ላኩራዋ ፥ በናይጄሪያ ተጨማሪ ስጋት የደቀነው የሽብር ቡድን
-------------
ናይጄሪያ ላኩራዋ የተሰኘውን ታጣቂ ቡድን በሽብርተኝነት በመፈረጅ በመላ ሀገሪቱ እንዳይንቀሳቀስ አገደች።
ላኩራዋ ታጣቂ ቡድን ሙዚቃ የሚሰሙ ሰዎችን የሚገርፍ፣ ጥቃት የሚፈፅም እና በሰሜን ምዕራብ ናይጄሪያ እና ከኒጀር አዋሳኝ ድንበር አካባቢ ያሉ ነዋሪዎችን ዒላማ የሚያደርግ አዲስ ታጣቂ ቡድን መሆኑ ተገልጿል።
የናይጄሪያ ባለሥልጣናት እንዳሉት ላኩራዋ በማሊ እና ኒጀር ካሉ 'ጂሃዲስት ቡድኖች' ጋር ግንኙነት ያለው ሲሆን፤ ታጣቂዎቹ ለዓመታት በናይጄሪያ እና ኒጀር ድንበር ላይ ተቀምጠው የአካባቢውን ሴቶች ያገባሉ፤ ወጣቶችን ይመለምላሉ።
ይህም ከእስላማዊ ታጣቂ ቡድን ቦኮሃራም እስከ አጋች ወንበዴዎች እንዲሁም ከሌሎች በርካታ ታጣቂ ቡድኖች ጋር እየተዋጋች ላለችው ናይጄሪያ ተጨማሪ የደኅንነት ስጋት ሆኖባታል ተብሏል።
በዚህም የናይጄሪያ መንግሥት ሐሙስ ዕለት የቡድኑን ተግባራት በመዘርዘር በዋና ከተማዋ አቡጃ ለሚገኘው ከፍተኛ ፍርድ ቤት የክስ ሰነድ አስገብቶ ነበር።
ሰነዱ ላኩራዋ ከብቶችን መዝረፍ እና ለገንዘብ ሰዎችን ማገትን፣ ጠለፋን፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ ጥቃት መፈፀምን ጨምሮ በሽብር ተግባራት ላይ ሲሳተፍ መቆየቱን ያስረዳል።
ከዚህም በተጨማሪ ቡድኑ በአካባቢው የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ያጠፋ፣ ጉዳት እና የንብረት ውድመትን ያስከተለ ጎጂ የሆነ ርዕዮተ ዓለምን በማሰራጨት እና ነዋሪው ባለሥልጣናትን እንዳያከብር በማበረታታት ተከሷል ነው የተባለው።
ቡድኑ የተፈጠረው በሶኮቶ እና ኬቢ ግዛቶች ውስጥ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ ከጥቂት ዓመታት በፊት የነበረ ሲሆን የአካባቢው ሰዎች ለባለሥልጣናት ቢያሳውቁም የተሠራ ሥራ አልነበረም።
መጀመሪያ ላይ የላኩራዋ አባላት የአካባቢውን ማኅበረሰቦች ከታጣቂዎች እና ከከብት ዘራፊዎች እንደሚጠብቁ ቃል ገብተው እንደነበር ነው የተገለጸው።
ሆኖም የነዋሪዎችን ስልክ መፈተሽ እና በስልካቸው ላይ ሙዚቃ የጫኑ ሰዎች ሙዚቃውን ከማጥፋታቸው በፊት መግረፍ ሲጀምሩ ነገሮች እንደተባባሱ አንድ ግለሰብ ተናግሯል።
ለፍርድ ቤቱ በቀረበው ሰነድ ላይም የናይጄሪያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ እና የፍትሕ ሚኒስትሩ ላቴፍ ፋግቤሚ፣ የቡድኑ ድርጊቶች ለብሔራዊ ደኅንነት ከፍተኛ ስጋት ሆኗል ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የጦሩ ቃል አቀባይ ሜጄር ጀኔራል ኤድዋርድ ቡባ፣ የላኩራዋ ቡድን መፈጠር በጎረቤት ሀገራት ማሊ እና ኒጀር ካለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር በቀጥታ እንደሚያያዝ መናገራቸው ይታወሳል።
ጦሩ በእስላማዊ ሽምቅ ተዋጊዎች ግፊት ምክንያት በሁለቱም ሀገራት ተሰማርቶ ነበር።
ዳኛ ጀምስ ኦሞቶሾ ባሳለፉት ፈጣን ውሳኔም ቡድኑን የሽብርተኛ ድርጅት ብለው የፈረጁ ሲሆን ሌሎች ተመሳሳይ ቡድኖችም በመላ ሀገሪቱ በተለይም በሰሜን ምዕራብ እና ሰሜን ማዕከላዊ ክልሎች እንዳይንቀሳቀሱ የጣለውን እገዳ አራዝመዋል።
ይህ ውሳኔ የናይጄሪያ መንግሥት በቡድኑ ላይ ጠንካራ እርምጃ ለመውሰድ ሥልጣን ይሰጠዋል ነው የተባለው።
የፀጥታ ተቋማትም የቡድኑን እንቅስቃሴ የማደናቀፍ እና የማፍረስ ሰፊ ሥልጣን ያላቸው ሲሆን ይህም እስራትን፣ ክስ ማቅረብን፣ የንብረት እገዳን እና ክትትልን ይጨምራል።
ከዚህም በተጨማሪ በሽብር ከተፈረጀው ቡድኑ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ላይ መገለልን ሊያስከትል ይችላል።
በመላ ሀገሪቱ በተለይም በሰሜናዊ ናይጄሪያ በአውሮፓውያኑ 2000 መጨረሻ ላይ ብቅ ካለው ቦኮሃራም ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሁኔታ እንዳይፈጠር ነዋሪዎች ሰግተዋል።
ቦኮሃራም ማለት " የምዕራባውያን ትምህርት የተከለከለ ነው" ማለት ሲሆን በክልሉ እስላማዊ አገዛዝ ለመመሠረት በተደጋጋሚ ዓለማዊ ትምህርት ቤቶችን ዒላማ ያደርጋል።
ቡድኑ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 ከሰሜን ምሥራቃዊቷ ከተማ ቺቦክ ከ200 በላይ ሴት ተማሪዎችን አግቶ ከወሰደ በኋላ ስሙ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታውቋል።
https://t.me/Ethioplus_s