"አር ማረኝ"
~
ተውሒድን አጥብቀህ ተማር። ተውሒድ ለኣኺራ ብቻ አይደለም ፋይዳው። ለዱንያም መከበሪያህ ነው።
ተውሒድ ካልተማርክ
• ጉጉት ትፈራለህ፣
• አይጥ ትለማመጣለህ፣
• ውሻ አላዘነ ብለህ ትሸበራለህ፣
• የቁራ ድምፅ ከመንገድ ይመልስሃል፣
• እጅ ወይም አንገት ላይ በታሰረ እርባ ቢስ ክር ትተማመናለህ፣
• ዛፍ ላይ ክር ትተበትባለህ፣ ቅቤ ትቀባለህ፣
• እጅህን ስላሳከከህ ትደሰታለህ፣ (ሰዎች እጃቸውን ሲያሳክካቸው ምን እንደሚሉ አስታውስ።)
|
• ተውሒድ ካልተማርክ ከሶላት የተኳረፈ ገሪባ "ዐርሽ ላይ ነው የምሰግደው" እያለ ይጫወትብሃል። ጠንቋይና ወሊይ ይምታታብሃል።
• ሃያሉን ጌታ ጥለህ ሙታን ትማፀናለህ። (ይልቅ እነሱን መለመንህን ትተህ ለነሱ ዱዓእ አድርግላቸው።)
• ተውሒድ ካልተማርክ "ማርያም በሽልም ታውጣሽ"፣ "የማርያም መቀነት"፣ "የማርያም ፈረስ"፣ "ማርያም ስማህ ነው"፣… እያልክ ክርስትና ክርስትና የሚሸት ኹራፋት ታራምዳለህ።
• የአምስት ብር ጎመን የማያክል አረንጓዴ መርዝ (ጫት) መቶ ሁለት መቶ ብር ገዝተህ "የዱዓእ መሳሪያ" እያልክ ትጃጃላለህ።
• የሁለት አመት ህፃን "ካካ" ስትለው የሚፀየፈውን አፈር፣ "ቱራብ" እያሉ ከቀብር አካባቢ ቆንጥረው ሲሰጡህ በጥብጠህ ትጠጣለህ።
• አዎ ተውሒድ ካልተማርክ የተቀበረ ብር አገኛለሁ ብለህ ጠንቋይ እየቀለብክ በእጅህ ያለውን ገንዘብ ታጣለህ።
• ልጅህ ሲባልግ፣ ሲያፈነግጥ ዝም ብለህ ተውሒድ ሲማር፣ ሶላት ሲሰግድ፣ መስጂድ ሲያዘወትር፣ ጥሩ ጓደኛ ሲይዝ እሪ ትላለህ፣ (እንዲህ ነው የሸይጧን መጫወቻ መሆን።)
• ተውሒድ ካልገባህ ከሺርክ የሚያስጠነቅቁ ተቆርቋሪዎችን እንደ ጠላት እየቆጠርክና ጧት ማታ እያጠለሸህ ሶሐቦችን የሚያወግዙ፣ ቁርኣንን የሚያረክሱ ሺዐዎችን ታወድሳለህ። አልተማርክማ! እንዲሁ "ሲሉ ሰማሁ ብየ፣ እላለሁ ነብዬ" ብቻ!
• ተውሒድ ካልተማርክ ለቶንሲል ህመም "አር ማረኝ" እያልክ በአይነ ምድር ታሻርካለህ። ሰው እንዴት ካካውን ይማፀናል? ወላሂ ከእንዲህ አይነቱ ካካውን ዞሮ ከሚማፀን ጉደኛ ፍጡር፣ ካካውን የሚያቦካ የአእምሮ በሽተኛ ሺ ጊዜ ይሻላል።
ጎንበስ ብለህ ተውሒድህን ተማር። አካዳሚ ትምህርት ከሺርክ አያወጣህም። ስንት እንጨት፣ ላም፣ ድንጋይ፣ ሰው፣… የሚያመልኩ፣ ጠንቋይ ለጠንቋይ የሚርመጠመጡ ዶክተሮችና ፕሮፌሰሮች አሉ መሰለህ?
\=\
የቴሌግራም ቻናል
https://t.me/IbnuMunewor