#ፍትሕ
በሀገራችን በተደጋጋሚ ጊዜ ሴቶች ፣ ትንንሽ ህጻናት ሳይቀሩ ይደፈራሉ ፤ ይገደላሉ የሚሰጠው ፍርድ ግን " እውነት ፍርዱ ለማስተማር ነው ? ፍትሕ ለማስፈን ነው ? " የሚል ጥያቄ የሚያስነሳና እጅግ በጣም አስደንጋጭ ጭምር ነው።
ውድ የቲክቫህ ኢትዮጵያ ቤተሰቦቻችን ፥ መቼም ስለ ሚደፈሩ ሴቶች ፤ ደጉን ከክፉ ያለዩ ምንም የማያውቁ ህጻናት ሳይቀሩ ስለሚፈጸምባቸው አሰቃቂ ግፍና ወንጀለኞች ላይ ስለሚተላለፉት ፍርዶች ብዙ ጊዜ መረጃ ስንለዋወጥ መቆየታችን ይታወሳል።
ለአብነት በቅርብ ወራት እንኳን ፦
- " የ11 ዓመቷን ልጅ የደፈረው አባት 16 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ። "
- " አንገቷን አንቆና አፏ ውስጥ ጨርቅ ጠቅጥቆ የ14 ዓመቷን ልጅ የደፈረው እና ሕይወቷ እንዲያልፍ ያደረገው ግለሰብ በ19 ዓመት ተቀጣ። "
- " የ5 ዓመቷን ህፃን የደፈረው የ17 ዓመት ወጣት በ6 ወር እስር ተቀጣ። "
- " የ10 አመቷን ህፃን ልጅ አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ በ14 ዓመት ፅኑ እስራት ተቀጣ። "
- " የ4 አመቷን ህጻን አስገድዶ የደፈረው ግለሰብ በ17 ዓመት ጽኑ እስራት ተቀጣ። "
- " የ8 አመት ህፃናትን አስገድዶ የደፈረው የ41 አመት ጎልማሳ በ10 አመት ፅኑ እስራት ተቀጣ። "
- " እጅግ አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታ ሁለት የ16 እና የ17 ዓመት ልጆቹን በአልኮል አደንዝዞ አስገድዶ የደፈረው አባት በ21 አመት ተቀጣ። "የሚሉ እነዚህን መረጃዎች በቲክቫህ ገጻችሁ ላይ አንብባችኋል።
ይኸው ዛሬ ደግሞ ጆሮን ጭው ፤ ልብን ቀጥ የሚያደርግ የባህር ዳሯን የ7 ዓመት ህጻን ሔቨንን ጉዳይ ሰማን።
ህጻን ሔቨን ላይ እጅግ አሰቃቂ የመድፈር እና የግድያ ወንጀል የፈጸመው ግለሰብ 25 ዓመት እንደተፈረደበት ተሰማ።
ጭራሽ ይህም እንዳይሆነ የግለሰቡ ቤተሰቦች፣ ጎረቤቶች ፣ አንዳንድ የፖሊስ አባላት ፣ ከፍትህ አካላት ጭምር ጥረት ሲያደርጉ ነበር።
በሔቨን ጉዳይ በርካቶች ልባቸው ተሰብሯል ፤ ተቆጥተዋል። የመንግስት አካላትም ስለ ጉዳዩ ፊት ለፊት ወጥተው ተናግረዋል።
እናት የፍትሕ እያለች ነው። ለፍትሕ እያነባች ነው።
የግለሰቡ ቤተሰቦችም #እህቱን ጨምሮ ስራ የምትሰራበት ቦታ ድረስ ተከታትለዋት መቀመጫ መቆሚያ አሳጥተዋት ስራ እንድትልቀ አድርገዋል።
ከፍርዱ በፊትም ብዙ ማስፈራሪያ ሲደረግባት ነበር። ኃላም እንደዛው።
ማስፈራሪያ እና ክትትሉ ብዙ ጊዜ ቤት እንድትለቅ አድርጓታል።
ዛሬም ለቅሶ ላይ ናት። እናት ዛሬም የፍትሕ ያላህ ትላለች።
" የት እንሂድ እንግዲህ ? ወይ ሌላ ሀገር የለን ? ለማን እንናገር ? ማንስ ይሰማናል ? የእውነት አምላክ እሱ ይፍረድ ነው " ቃሏ።
የሔቨን ጉዳይ የብዙዎች ነው።
የእናቷ አንባ የብዙዎች ነው።
ስንት እናቶች ናቸው ይሁኑ እውነተኛ ፍርድና ፍትሕ አጥተው ቤታቸውን ዘግተው እያለቀሱ ያሉት ?
መሰል ጉዳዮች ሰሞነኛ ጉዳይ እየሆኑ እያለፉ ነው።
አንድ ሰሞን ይወራል ከዛ ይተዋል። በቃ ሊባልና መፍትሄ ሊፈለግ ይገባል።
የወንጀለኞቹ መታሰር የልጆቻችንን ህይወት እንኳ ባያስመልስም ትክክለኛ ፍርድ ግን ቢያንስ እንባ ያብሳል። ሌላውን ያስተምራል። አሁን እየሆነ ያለው ያ አይደለም።
ፍትሕ ይስፈን !
አስተማሪና ሀቀኛ ፍርድ ይፈረድ !
ፍትሕ ! እውነተኛ ፍትሕ ለተነፈጉ በርካታ ሴቶች፣ እናቶች ፣ ህጻናት !
#TikvahEthiopia⚖
@tikvahethiopia