ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ “አሞራው ካሞራ” ሲል ያዜመላቸው…
ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ ከሰሞኑ በለቀቀው የብዙዎችን ቀልብ በሳበው ነጠላ ዜማው “አሞራው ካሞራ” ሲል ያዜመላቸው ራስ አሞራው ውብነህ ተሰማ ማን ናቸው?
ግጥሞቹ ታሪካዊ ዳራ ያላቸው የአሞራው ውብነህ ተሰማን ታሪክና ጸባይ አብጠርጥረው የሚገልጹ ናቸው። ራስ አሞራው ውብነህ የፋሽስትን ጦር የሰማይ አሞራ ሆነው መቆሚያ መቀመጫ ያሳጡት ጀግና እንደነበሩ ታሪካቸው ያስረዳል።
ለዚህ ጀብዳቸው በሚመጥን መልኩ ድምጻዊ አስቻለው ፈጠነ “አሞራው ካሞራ” በተሰኘው ድንቅ የሙዚቃ ሥራው…
ያየም ሰው ይናገር የነበረም ያውጋ
ተጋጥሟል ይባላል አሞራው ከአሞራ
ጎንደር ጀግና ትውለድ ታሳድግ ፀንሳ
እንደአሞራው ውብነህ ስሙ ማይረሳ … ሲል ለጆሮ በሚስማማ ድምጹ ለጀግናው ይቀኛል። ታሪኩን እያነሳሳም ያወድሳል።
“አሞራው ውብነህ” ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም ፋሽስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት በምዕራብ በጌምድር ግዛት በተደረገው የፀረ-ፋሽስት ትግል ግንባር ቀደም መሪ ነበሩ።
ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ቆላማ አካባቢ የአርማጭሆ አውራጃ ተወላጅ የሆኑት ውብነህ ተሰማ ገና በ16 ዓመታቸው ነበር ትግል የጀመሩት።
በፋሽስት ኢጣሊያ ወረራ ወቅት በጎንደር በኩል ታላቅ ጀብዱ ከፈጸሙ ስመ ጥር አርበኞች መካከል ውብነህ ተሰማ አንዱ ናቸው። አገርንና ወገንን የሚወዱ፣ ከአገር የሚበልጥብኝ ነገር የለም በማለት ራሳቸውን ያሳመኑ እና ጸሎተኛም እንደነበሩ የልጅ ልጃቸው ገብርኤላ አድማሱ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ገልጸዋል።
ታዲያ ይህንን ሀገር ወዳጅ፣ አርበኛ እና ጸሎተኛ ባህሪያቸውን ጽምጻዊ አስቻለው ፈጠነ…
ያ የአርበኛው ምንጣፍ ያ ምጅምር ገጡ
የጦሩ መሳፍንት ፈሪሀ እግዜር ያለው
ከጦር መሀል ሲሄድ ይመስላል ክንፍ ያለው
አሞራው ከአሞራ … ሲል በተመጠኙ እና ውብ በሆኑ ቃላት ይገልጸዋል።
ልጃቸው ኢትዮጵያ ውብነህ ከፋና ቴሌቪዥን ጋር በነበራቸው ቆይታ ከነፃነት በኋላ እንግሊዞች ጎንደር ገብተው የራሳቸውን ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቅሉ የተመለከቱት ራስ አሞራው ውብነህ፤ በአገሬ ላይ የውጭ ሀገር ሰንደቅ ዓላማ አይሰቀልም በማለት የእንግሊዞችን አስገድደው አውርደው በምትኩ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንዲሰቀል ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
ከሱዳን ገዳሪፍ ተስቦ እንደ ሰርዶ
ኢትዮጵያን ሰቀላት ያን ሰንደቅ አውርዶ
የአበቅየለሽ ልጆች ዳር እስከዳር ኩሩ
ጎንደር ጀግና አታጣም አትጠራጠሩ … በማለት አስቻለው “አሞራው ካሞራ” በተሰኘው ሙዚቃ ላይ የተቀኘለትም ለዚሁ ነው።
አርበኛው ውብነህ ተሰማ ባለቤታቸውን ጨምሮ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረ ከመጣ ሀገር ወዳድ አርበኞች ጋር በዱር በገደል ስለተዋደቁ ፋሽስት ኢጣልያ በጌምድርን ተረጋግቶ መቆጣጠር ሳይቻለው ቀርቷል።
ራስ አሞራው ውብነህ በተወለዱ በ94 ዓመታቸው መስከረም በ1975 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ቀብራቸውም በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።
ድምጻዊው ስለግጥሞቹ ይዘት፣ በግጥሞቹ ውስጥ ስለተካተቱት ስሞች እና አጠቃላይ ስለ ታሪካዊ ዳራቸው አስተያየቱን ጠይቀነው አድማጭ እና ተመልካች በተረዳው ልክ እንዲተረጉመው፤ ለተደራሲያን ትችዋለሁ ከማለት በዘለለ ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥቧል።
ከሶስት ዓመታት በፊት በፋና ቴሌቪዥን በ#ፋና_ቀለማት የታላቁ አርበኛ ራስ አሞራው ውብነህ ተሰማ ታሪክ በልጆቻቸው አንደበት የተገለጸበትን ዝግጅታችንን ተከታዩን ማስፈንጠሪያ ተጭነው እንዲከታተሉ ጋበዝንዎት።
ማስፈንጠሪያው👇👇
https://www.youtube.com/watch?v=WWSnijy3a3c