ከእኔ አብ ይበልጣል
ብዙ አርዮሳውያን ሆነ ሙስሊም ወገኖቻችን ይህንን ጥቅስ መሠረት አድርገው ኢየሱስ ፍጡር ነው ከአብ ያንሳል ይሉናል። እስኪ እንቃኘው!
“የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ #ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር።”
— ዮሐንስ 14፥28
ክርስትና አንድ አምላክ ብቻ መኖሩን ቢያስተምርም ይህ አንዱ አምለክ ሦስት አካላት እንዳሉት ስለሚያስተምር በነዚህ አካላት መካከል የሥራ ድርሻ (function) ወይም የደረጃ (rank) ብልጫ ሊኖር ይችላል፡፡ ይህ በእግዚአብሔር በራሱ ሕላዌ ውስጥ የሚገኝ እንጂ ከእርሱ ውጪ የሚገኝ ባለመሆኑ በሥላሴነት ከሚኖረው ከአንዱ አምላክ ውጪ የሚገኝ አካል ብልጫ እንዳለው እስካልተነገረ ድረስ ምንም የሚፈጥረው ችግር የለም፡፡ በነዚህ ቦታዎች የተጠቀሰው μείζων(ሜይዞን) የሚለው የግሪክ ቃል ደረጃን እንጂ የግድ የባሕርይ ብልጫን የሚያመለክት አይደለም፡፡
ማሳያ አንድ፦ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከሴት ከተወለዱት መካከል እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያለ አልተነሣም፤ ሆኖም በመንግሥተ ሰማያት ከሁሉ የሚያንሰው #ይበልጠዋልμείζων[ሜይዞን]።
— ማቴዎስ 11፥11
ይህ ማለት በመንግሥተ ሰማይ ያለው አካል በባሕርይ ይበልጠዋል ማለትም በመንግሥተ ሰማይ ያለው ፈጣሪ ዮሐንስ ፍጡር ነው ማለት ማለት አይደለም። ሁለቱም ፍጡሮች ናቸውና ነገር ግን በሥራ ድርሻ የደረጃ ብልጫን ነው የሚያሳየው።
ማሳያ ሁለት፦“እውነት እላችኋለሁ፤ በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ ይሠራል፤ እንዲያውም እኔ ወደ አብ ስለምሄድ፣ ከእነዚህም #የሚበልጥ ሜይዞን[μείζων] ያደርጋል።”
— ዮሐንስ 14፥12
ይህም ማለት እኛ በባሕሪያችን ከክርስቶስ እንበልጣለን ማለት አይደለም።
በአጭሩ አንድ አካል ከሌላው በሥራ ድርሻ፣ በሥልጣን ወይም በደረጃ ይበልጣል ማለት የባሕርይ ብልጫ አለው ማለት እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ለምሳሌ ያህል የአንድ አገር መሪ በሥራ ድርሻ፣ በሥልጣንም ሆነ በደረጃ በስሩ ከሚተዳደሩት ዜጎች ይበልጣል፡፡ ይህ ማለት ግን እንደ ሰው ያለው ዋጋ (Value) ከማንም ይበልጣል ማለት አይደለም፡፡ ባል የቤተሰብ ራስ እንደመሆኑ መጠን ከላይ በተጠቀሱት መንገዶች ከሚስቱ ሊበልጥ ይችላል ነገር ግን ወንድ እንደ ሰውነቱ ከሴት ይበልጣል ወይም ሴት ከወንድ ታንሳለች ማለት ግን አይደለም፡፡ የግሪክ አዲስ ኪዳን የባሕርይ ብልጫን ለማመልከት “ዲያፎሮስ”[διάφορος] የሚል ሌላ ቃል የሚጠቀም ሲሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በባሕርዩ ከመላእክት የላቀ መሆኑን ለማመልከት ዕብራውያን 1፡4 ላይ ጥቅም ላይ ውሏል፡፡
ከመላእክት ይልቅ እጅግ የሚበልጥ ስምን በወረሰ መጠን እንዲሁ ከእነርሱ አብዝቶ #ይበልጣል[διαφορώτερον]።
— ዕብራውያን 1፥4
በሥላሴ አካላት መካከል የሚገኘውን ግንኙነት ለማመልከት ግን ይህ ቃል ጥቅም ላይ ውሎ አናገኝም፡፡ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አብ ከወልድ መብለጡ መነገሩ የመለኮታዊ ባሕርይ ብልጫን ሳይሆን የሥራ ክፍፍልን እና ወልድ ሥጋን በመልበስ መለኮታዊ ክብሩን ትቶ ወደ ምድር እንደመምጣቱ መጠን (ፈልጵስዩስ 2፡5-11) የደረጃ ብልጫን ብቻ የሚያመለክት በመሆኑ የኢየሱስን አምላካዊ ባሕርይ ከአብ የሚያሳንስ አይደለም፡፡
@mkc1933@mkc1933