ዩኤስኤድ በኢትዮጵያ በ5 ቢሊየን ብር የሚተገበር የአደጋ ሥጋት አመራር ፕሮግራም ይፋ አደረገ! የአሜሪካ አለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤድ) በኢትዮጵያ 9 ክልሎች የሚተገበርና 5 ቢሊየን ብር ድጋፍ የተደረገበትን የአምስት ዓመት የአደጋ ሥጋት አመራር ፕሮግራም በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ ይፉ የተደረገው ይህ ፕሮግራም፤ በአሜሪካ መንግሥት በሚገኝ የ49 ሚሊዮን ዶላር ወይንም ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የሚተገበር ሲሆን፤ በኢትዮጵያ በሚገኙ 9 ክልሎችና 120 ወረዳዎች ላይ ከ14 ሚሊዮን በላይ ሕዝቦችን ማዕከል አድርጎ እንደሚሰራ ተነግሯል፡፡
የድርጅቱ በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ድጋፍ ቢሮ ምክትል ዳይሬክተር ሄኖክ ሁንበላይ፤ ለፕሮግራሙ የ5 ዓመታት ጊዜ መያዙን ገልጸው፤ ሦስት መሰረታዊ ትላልቅ አላማዎች በውስጡ መያዙን ለአሐዱ ተናግረዋል፡፡
እነርሱም አንደኛ የአገሪቱ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ሥራዎች በተፋጠነ እና በተቀላጠፈ መልኩ በተሻለ ዝግጁነት እንዲሰሩና ከአሁን በፊት በተደረጉ ሥራዎች ላይ ተመስርቶ የተሻለ ትንበያ እንዲሁም የአደጋ ምላሽ እንዲሰጥ ማስቻል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ በየክልሎቹ ያሉ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ተቋማትን አቅም የማጎልበት ሥራ ነው ብለዋል፡፡
በሦስተኛው ደረጃ ደግሞ የግሉ ዘርፍ አደጋ ከተከሰተ በኋላ ሳይሆን፤ አደጋ ከመከሰቱ በፊት አስተዋጽዖ እንዲያደርግ ማስቻል እና ማስተባበር የፕሮግራሙ ዋና አላማዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በየክልሎቹ የሚገኙ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽኖች የተሻለ የአደጋ ትንበያ እንዲሰጡ፣ ያላቸውን ሀብትና ሌሎች ግብዓቶችን በአግባቡ እንዲጠቀሙ እንዲሁም አደጋው ችግር ከማስከተሉ በፊት ከማህህረሰቡ ጋር እንዲሰሩ የሚያደርግ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እንደሚሰሩም አቶ ሄኖክ አስረድተዋል፡፡
በዚህም መሰረት ፕሮግራሙ የሶማሌ ክልል፣ የደቡብ ክልል፣ የአፋር ክልል፣ የኦሮሚያ ክልል፣ የአማራ ክልል፣ የትግራይ ክልል፣ የደቡብ ምእራብ እና ማዕከላዊ ደቡብ ክልሎችን ማዕከል አድርጎ እንደሚሰራ የገለጹ ሲሆን፤ በዚህም እንደየክልሎቹ የአደጋ ተጋላጭነት የክልሎቹን አቅም የመገንባት ሥራ ይሰራል ሲሉ ለአሐዱ ገልጸዋል፡፡
የአሜሪካ አለም አቀፍ የተራድኦ ድርጅት በዚህ ፕሮጀክት ከፌደራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን፣ ከገንዘብ ሚኒስትር እንዲሁም ከሌሎች የመንግሥት አካላትና የልማት አጋር ድርጅቶች ጋር በትብብር እንደሚሰራ የገለጹት ምክትል ዳይሬክተሩ፤ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበርን ጨምሮ ሦስት አለም ዓቀፍ እና የአገር ውስጠ ተቋሟት ፕሮግራሙ በማስፈጸም ደረጃ አብረው እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
ይህ ድጋፍ በአደጋ ሥጋት አመራር ዘርፍ በዩኤስኤድ እስካሁን ከተደረጉ ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፤ በዚህም ምክንያት ፕሮግራሙ በአግባቡ ተግባራዊ ስለመደረጉ ትልቅ አጽዕኖት ተሰጥቶበት የቁጥጥር ሥራ እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡
Via Ahadu
@YeneTube @FikerAssefa