እስራኤል የመላ ጋዛ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲቋረጥ አዘዘችእስራኤል በመላው ጋዛ ሰርጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ሰጠች።
የአገሪቱ የኃይል ሚኒስትር ሐማስ ቀሪ ታጋቾችን እንዲለቅ ጫና ለመፍጠር በሚል ይህ እርምጃ እንደተወሰደ ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ ኤሊ ኮኸን ይህንን ያስተላለፉት እስራኤል ከሁለት ሚሊዮን በላይ ህዝብ በሚኖርባት ጋዛ ማንኛውንም የእርዳታ አቅርቦት ካቋረጠች ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው።
"ታጋቾቹን ለማስመለስ እንዲሁም በጦርነቱ ማግስት ሐማስ በጋዛ ውስጥ አለመኖሩን ለማረጋገጥ በእጃችን ያሉ ማንኛውንም መሳሪያዎች እንጠቀማለን" ሲሉ ኮኸን እሁድ ዕለት በቪዲዮ ባስተላለፉት መግለጫ ተናግረዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ በዋነኝነት ለግዛቲቷ ንጹህ መጠጥ አቅርቦት ወሳኝ በሆነው የጨዋማ ውሃ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ስራ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንደሚኖረው ተገልጿል።
የእስራኤል መንግሥት የውሃ አገልግሎት ሊያቋርጥ እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቷል።
ሚኒስትሩ በመግለጫቸው "ለጋዛ ሰርጥ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት በአስቸኳይ እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ፈርሜያለሁ" ብለዋል።
እስራኤል በጦርነቱ ወቅት ጋዛን በሙሉ ከበባ አስገብታ ኤሌክትሪክን ጨምሮ መሰረታዊ የሚባሉ አገልግሎቶችን ማቋረጧ ይታወሳል።
የጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት የመጀመሪያው ምዕራፍ ከአስር ቀናት በፊት የተጠናቀቀ ሲሆን ይህንን ያልጸና ስምምነት ለማራዘም የሚደረገው ውይይት በያዝነው ሰኞ በኳታር ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።
እስራኤል የመጀመሪያው ምዕራፍ የተኩስ አቁም ስምምነትን መራዘምን ሐማስ እንዲቀበል ትፈልጋለች።
ሐማስ በበኩሉ ሁሉም ታጋቾች እንዲለቀቁ እንዲሁም የእስራኤል ጦር ከጋዛ ሙሉ በሙሉ እንዲወጣ እና ዘላቂ መረጋጋትን ማምጣት ያለመው ሁለተኛው ምዕራፍ ተግባራዊ ይሁን እያለ ነው።
[
@MadoNews ]