በጋምቤላ ክልል በተከሰተ የአተት ወረርሽኝ፤ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ 136 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋልበጋምቤላ ክልል ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በተከሰተ የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት (አተት) ወረርሽኝ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
በክልሉ በአራት ወረዳዎች ላይ የተከሰተው ወረርሽኝ፤ መነሻው በአጎራባች ከሚገኙት የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች መሆኑንም የጤና ቢሮው ገልጿል።
የክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ወንድማገኝ በላይነህ፤ ወረርሽኙ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት በአኮቦ ወረዳ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
በአተት ወረሽኝ ለመጀመሪያ ጊዜ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠው በዘጠኝ ሰዎች ላይ ቢሆንም፤ ከአንድ ሳምንት በኋላ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 136 መድረሱን ኃላፊው አስረድተዋል።
በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች በአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት የሚያጋጥማቸው በመሆኑ በአተት መጠቃታቸው ይገልጽ እንጂ፤ የበሽታው ምልክቶች የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ትንታኔ በኮሌራ መያዛቸውን የሚያመለክት መሆኑን አቶ ወንድማገኝ አብራርተዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ወረርሽኙ ኮሌራ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ናሙና ወደ አዲስ አበባ አበባ መላኩንም አክለዋል።
“እኛ ከዚህ ወደ ኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ናሙና ልከናል። ትክክለኛ ኮሌራ ነው ብሎ ማረጋገጫ አላከልንም” ሲሉ አቶ ወንድማገኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በማስከትል፣ በሰውነት ውስጥ የሚገኝን ፈሳሽ አሟጥጦ በማስወጣት፣ አቅምን በማዳክም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው።
🔴 ለዝርዘሩ ▶️
https://ethiopiainsider.com/2025/15099/@EthiopiaInsiderNews