ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ:-
አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥር አራት በዚች ቀን የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚወደው የከበረና የተመሰገነ ወንጌልን የጻፈ የሐዋርያው ዮሐንስ የፍልሰቱ መታሰቢያ ነው::
አባቶቻችን ይህን ቅዱስ ዮሐንስን በተለያዩ ስሞች እንዲህ በማለት በዜማ ይጠሩታል። ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ፤ ዮሐንስ ሐዋርያ፤ ዮሐንስ ወንጌላዊ፤ ዮሐንስ ወልደ ዘብዴዎስ፤ ዮሐንስ ፍቁረ እግዚእ፤ ዮሐንስ አቡቀለምሲስ፤ ሰአል ለነ ከመ ንስማዕ ወንግበር ቃለ ወንጌሉ ለወልደ ማርያም ድንግል። ይላሉ ዘወትር በሰዓታቱ።
ለዚህም ቅዱስ ወደ እስያ ሀገር ይሔድ ዘንድ ዕጣው በወጣ ጊዜ እጅግ አዝኖ አለቀሰ:: እነርሱ ክፉዎች ከሀዲዎች ልባቸው የደነደነ መሆናቸውን አውቋልና:: ግን ከጌታችን ኃይልን መጽናናትን አግኝቶ ከደቀ መዝሙሩ ከአብሮኮሮስ ጋር ወጥቶ ወደ ክፍሉ ሔደ::
ወደ ኤፌሶንም ሊሔድ ወዶ በመርከብ ላይ ተሳፈረ:: መርከቡም ተሰበረ:: እየአንዳንዱ በመርከብ ስባሪ ሠሌዳ ላይ ተንጠለጠለ:: ደቀ መዝሙሩን አብሮኮሮስንም የባሕሩ ማዕበል ወደ አንዲት ደሴት አደረሰው:: ቅዱስ ዮሐንስ ግን በባሕሩ ማዕበል መካከል አርባ መዓልት አርባ ሌሊት ኖረ::
ከዚህም በኋላ ደቀ መዝሙሩ አብሮኮሮስ ወዳለበት ወደ የብስ ባሕሩ ተፋው:: ስለ መገናኘታቸውም እግዚአብሔርን አመሰገኑት:: በዚያም ጊዜ ተነስተው ወደ ኤፌሶን ከተማ ገቡ:: ግን በክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይሰብኩ ዘንድ አልተቻላቸውም እነዚያ ያገር ሰዎች እጅግ የከፉ ናቸውና::
ስለዚህ ምክንያት ፈጥረው ዮሐንስ ሮምና ለምትባል ሴት የውሽባ ቤት እሳት የሚያነድ ሆነ:: ረድኡ አብሮኮሮስም አጣቢ ሆነ:: ያቺ ሴትም እጅግ ታሰቃያቸው ነበር:: መጻተኞችም ስለሆኑ ታጎሳቁላቸዋለች:: ትደበድባቸዋለች:: ትረግማቸዋለች:: ባሮቿም እንደሆኑ ጽፈውላታልና ለእርሷ ባሮች አደረገቻቸው በዚህም በታላቅ ጉስቁልና ውስጥ ኖሩ::
ከዚህም በኋላ በአንዲት ዕለት ይታጠብ ዘንድ የአገር ገዥው ልጅ ገባ:: በዚያም የውሽባ ቤት ከተሠራ ጀመሮ የሰይጣን ኃይል አለ:: የመኰንኑንም ልጅ አንቆ ገደለው:: በዚያንም ጊዜ የአገር ሰዎች ለዚያ ለሞተው ሊያለቅሱለት ተሰበሰቡ:: የከበረ ዮሐንስም ከእርሳቸው ጋር መጥቶ እንደ ሰው ሁሉ ሊያይ በዛው ቆመ::
ሮምናም በአየችው ጊዜ ረገመችው አንተስ በጌታዬ ልጅ ሞት ደስ ብሎህ ልትዝትብኝ መጣህ አለችው:: ቅዱሱ ግን በቅንነት አይዞሽ አትዘኝ አላት:: ይህንንም ብሎ ወደ ሞተው ቀረብ ብሎ በመስቀል ምልክት አማተበበት:: በፊቱም ላይ እፍ አለበት:: በዚያንም ጊዜ ያ የሞተው ድኖ ተነሣ:: የአገር ሰዎችም ደነገጡ::
ሮምናም ወዮልኝ እግዚአብሔር የሚሉት አምላክ አንተ ነህን አለች:: እርሱም አይደለሁም እኔ አገልጋይ ሐዋርያው ነኝ እንጂ አላት:: በእነርሱ ላይ የሠራችውን በደል ሁሉ ይቅር ይሏት ዘንድ መሪር ለቅሶ በማልቀስ ሐዋርያትን ለመነቻቸው:: እነርሱም አረጋጓት አጽናኗትም::
ከሀገሩም ሰዎች ብዙዎቹ በክብር ባለቤት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አመኑ:: የክርስትና ጥምቀትንም አጠመቃቸው::
በፊታቸውም ብዙዎች የሆኑ ድንቆች ተአምራትን አደረጉ:: ይህንንም አይተው የሀገሩ ሰዎች ሁሉም በጌታችን አመኑ::
ከጣዖታቱ አገልጋዮች በቀር እነርሱም ሰይጣን በእርሱ ላይ ስለሚያነሣሣቸው ሊገድሉት ይሹ ነበር:: ነገር ግን ምርጦቹን እግዚአብሔር ጠበቃቸው::
የከበረ ዮሐንስም ሁሉንም እግዚአብሔርን ወደ ማወቅ እስከመለሳቸው ድረስ ታላቅ ድካምና ጭንቅ የሆነ መከራ ደረሰበት:: የከበረ ሐዋርያ ጳውሎስም ስለ ልቡናቸው ደንዳናነት ጣዖታትን ስለመውደዳቸው ስለ እነርሱ መስክሮአል::
እርሱም ዮሐንስ በታላቅ ድካም ወደ ቀናች ሃይማኖት መለሳቸው:: ከዚህም በኋላ ኤጴስ ቆጶሳትን ቀሳውስትን ዲያቆናትን ሾመላቸው::
ከዚህም በኋላ ከእስያ በዙሪያዋ ወዳሉ አገሮች ሁሉ ወጥቶ አስተማረ እግዚአብሔርንም ወደ ማወቅ መለሳቸው::
ይህም የከበረና የተመሰገነ ዮሐንስ በዚህ ዓለም ዘጠና ዓመት ኖረ:: እጅግም ሸመገለ:: ግን እንደ ባልንጀሮቹ ሐዋርያት በመሰየፍ ሞትን አልቀመሰም::
ስለ ድንግልናውን ስለ ንጽሕናው ይህ ሆነ:: ሁሉም በክብር ይስተካከሉ ዘንድ እርሱም ወንጌልን ቀለምሲስ የሚባለውን ራእይ ሦስት መልአክታትን የጻፈ ነው::
ራት ሲበሉ በጌታ ኢየሱስ አጠገብ የተቀመጠውና አቤቱ የሚያሲዝህ ማን ነው ያለው እርሱ ነው::
ጌታችንም በተሰቀለ ጊዜ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጋር በመስቀሉ አጠገብ የቆመ እናቱንም እንሆ ልጅሽ ያላት እርሱን ደቀ መዝሙሩን እንኋት እናትህ ያለው ነው::
ጴጥሮስም እርሱን ሲከተለው በአየው ጊዜ ስለርሱ ጌታ ኢየሱስን አቤቱ ይህስ እንዴት ነው ብሎ የተናገረ:: ጌታ ኢየሱስም እስክመጣ ድረስ ይኖር ዘንድ ከወደድኩ አንተ ምን አለህ አንተ ግን ተከተለኝ ያሉት ይህ ነው::
የተመሰገነ ዮሐንስም ከዚህ ዓለም የሚወጣበት ሰዓት እንደ ቀረበ በአወቀ ጊዜ ሕዝቡን ጠራቸው:: ጸሎትንም ጸለየና ኅብስቱን ባርኮ ቆረሰ ይህም የጌታችን ሥጋውንና ደሙን ሰጣቸው በቀናች ሃይማኖትም እንዲጸኑ አዘዛቸው:: ባረካቸው:: አጽናናቸውም::
ከዚህም በኋላ ደቀ መዝሙሩ አብሮኮስን ከወንድማቸው ሌሎች ሁለቱን መቆፈሪያ ይዘው ይከተሉት ዘንድ አዘዘ::
ከኤፌሶንም ከተማ ውጪ ወጣ ጉድጓድ እንዲቆፍሩም አዘዘ:: ከውስጥዎም ገብቶ ቆመ:: ልብሱንም አስወገደ:: ከአንድ የበፍታ ቀሚስ በቀር አላስቀረም እጆቹንም አንሥቶ ጸለየና ወደ ከተማ ይመለሱ ዘንድ አሰናበታቸው::
በክርስቶስም ሃይማኖት ይጸኑ ዘንድ ለሕዝቡ ይነግሩአቸው ዘንድ አዘዛቸው:: በጎ ሥራዎችንም ይሠሩ ዘንድ ጌታችን ለሁሉም እንደ ሥራው ይከፍለው ዘንድ አለውና::
ሁለተኛም እንዲህ አላቸው:: እኔ ከሁላችሁ ደም ንጹሕ ነኝ ከእግዚአብሔር ትእዛዝና ሕግ ሳልነግራችሁ የተውኩት ምንም ምን የለምና እናንተም ከእንግዲህ ከቶ ፊቴን አታዩኝም::
ይህንንም በተናገረ ጊዜ አለቀሱ እጆቹንና እግሮቹን ስመው በጕድጓድ ውስጥ ትተዉት ወደ መንደር ተመለሱና የሆነውን ሁሉ ለሰዎች ነገሩዋቸው:: ሁሉም ደንግጠው መጡ:: ግን ልብስና መጫሚያ እንጂ መቃብሩን አላገኙም:: እጅግም አደነቁ ደቀ መዝሙሩ ዮሐንስን በዚህ በጎ ዕረፍት ያሳረፈው እግዚአብሔርንም አመሰገኑት::
ለእግዚአብሔርም ምስጋና ይሁን እኛንም በዚህ በከበረ አባት በሐዋርያ ዮሐንስ ጸሎት ይማረን በረከቱም ከእኛ ጋር ትኑር ለዘላለሙ አሜን::
🇪🇹
@ethiopianorthodoxs⛪️⛪️