕብረተሰቡ ተስፋ እንዲኖረው አድርጎ ነበር" ብሏል።

ቢቢሲ ከክልሉ ዋና ከተማ መቀለ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የከተማዋ እንቅስቃሴ የተለመደው ዓይነት ቢሆንም የስሜት መረበሽ እንዳለ ይገልጻሉ።

ስሟ እንዳይጠቀስ የጠየቀች አንድ የከተማዋ ነዋሪ "አንድም ደስ የሚል ነገር የለም። ገበያው ዋጋ ጨምሯል። ሰውም ፊቱ ላይ ጭንቅ ብቻ ነው የሚነበበው። ይህ ሁኔታ ዳግም መውጫ እና መግቢያ ወደ ሌለው ከበባ እንዳያስገባን ነው የምሰጋው።"

ሐዱሽ የተባለው ወጣት ደግሞ ፍርሃት እና ጭንቀት በአካባቢው የሚያየው ሁኔታ የሚገለፁበት መንገድ እንደሆነ በመግለጽ "ጦርነት አይቀርም" የሚል ስጋት አለው።

ደም አፋሳሹ የሁለት ዓመት ጦርነት ፍርሃት እንዳልለቀቀው የሚናገረው ወጣቱ "በሰላም እጦት ምክንያት መሥራት አልቻልኩም፤ አሁን ያለውን ሁኔታ ሳይ በጣም አዝናለሁ፣ እበሳጫለሁ። በከበባው ወቅት ብዙ ነገር አሳልፈናል። ረሃብ: ጥማት የካድሬዎች ጉትጎታን አሳልፈናል። ተመልሰን ወደ ዚያ ልንገባ ነው ወይ? በሚል እሰጋለሁ።"
በበርካታ የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ከአካባቢያቸው ወጥተው ወደ አዲስ አበባ እና አንዳንዶቹም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ለስደት ማምራታቸውን ይናገራል።

የክልሉ የፖለቲካ አመራሮች ይህ ሁሉ ስጋት እንዲጨምር አድርገዋል በሚል ይወቀሳሉ።

አስተያየት ሰጪዎቹ በምንም ሁኔታ ክልሉ አሁንም የጦር አውድማ መሆን የለበትም ይላሉ።

Via ቢቢሲ አማርኛ
#ዳጉ_ጆርናል


በትግራይ ክልል ያለው ውጥረት ወደ ግጭት እንዳያመራ ስጋት ስለመኖሩ ተነገረ‼️

የሁለቱ የህወሓት ቡዱኖች አለመግባባት አሁን ላይ ወደ ግጭት እየተሸጋገረ ያለ ይመስላል። ዛሬ ማለዳ የአዲግራት ከተማ አስተዳደር ፅህፈት ቤት "በጉልበት" የተቆጣጠረው በእነ ደብረፅዮን የሚመራው ህወሓት በአዲግራት ያደረገውን በሌሎች የትግራይ ከተሞች ለመድገም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ዳጉ ጆርናል በትግራይ የተለያዩ ከተሞች ካሉ ምንጮቹ ሰምቷል።

ዛሬ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ/ም በነ ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ቡዱን የመንግስት ስልጣን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ለመቀማት ከሞከረባቸው አከባቢዎች መካከል አንደኛዋ በሆነችው ዓዲ ጉዶም ከተማ ዛሬ በተኩስ ድምፅ ስትናወጥ ማምሸቷን የነገሩን አንድ የከተማዋ ነዋሪ "የዛሬው ድርጊታቸው በስልጣናቸው ለመጣ ምንም ርህራሄ እንደሌላቸው ማሳያ ነው" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ቡድኑ በመቀለ ከተማ የሚገኙ የክፍለ ከተማ አስተዳደር ፅህፈት ቤቶችን በተለይም የአዲ ሓቂ ክፍለ ከተማ ፅህፈት ቤት በጉልበት ለመቆጣጠር ያደረገው ጥረት በገጠመው ከፍተኛ ተቃውሞ ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱ ተገልፆል።

በእነ ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን እያካሄደው ያለው ስልጣን የማስመለስ ዘመቻ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በተገለፀበት በዚህ ወቅት በአዲግራትና አዲ ጉዶም ከተሞች የተስተዋለው ክስተት ወደ ግጭት እንዳያድግ ስጋት ጭሯል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ ትላንት በሰጡት መግለጫ በእነ ደብረፅዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን ዳግም ወደ ስልጣን እንዳይመለስ ለማድረግ እንደሚሰሩ በገለፁ ማግስት ቡድኑ የአዲግራት ከተማ መስተዳድር በመቆጣጠር የራሱ ከንቲባ ወደ ቢሮ ማስገባቱ በይፋ አስታውቋል።

#ዳጉ_ጆርናል


ባለፉት አራት ወራት ከ300 ሺ በላይ ሱዳናውያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል

ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይኦኤም) እንዳስታወቀው ከሆነ ከዚህ ቀደም በአልጃዚራ፣ ሴናር እና ካርቱም ግዛቶች ይኖሩ የነበሩ ነገር ግን በጦርነቱ የተፈናቀሉ 396ሺ ሰዎች ወደ መኖርያ ቀያቸው መመለሳቸው ገልፆል።እ.ኤ.አ ኦክቶበር 23 የሱዳን ጦር በአብዛኛዎቹ ሴናር እና አልጃዚራ ግዛቶች እንዲሁም በካርቱም ባህሪ (ሰሜን ካርቱም) እና በኦምዱርማን እንዲሁም ደቡብ ካርቱም ላይ ቁጥጥሩን ከማስፋፋቱ በፊት የአል ዲንዲርን ከተማ መልሷል።

አይኦኤም በሰጠው መግለጫ ከታህሳስ 18 ቀን 2024 እስከ መጋቢት መጀመሪያ ባለው ጊዜ ውስጥ 396ሺ 738 የሚጠጉ ተፈናቃዮች ወደነበሩበት መመለሳቸውን የመስክ ቡድኖቹ አረጋግጠዋል። አብዛኛዎቹ ተመላሾች ወደ አል ጃዚራህ ፣ ሴናር  እንዲሁም ካርቱም መሆናቸውን ገልጿል።አይኦኤም ስለ ተመላሾቹ የቀድሞ ቦታዎች ዝርዝር መግለጫ የሰጠ ሲሆን ወደ አል ጃዚራህ ግዛት ከተመለሱት 262ሺ 645 ግለሰቦች መካከል ትልቁን ድርሻ የያዙት ከገዳረፍ 44 በመቶ፣ ሴናር 21 በመቶ፣ ካሳላ 11 በመቶ እንዲሁን ናይል ወንዝ 9 በመቶ ናቸው ብሏል።

ወደ ሰናር ግዛት የተመለሱት ደግሞ 114ሺ 759 ሰዎች ሲሆኑ ወደ ካርቱም ግዛት የተመለሱት ደግሞ 19ሺ 334 ግለሰቦች ናቸው ብሏል።በቀጠለው ግጭት 11.5 ሚሊዮን ሱዳናውያን ቤታቸውን ጥለው ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እንዲሰደዱ የተገደዱ ሲሆን 3.3 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ለደህንነት ሲባል ድንበር ጥሰው ወደ ጎረቤት ሀገራት ገብተዋል።የስደት ተመላሾች አሀዛዊ መረጃ በዚያው ክልል ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃዮችን የመመለስ እንቅስቃሴ እንደማይጨምር IOM ገልጿል።  ይህ ማለት የተመላሾች ቁጥር ከተዘገበው በላይ ሊሆን ይችላል ። የሱዳን መንግስት ሰራዊች ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ እያበረታታ ይገኛል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል




በዶ/ር ደብረፂዮን የሚመራዉ የህወሓት ቡድን በአንዳንድ አካባቢዎች የአስተዳደር ተቋማትን በሀይል መቆጣጠር ጀመረ‼️

ለወራት የቆየው በህወሓት አመራሮች መካከል ያለው አለመግባባት ተባብሶ እንደቀጠለ መሆኑ ተሰምቷል። ባለፉት ወራት በደብረፂዮን (ዶ/ር) የሚመራው ወገን የጊዜያዊ አስተዳደሩን ሥልጣን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎች ሲወስድ ቆይቷል።

በአቶ ጌታቸው የሚመራው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደርም ይህ ሙከራ በክልሉ አለመረጋጋት በማስፈን ያለውን ችግር እንደሚያባብስ በመግለጽ ቢያስጠነቅቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ውጥረቱ እየተባባሰ ይገኛል ሲል ቢቢሲ አማርኛ ዘግቧል።

ባለፉት ቀናት በክልሉ ያሉት ታጣቂ ኃይሎች አመራሮች ድጋፍ እንዳለው የሚነገርለት የደብረፂዮን ቡድን በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ የአስተዳደር ተቋማትን በኃይል የመቆጣጠር አዝማሚያ እያሳየ መሆኑ እየተገለጸ ነው።

ይህ ሁኔታም በክልሉ ዳግም ግጭት ሊያስከትል ይችላል በሚል ነዋሪዎች ላይ ከባድ ስጋትን የፈጠረ ሲሆን፣ አቅም ያላቸው ወደ አዲስ አበባ እና ወደ ሌሎች አካባቢዎች እያቀኑ መሆናቸውን ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በተለይ በአቶ ጌታቸው የሚመራው አስተዳደር የትግራይ ኃይልን ከሚመሩት ወታደራዊ አዛዦች መካከል ዋነኛ የሚባሉትን ሦስት መኮንኖች ማገዱን ካስታወቀ በኋላ ውጥረቱ አይሏል።

ዛሬ ማክሰኞ ረፋድ ላይ በምሥራቃዊ ዞን የጊዜያዊ አስተዳደሩን የተቃወሙ የሠራዊት አመራሮች ከመሩት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የአዲግራት ከንቲባ ጽህፈት ቤት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ቁጥጥር ውጪ መሆኑ ታውቋል።

ይህንን ተከትሎ በሰላማዊ ሰዎች እና በታጣቂዎች መካከል የተፈጠረ ግጭት ወይም የደረሰ ጉዳት እንዳለ አልተገለፀም።

ትናንት ሰኞ የዞኑ ሰላም እና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ለአራት ሰዓታት በዶ/ር ደብረፂዮን በሚደግፉ የፀጥታ ኃይሎች ታስረው ነበር።

የአዲግራቱን ከንቲባ ጽህፈት ቤት በቁጥጥር ስር ማዋሉን ህወሓት በፌስ ቡክ ገፁ አረጋግጧል።

"የአዲግራት ከተማ ከንቲባ ሆኖ በምክር ቤት የተሾመው ረዳኢ ገብረ እግዚአብሔር በምስለኔ ግለሰቦች በተሾሙ ሰዎች ምክንያት ጽህፈት ቤቱን ተረክቦ አገልግሎት እንዳይሰጥ አደርጎ ቆይቷል" በማለት ጽህፈት ቤቱን መልሰው መቆጣጠራቸውን ገልጸዋል።

Via ቢቢሲ አማርኛ
#ዳጉ_ጆርናል




በመቱ ከጋብቻ ውጪ የወለደቻትን ልጅ በመግደል መፀዳጃ ቤት ውስጥ የከተተችዉ ግለሰብ በእስራት ተቀጣች

በኢሊባቡር ዞን መቱ ወረዳ ውስጥ ከጋብቻ ውጪ የወለደቻትን ልጅ በመግደል መፀዳጃ ቤት ውስጥ የከተተችው ግለሰብ በእስራት መቀጣቷ ተገለፀ። የኢሊባቡር ዞን ፖሊስ ዋና መምሪያ የኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ለማ ቦይዶ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት ተከሳሽ አሚና እንድሪስ የተባለችው የ23 ዓመት ወጣት ሀምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ከቀኑ 5:30 ላይ ሴት ልጅ ከጋብቻ ውጪ የተገላገለች ሲሆን ወዲያውኑ የወለደቻትን ልጅ  መፀዳጃ ቤት ውስጥ እንደከተተቻች በማስረጃ ተረጋግጧል::

ተከሳሿ ሳታውቅ ከጋብቻ ውጪ አርግዛ ሴት ልጅ በሰላም ከተገላገለች በኋላ ከጎረቤቷ ባለው መፀዳጃ ቤት ውስጥ በህይወት ያለችውን ልጅ በመክተት ህይወቷ እንዲያልፍ ማድረጓ ተረጋግጧል። በመፀዳጃ ቤት ውስጥ የተለየ የደም ምልክት የተመለከቱት የቤቱ ባለቤቶች ጉዳዩ እንዲጣራ ለፖሊስ በማመልከታቸው ፖሊስ ባደረገው ማጣራት እና ክትትል ተከሳሿ  በህብረተሰቡ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ዉላለች፡፡

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላትን ተከሳሽ ከጋብቻ ውጪ በመውለዷ የወላጆቿን እና የአካባቢውን ሰዎች ተፅዕኖ በመፍራት የወለደቻትን ሴት ልጅ ከነ ህይወቷ በመፀዳጃ ቤት ውስጥና መክተቷን ለፖሊስ በሰጠችው ቃል ማረጋገጥም ተችሏል። ፖሊስ አስፈላጊ የተባለውን ምርመራ ሂደት በበቂ ማስረጃ በማጠናከር የምርመራ መዝገቡን ለአቃቤ ህግ ልኳል።

አቃቤህግም ከፖሊስ የተላከለትን የምርመራ መዝገብ በወንጀል ህግ ቁጥር 544 ንዑስ አንቀፅ 2 ልጅን አስቦ ወይም በቸልተኛነት በመግደል ወንጀል ክስ መስርቷል። የተመሠረተውን ክስ ሲከታተል የነበረው የኢሊባቡር ዞን ከፍተኛዉ ፍርድ ቤት ተከሳሿ በአቃቤ ህግ የተመሠረተውን ክስ ማስተባበል ባለመቻሏ እና ጥፋተኛነቷ ሙሉ በሙሉ በመረጋገጡ አሚና እንድሪስ በዘጠኝ አመት እስራት እንድትቀጣ የካቲት 28 ቀን 2017 ዓ.ም በዋለው ችሎት ዉሳኔ ማሳለፉን ምክትል ኢንስፔክተር ለማ ቦይዶ ጨምረው ለብስራት ተናግረዋል፡፡

በሰመኃር አለባቸዉ
#ዳጉ_ጆርናል




በአዲስ አበባ ብሥራተ ገብርኤል አካባቢ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካርል አደባባይ ቅርንጫፍ ላይ በዛሬው ዕለት በተፈጠረ አለመግባባት የሰዎች ህይወት ማለፉ ተሰምቷል።

በአለመግባባቱ ሳቢያ የሦስት ሰዎች ህይወት ሳያልፍ እንዳልቀረ ቲክቫህ ኢትዮጵያ ጉዳዩን ከተከታተሉ ሰዎች መረዳት ችሏል።

ህይወታቸው ያለፈው በባንኩ በጥበቃ ሰራተኝነት ሲያገለግሉ የነበሩ አካላት ናቸው።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ በባንኩ የሰው ህይወት ስለማለፉ ማረጋገጥ ቢችልም ዝርዝር ክስተቱን ከባንኩ ለማረጋገጥ ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም።

ይህንን በሚመለከት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንን የጠየቅን ሲሆን "ጉዳዩ በምርመራ ላይ ነው" የሚል አጭር ምላሽ አግኝተናል።

ቲክቫህ ኢትዮጵያ
#ዳጉ_ጆርናል


የዓለማችን የሙቀት መጠን መጨመር የአይጦች ቁጥር እንዲበራከት እያደረገ ነው ተባለ

አይጦች በተለየና በተሻለ መንገድ ከተሞችን የመላመድ ክህሎት እንዳላቸው ይነገራል። ጥር ወር ላይ የወጣ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ ደግሞ በከተሞች ላይ ያለው የሙቀት መጠን እየጨመረ በሄደ ቁጥር የአይጦች ቁጥርም በዛ ልክ እያደገ ይሄዳል።

ጥናቱ "ከተሞች ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን እያስተናገዱ በሄዱ ቁጥር በዋሻዎቻቸው ያሉ አይጦችም ቁጥራቸው ይጨምራል" ያለ ሲሆን በሪችሞንድ ዩኒቨርስቲ አርባን ኢኮሎጂስት የሆኑትና የጥናቱ ዋና ፀሓፊ  ጆናታን ሪቻርድስ በበኩላቸዉ "ከፍተኛ የሆነ የሙቀት መጠን ባለው አከባቢ የሚኖሩ ሴት አይጦች በቶሎ መውለድ እንደሚጀምሩ ለማወቅ ችለናል" ብለዋል።ጥናቱ በ16 ከተሞች ከ2007 እስከ 2024 የተመዘገቡ ከአይጥ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎችን እንደ ግብዓት የተጠቀመ ሲሆን ቅሬታዎቹ የአይጥ ቁጥር ጭማሬ እያሳየ መሆኑን አመላካች ናቸው።

በጥናቱ መሰረት በ11 ከተሞች ቅሬታዎቹ እየቀረቡ በነበረበት ጊዜ የአይጦች ቁጥር ጭማሬ ማሳየቱ አረጋግጧል። በከፍተኛ ሁኔታ የአይጦች ቁጥር እየጨመሩባቸው ካሉባቸዉ ከተሞች መካከል ደግሞ ቀዳሚዋ ዋሽንግተን ዲሲ ስትሆን ባለፉት 10 ዓመታት በከተማይቱ ያሉ አይጦች ቁጥር በ390 በመቶኛ ጭማሪ አሳይቷል። ከዲሲ በመቀጠል ሳን ፍራንሲስኮ 300 በመቶኛ ጭማሪ ያሳየች ሲሆን፣ ቶሮንቶ በ186 በመቶኛ፣ ኒውዮርክ በ162 በመቶኛ ተከታዩን ስፍራ ይዘዋል። ከዚህ ባሻገር እንደነ ኒው ኦርላንስ፣ ቶኪዮ፣ ሉዊስቪልና ኬንታኪ የመሳሰሉ ከተሞች ደግሞ የአይጥ ቁጥር መቀነስ የታየባቸው ናቸው።

ተመራማሪዎቹ በርካቶች የአየር ንብረት ለውጡ እንዴት ነው የአይጦች ቁጥር ጭማሪ ላይ ተፅእኖ ሊያሳድር የሚችለው ብለው ይጠይቃሉ ነገር ግን አይጦች በእርግጥም አይሩ በተቀያየረ ቁጥር ፀባያቸው ይቀያየራል፣ ይህም አየሩ ቀዝቀዝ ሲል አይጦቹ ለመደበቅ ይሞክራሉ የሚደበቁት ደግሞ በግድግዳ ውስጥና ሌሎች ተመሳሳይ ነገሮች ነው፤ አየሩ ሞቅ በሚልበት ሰዓት ደግሞ አይጦች መንቀሳቀስና ምግብ ለመፈለግ እንደሚሰማሩ በጥናታችን አረጋግጠናል ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በከተሞች ላይ ያለው የሙቀት ጭማሪ ለአይጦች ተስማሚ ነው ያለው ጥናቱ ህንፃዎችና ኮንክሪቶች የፀሓይን መቀት አምቀው የመያዝ አቅም አላቸው በተለይ ከ27 ዲግሪ ፋራንሀይት በላይ የሆነ የሙቀት መጠን ካለ ህንፃዎች ቀኑን ሙሉ ሲሰበስቡት የዋሉትን ሙቀት ምሽት ላይ ይለቁታል፡፡ ይህ ደግሞ ለአይጦች መራባት በጣም ምቹ ይሆናል ሲሉ ተመራማሪው ሪቻርድስ አክለዋል።ከመቀቱ በተጨማሪ ግን በከተሞች የሚኖር ህዝብ ቁጥሩ መጨመሩን ሌላ ምክንያት ነው:: የህዝብ ቁጥር በጨመረ ቁጥር ተርፎ የሚጣል ምግብና ቆሻሻ በዛ ልክ ይጨምራል ይህ ደግሞ ለአይጦች ጥሩ የምግብ ግብዓት ሆና ያገለግላል ብለዋል።

በሚሊዮን ሙሴ
#ዳጉ_ጆርናል




አቶ አቤል ታደሰ የኢትዮጵያ መድህን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሆነው ተሾሙ


የኢትዮጵያ ኢንቨስትመት ሆልድንግ አቶ አቤል ታደሰን የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አድርጎ ሾሟል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዱንግ የፋይናንስ ክሊስተር ዘርፍ አማካሪነት በማገልገል ላይ የነበሩ ሲሆን በዘርፉም የ23 ዓመታት የስራ ልምድ ያላቸው መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዱንግ በአሁኑ ሰዓት በሥሩ ከሚያስተዳድራቸውና ከሚቆጣጠራቸው ድርጅቶች አንዱ የመንግስት የልማት ድርጅት መሆኑ ተገልጿል።

በኢትዮጵያ የመድን ኢንዱስትሪ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት በ1968 ዓም መመስረቱም ተገልጿል።

#ዳጉ_ጆርናል


የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የትኛውንም ዓይነት የሃይማኖት ተቋማትን፣ አስተምህሯቸውንና መገለጫዎቻቸውን የሚያንቋሽሹና የሚያዋርዱ ንግግሮችንም ሆነ ተግባራትን በጽኑ አወገዘ

ጉባኤዉ ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ እየታየ ያለዉን ሀይማኖታዊ አለመከባበር አዉግዞ መግለጫ አዉጥቷል።

በጉባኤዉ መግለጫ በእስልምና እና በኦርቶዶክስ ተዋህዶ አንዳንድ አማኞች ዘንድ ታይቷል ያለዉን ጸያፍ ንግግሮች ነዉ ያወገዘዉ።

አንዳንድ የኦርቶዶክስ ክርስትና አማኝ ነን የሚሉ ግለሰቦች፣ የእስልምና ሃይማኖት ነቢይ በሆኑት በነቢዩ መሐመድ ላይ ድፍረት የተሞላበት ክብረ ነክና ጽያፍ ንግግር ሲያደርጉ ታይተዋል ፤ ይህም ሙስሊሙን ወገን ብቻ ሳይሆን ሰላም ወዳዱን ወገን ሁሉ አሳዝኗል ብሏል ጉባኤዉ፡፡

በተመሳሳይ አንዳንድ ሙስሊም ነን የሚሉ ግለሰቦች ተደፈርን በሚል ስሜት የክርስትና አስተምህሮንና የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር የሚነቅፍና የሚያጠለሽ፣ መላውን ክርስቲያን በሚያዋርድ መልኩ ምላሽ ሲሠጡ እና ድርጊቱን በፈፀመው ግለሰብ ላይ የደቦ ፍርድ ሲያስተላልፉ ይታያሉ፡፡

ጉባኤዉ ይህ ዓይነቱ ኢ-ሥነምግባራዊ እና ሕገ ወጥ ተግባር የትኛውንም የሃይማኖት ተቋም የማይወክል፣ ይልቁንም የሚወገዝ ተግባር መሆኑን ገልጿል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም አንዳንድ የኦርቶዶክስ አማኝ ነን የሚሉ ወንድሞችና እህቶች የግለሰቡን ሕገ-ወጥ ተግባር ተቋማዊ ለማድረግ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲያጤኑና ግለሰብንና ተቋምን እንዲለዩ ጉባኤዉ መክሯል፡፡

በተመሳሳይ በአንዳንድ የእስልምና እምነት ተከታዮች የደቦ ፍርድን በማስተላለፍ ላይ ከመሆናቸዉ ጋር ተያይዞ ሕገ-ወጥነትን ከማስፋፋት ባለፈ ጥፋትን በሌላ ጥፋት ማረም ፈጽሞ የማይቻል መሆኑን ተገንዝበው ከድርጊታቸው በመታረም የሕግ የበላይነትን እንዲስቀድሙ ጉባኤዉ መክሯል፡፡

በየትኛውም አካል የተፈፀሙትና የሚፈፀሙት ይህን መሠል ሕገ-ወጥ ተግባራት በሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ ተቀባይነት የሌላቸው ብቻ ሳይሆን የሚወገዙ ተግባራት መሆናቸውን ጉባኤዉ አስገንዝቦ ድርጊቱ በወንጀል የሚስጠይቅ ስለመሆኑም አስታዉሷል።

#ዳጉ_ጆርናል




በወራቤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የጉሮሮ ካንሰር  በብዛት እየተስተዋለ ይገኛል ተባለ

በወራቤ ኮምፕሬንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በጉሮሮ ህመም ለምርመራ ከሚመጡ አምስት ታካሚዎች ውስጥ ሁለቱ የጉሮሮ ካንሰር ተጠቂ ናቸው ይላል::

የሆስፒታሉ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን  ክፍል ባለሙያ የሆኑት አብዱልጀባር አብደላ ለብስራት ሬዲዮ  እና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ከሆስፒታል የኢንዶስኮፒ ምርመራ ክፍል የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በአካባቢው የጉሮሮ /የምግብ መውረጃ ቱቦ/ ካንሰር በጣም እየበዛ መሆኑን ገልጸዋል ።

ወደ ክፍሉ ለምርመራ ከሚመጡ አምስት ታካሚዎች ውስጥ ሁለቱ የጉሮሮ ካንሰር ተጠቂ ሆነው እንደሚገኙ ነው የምርመራ ክፍሉ መረጃ ያሳያል።የጉሮሮ ካንሰር  የመዋጥ ችግር ፣ በተደጋጋሚ ማስመለስ ፣ ክብደት መቀነስ፣ የምግብ ፍላጎት ማጣት ፣አቅም ማጣት ድካም እንዲሁም የምግብ አለመፈጨት ስሜት ፣ የማይቋረጥ ሳል ፣ የድምጽ መጎርነን የበሽታው ምልክቶች መሆናቸው  ተጠቁሟል። ለህመሙ  ተጋላጭ ምክንያቶች የሚባሉት ደግሞ ማጨስ፣ ከመጠን ያለፈ አልኮል መጠጣት ፣ ትኩስ ነገር /ከፍተኛ ሙቀት ያለው ምግብና መጠጥ ፣ የቆየ የጨጓራ ህመም መሆኑ ተጠቁሟል ።

በተቋሙ ህመሙ የተገኘባቸው ታካሚዎች አብዛኛዎቹ ከሲጋራና ከአልኮል ጋር ግንኙነት የነበራቸው አለመሆኑ ተነግሯል ። ይሁን እና ታካሚዎቹ እንደ ገንፎ፣ ድንች ያሉ በጣም በትኩስነታቸ ለምግብነት የሚቀርቡ  ምግቦች እንዲሁም እንደ ቅሽር ያሉ ትኩስ ሻይ ፣ ቡና አጠቃቀም ላይ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ አመላካች ነገር መኖሩን የክፍሉ ባለሙያዎች ጠቁመዋል።

ህመሙ በተመለከተ ከሚመለከተው አካል ጋር በመሆን ሰፋ ያለ ጥናት እንደሚያስፈልገው እና አሁን ግን ማንኛውም የማህበረሰብ ክፍል ህክምና ማድረግ እንዳለበት አቶ አብዱልጀባር አብደላ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን  ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ
#ዳጉ_ጆርናል




አንጋፋው የማሲንቆና በገና ተጫዋች አለማየሁ ፋንታ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

አንጋፋው የማሲንቆና በገና ተጫዋች፣ ድምጻዊና የሙዚቃ መምህር አለማየሁ ፋንታ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

ግጥምና ዜማ በመድረስና ክራር በመጫወት የሚታወቁት አለማየሁ ፋንታ፤ ለበርካታ ዓመታት በያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡

በተለየ የማሲንቆ አጨዋወታቸው የሚታወቁ ሲሆን፤ በዓለም ዙሪያ የኢትዮጵያን ባህል ማስተዋወቅ ችለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት የአለማየሁ ፋንታን ህልፈት አስመልክቶ ባስተላለፈው የሀዘን መግለጫ መልዕክት፤ ለኢትዮጵያ የሙዚቃ ማህበረሰብና ለመላው ሕዝብ ከባድ ሀዘን ነው ብሏል፡፡

በነገው ዕለት የአስክሬን ሽኝት መርሐ-ግብር ተደርጎ የቀብር ሥነ ሥርዓት እንደሚፈጸምም ተገልጿል፡፡

Via:- Fana

#ዳጉ_ጆርናል


የወረባቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪን ጨምሮ የወረዳዉ ፖሊስ ሃላፊዎች ተገደሉ

የወረባቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፈንታው ከበደ፣ የወረባቦ ወረዳ ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል ምርመራ ክፍል ኃላፊ እና ተወካይ የፖሊስ ጽ/ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር አድስ ዘመን ፍሰሃ እና ሹፌር አቶ ከበደ እንድሪስ ለመስክ ስራ በወጡበት በታጠቁ ፅንፈኛ ሃይሎች በደረሰባቸው ጥቃት ሕይወታቸው አልፏል ሲል የዞኑ መንግስት አሳዉቋል::

የዞኑ መንግስት "ፅንፈኛ ሀይሎች" ያላቸዉ አካላት ግድያዉን ፈጽመዋል ብሏል።

አመራሮቹ ለስራ በጉዞ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን መንገድ ላይ በደፈጣ ጥቃት ጠብቀው ገድለዋል ሲል በመግለጫው መጥቀሱን ዳጉ ጆርናል ተመልክቷል።

የዞኑ መንግስት እነዚህ ህይወታቸውን ያጡ አመራርና ባለሙያ የህዝብና የመንግስትን ተልዕኮ ለማስፈፀም ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ህብረተሰቡን በልማት እና በመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ለማድረግ ቀን ከሌት ሲተጉ የነበሩ ቅንና ታታሪ የህዝብ ልጆች ነበሩ ብሏል።

የዞኑ መንግስት በግድያዉ ህይወታቸዉን ላጡ ቤተሰቦቻቸዉ እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ተመኝቷል።

#ዳጉ_ጆርናል

20 last posts shown.