+"+ በስመ አብ: ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ: አሐዱ አምላክ
+"+ *" አዝማሪነትን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን ከተተው?! "*
[አዝማሪነት]
=>'አዝማሪ' የሚለውን ቃል የግዕዙ ልሳን 'መዓንዝር' ይለዋል:: በዚህ ተግባር ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች ከክርስቶስ ልደት በፊትም ሆነ በሁዋላ እንደ ነበሩ ይታመናል:: ይህ ተጥባበ ሥጋዊ ሙያ ከኢትዮዽያ ውጪ እንደ ነበረ የተለያዩ ጽሑፎች ያሳያሉ::
¤ለምሳሌ:- ቅዱስ ዮልዮስ በጻፈው ዜና ሰማዕታት በ3ኛው መቶ ክ/ዘመን አዝማሪዎች በሶርያ (አንጾኪያ)ና በግብጽ እንደ ነበሩ ያሳያል:: በጊዜው አዝማሪዎቹ ነገሥታቱንና ጣዖታቱን ያገለግሉ ነበር:: ብዙዎቹም ክርስትና ስቧቸው ይሕንን ሥጋዊ ተግባር ትተው ለሰማዕትነት በቅተዋል::
¤በሃገራችን በኢትዮዽያ ደግሞ መቼ እንደ ጀመረ በውል ባይታወቅም ረዥም ጊዜን ያሳለፈ ተጥባበ ሥጋ መሆኑን መገመት ይቻላል:: በተለይ ደግሞ ከ17ኛው መቶ ክ/ዘመን (ከጐንደር ዘመን) ጀምሮ በሰፊው እንደ ነበረ የታሪክ መዛግብት ይናገራሉ::
¤ወደ ዋናው ጉዳያችን እንመለስ ዛሬ ስለዚህ ጉዳይ የጻፍኩት ስለ አዝማሪነት ለማውራት አይደለም:: ይልቁኑ አቶ ሠርጸ ፍሬ ስብሐት (መጠሪያ ማዕረግ ካላቸው ይቅርታ): እርሳቸውን ጨምሮ አንዳንዶች ዘፈንን (ዘፋኝነትን) ወደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለመቀላቀል የቆረጡ ይመስል "አዝማሪነት ምንጩ ከቅዱስ ያሬድ ነው:: ዘፈን ኃጢአት አይደለም" እያሉ በየመድረኩ መስበካቸውን ቀጥለዋል::
¤ይህንን እያሉ ያሉ ሰዎች ዓላማቸው ምንም ይሁን እኛ ኦርቶዶክሳውያን ነገሮችን ልብ ብለን እንድንረዳ ያስፈልጋል::
1ኛ.አዝማሪነትን ከቅዱስ ያሬድ ጋር ማገናኘት ሰይጣናዊ ሃሳብ ነው::
¤ምክንያት:-
አዝማሪነት መሣሪያው (መሰንቆ) የወጣው በእርግጥ ከቤተ ክርስቲያን ነው:: ዜማውም ቢሆን ከነባሩ የቤተ ክርስቲያን ዜማ አፈንግጦ የወጣ ነው::
¤ምንም እንኩዋ 2ቱም በዚህ መንገድ ቢወጡም ቤተ ክርስቲያን ምንጫቸው እንደ ሆነች አስመስሎ መናገሩ ተገቢ አይደለም:: ድርጊቱ (ተጥባበ ሥጋው) ከዋናው አፈንግጦ የወጣበትን መንገድ ልንናገር ይገባል እንጂ ሥጋዊውን ነገር ከመንፈሳዊው: ምድራዊውን ከሰማያዊው: የጽድቅን ሥራ ከኃጢአት ተግባር ልንቀላቅል አይገባም::
¤ልክ አርዮስ: ንስጥሮስና መቅዶንዮስን የመሰሉ መ++ና+ፍ+ቃ++ን ከቀናችው ቤት ስለ ወጡ እነርሱን የወቅቱ ቤተ ክርስቲያን አንድ አካል አድርጐ መጥራት እንደማይቻለው: የያዙትም ነገር በቤተ ክርስቲያን ፍጹም የተወገዘ እንደ ሆነ ሁሉ አዝማሪነትም የኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን አካልና የተፈቀደ ነገር ማስመሰሉ የማይገባ ብቻ ሳይሆን ቅድስቷን ቤት የመገዳደር ያህልም የሚቆጠር ነው::
¤አዝማሪነት ምድራዊ ጉዳይ ነው:: ዛሬ ዛሬ አመሻሽ ላይ "አዝማሪ ቤት" እያለ በኃጢአት ሕይወት ውስጥ የሚዋኘውን ትውልድ ልንታደገው እንጂ ወደ ጨለማው ድርጊት ልንገፋው አይገባም::
*" ዘፋኝነትና ውጤቱ "*
=>በቅርብ ከሰማናቸው ነገሮች አንዱ ደግሞ "ዘፈን ኃጢአት አይደለም" የሚሉ ደፋሮችን ነው:: ሰው በእድሜ ከቆየ የማይሰማው ነገር የለምና ዛሬ ይህንንም ሰማን:: ¤አቶ ሠርጸን ጨምሮ ብዙ ዘፋኞች "ዘፈንን የሚከለክል ጥቅስን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥቀሱልን" ይሉናል:: (ገላ. 5:19) ያለውን ቃልም በተጥባበ ሥጋ ፍልስፍናቸው ሊተረጉሙልን ይታትራሉ::
¤ቆይ እኔ የምለው "ጫት አትቃሙ: ሲጋራ አታጭሱ: አጸያፊ ፊልሞችን አትዩ" የሚል ቃል (በጥሬው) መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይኖር ይሆን? ስለዚህም ለትውልዱ ጫትና ሲጋራን ቤተ ክርስቲያን ትፍቀድ? ኸረ ጉድ ነው!
¤መጽሐፍ ምን ይላል:- "እመቦ ዘይቴክዝ ለይጸሊ: ወእመቦ ዘተፈሥሐ ለይዘምር - ያዘነ ሰው ቢኖር ይጸልይ: ደስ ያለው ደግሞ ይዘምር" (ያዕ. 5:13) እነዚህ ስሜቶች በአንድ ክርስቲያን ላይ እየተፈራረቁ ነግሠውበት ይኖራሉ::
¤በተረፈው ግን ጾም: ስግደት: ምጽዋት . . . የመሳሰሉ ምግባራትን ይዞ ይኖራል እንጂ ክርስቲያን በፍጹም አይዘፍንም:: በዚያውስ ላይ "አትዝፈኑ" የሚል ቃልን ጥቀሱ ከማለት "ዝፈኑ" የሚል ቃል ካለ ቢጠቅሱልን የተሻለ ነበር::
¤(መዝ. 150:4) ላይ "ሰብሕዎ በትፍስሕት" የሚለው "በደስታ: በሐሴት" በመባል ፈንታ "በዘፈን" ተብሎ በ66ቱ ላይ ተተርጉሞ ነበር:: አሁን ግን እርሱ በሊቃውንት ማስተካከያ ተሰጥቶታል::
¤በተረፈ "ቅዱስ ዳዊት በታቦተ ጽዮን ፊት ዘፍኗል" (ዜና. 15:29) ለሚሉ: አዎ! በእርግጥ ዘፍኗል:: "ለምን?" የሚለው ሐተታ ይቆየንና አንድ ነገርን እናንሳ::
¤ክብር ይድረሰውና አባታችን ቅዱስ ዳዊት አንድ ቀን ወደ ደብተራ ገብቶ: ሊበላው ያልተፈቀደለትን ነገር በልቶ (ስለራበው ነው) በደል ሆኖ አልተቆጠረበትም ሲል ጌታ ተናግሯል:: (ማቴ. 12:3) ቅዱሱ ኃጢአት ሆኖ አልተቆጠረበትም ማለት እኛ ያንን ማድረግ እንችላለን ማለት አይደለም::
¤በዚያውስ ላይ እነርሱ (የብሉይ ኪዳን አበው) ያደረጉትን ሁሉ ማድረግ ካማረን እጅግ አስቸጋሪ ነው:: ለምሳሌ ብዙዎቹ አበው ከአንድ በላይ ሚስቶች ነበሯቸው:: እና እኛም እንደዛ እናድርግ? ይከብዳል!
¤ዋናው ነገር ፈቃደ ሥጋችንን ለመፈጸም ጥቅስ መጥቀስም ሆነ በብሉይ ኪዳን አባቶች ማመካኘቱ ፍትሐዊ አይደለም::
¤በመጨረሻ የመዝሙርና የዘፈን የሙዚቃን መሠረታዊ ልዩነት እንመልከት:: መዝሙርና ዘፈንን ለማገናኘት ሲባል 2ቱም በእንግሊዝኛው (በላቲኑ) "Music" መባላቸውን አንስተን ባንሞኝ አስቀድሜ እመክራለሁ:: ¤በልዩነት ደረጃ ግን እነዚህን እናንሳ:-
1.የዜማ ልዩነት (የመዝሙር ዜማ ከእግዚአብሔር ሲሆን የዘፈን ደግሞ ከዓለም [ከሰይጣን] ነው)
2.የዘፈን ተመስጦ ሰውን ወደ ኃጢአት ሲስበው የመዝሙር ግን ወደ ንስሃ ይስበዋል::
3.የዘፈን ይዘቱ በምድራዊ ቃላት (የሴትና የወንድን አካል በማሞገስ: ለዝሙት በመቀስቀስ) የተሞላ ሲሆን የመዝሙር ይዘቱ ቃለ እግዚአብሔር ብቻ ነው:: (ዘፋኝነት የዝሙት መሠረት ነው)
4.በመሣሪያ ደረጃም የዘፈን (ዘመናዊ) መሣሪያዎች ከተረሠሩበት አላማ ጀምሮ ሙሉ ነገራቸው ሥጋዊ ነው:: ሰሪዎቻቸውም የዚህ ዓለም ማሠሪያ የጠለፋቸው ናቸው::
¤የመዝሙር መሣሪያዎች ግን ከፈጣሪ የታዘዙ (መዝ. 150:1) ሲሆኑ ሰሪዎቻቸውም ቅዱሳን ናቸው:: ምናልባት እነዛን መሣሪያዎች የሰጠ በዘመኑ ለሚኖሩ ሰዎች ነው ካልን አምላክን አላዋቂ ማስመሰል (ሎቱ ስብሐት!) ነው:: ምክንያቱም ከዛ በሁዋላ በሌላ ዓይነት መሣሪያዎች ተጠቀሙ ብሎ አልተናገረምና::
¤ዋናው ልዩነታቸው ደግሞ ዓላማቸው ነው:: ዘፈንም ሆነ ዘፋኝነት ዓላማው ምድራዊ ሲሆን መጨረሻውም ኃጢአት ነው:: መዝሙር ግን ዓላማው ሰማያዊ: ፍጻሜውም የእግዚአብሔርን ርስት መውረስ ነው::
>
¤ስለ ዘፈን ኃጢአትነት እና ስለ ዘፋኝነት ውጤት ገድለ አዳምን: ድርሳነ ዮሐንስ አፈ ወርቅን: ትርጉዋሜ ኦሪትን መመልከት እንችላለን::
"ታላቁን ቅዱስ መጥምቁ ዮሐንስን ያስገደለች ወለተ ሔሮድያዳ ዘፋኝነቷ ያተረፈላት ቅዱሱን ማሳረድና ለራሷም መቀሰፍን ብቻ ነውና ወደ ልባችን እንመለስ::" (ማር. 6:21)
"ዘፈን የጣዖት መስዋዕት ነው::" (ዘጸ. 32:6)
"እግዚአብሔርን አመስግኑ: መዝሙር መልካም ነውና" (መዝ. 146:1)
Dn Yordanos Abebe
2008
https://t.me/zikirekdusn