ድንቅ አስተማሪ ታሪክ
ባለ ተሪኳ የአክስቴ ልጅ ነች፡፡ ከወራት በፊት ለስራ ጉዳይ ወደ መሃል ሀገር ሄጄ ከሷ ቤት አረፍኩ፡፡
እንደተለመደው ስንጫወት፥ አንድ ቀን ከእሷ ጋር ስለ ሶደቃ ጥቅም እየተዋወስን ነበር፡፡ ሶደቃ የአላህን ቁጣ እንደምታበርድና በአላህ ፈቃድ አደጋ እንደምትከላከል እየነገርኳት... በመሀል ሳላስበው ጣፋጭ ታሪኳን ነግራ ትልቅ ትምህርት አስተማረችኝ፡፡
"ታናሹ ልጄ "አኒ" በልጅነቱ አይኑን ታሞብኝ ነበር.." ብላ ታሪኳን ታጫውተኝ ጀመር፡፡ ታሪኳን ቀጥላለች...
"ህፃን እያለ አንድ አይኑ ላይ ነጭ ነገር ወጥቶበት ነበር፡፡ እንደሚታወቀው ባለቤቴ ስራው ክ/ሀገር ስለነበረ፥ ብዙ ጊዜ ለወራት ከልጆቼ ጋር ነበር የማሳልፈው፡፡
ታድያ አንድ ቀን የትንሹን ልጄን አይን ተመልክቼ፤ አንድ አይኑ ላይ የወጣበት ነጭ ነገር በጣም አስጨነቀኝ፡፡ ልጄ ሲያድግ ይህ ነገር እየሰፋ አይኑን ቢያሳጣውስ?
ህጻናት ጓደኞቹ በአይኑ ምክንያት ቢያሸማቅቁብኝስ?.. እያልኩ በመሳሰሉት ክፉ ሀሳቦች ተጨናነቅኩኝ፡፡
ወስጄ ላሳክመው አሰብኩና ለቤት ወጪ ከተሰጠኝ ሳንቲም በእጄ የቀረው ትንሽ ገንዘብ ነበር የቀረኝ፡፡ እሷን አንስቼ ልጄን አለርት(Alert) ሆስፒታል ልወስድ ፈለኩ፥ ግን ደግሞ በእጄ ያለችው ሳንቲም ትንሽ ስለሆነች በኋላ ደግሞ ለቤት ወጪ ቸግሮኝ ልጆቼን እንዳላስርብ ብዬ ከራሴ ጋር ሙግት ገጠምኩኝ፡፡
ሲጨንቀኝ በመሃል ክ/ሀገር ላለችው እናቴና ወንድሜ ደውዬ ስለ ተፈጠረው ችግር ነግሬአቸው ዱዓ አድርጉልኝ አልኳቸው፡፡ አሁንም ቀልቤ አልተረጋጋም፥ ባደርኩ ቁጥር ሁሌም ያሳስበኝ ጀመር፡፡
አስታውሳለሁ ጁምዓ ቀን ላይ ሆኜ ነበር፤ ምንም ቢቸግረኝ ይቸግረኝ እንጂ ሰኞ ልጄን አለርት ወስጄ አሳያለሁ ብዬ ወሰንኩ፡፡
ወዳው አንድ የዘነጋሁት ሁሌም በጣም በቅርቤ ያለ ረዳት ታወሰኝ፡፡ አላህን አስታውሼ በደንብ ዱዓ አደረኩ፡፡ ያቺ ቀን ብሩኳ ጁምዓ ቀን ስለነበረች ወዳው ሶደቃ መሰደቅ ፈለኩኝ፡፡ ንያ አድርጌ ባቅሜ ለመሰደቅ ዳቦ ደፋሁ፡፡ ቀን ላይ ደቦውን ይዤ ችግረኛ ናቸው የምላቸውን ገበያ አካባቢ የሚቀመጡትን ሰዎች እየዞርኩ ዳቦ አስያዝኳቸው፡፡ እነሱም ሳይንቁ ተቀብለው፣ መርቀውና መራርቀው ሸኙኝ አልሃምዱሊላህ፤ እኔም በጣም ደስ እያለኝ ወደቤት ተመለስኩ፡፡ ጁምዓን በዱዓና በሶደቃ አሳለፍኩ ማሻአላህ፡፡
ጁምዓን አድሬ ቅዳሜ ጠዋት እንደ ልማዴ ልጆቼን ላጣጥብ አወጣሁአቸው፡፡ ትንሽዬውን ልጄን እያጠብኩ ድንገት ያንን አይኑን ተመለከትኩና ደነገጥኩ!
አይኑን ትኩር ብዬ አየሁት፤ አይኑ ላይ ምንም ነጭ ነገር ማየት አልቻልኩም፡፡ ከአይኔ ነው ብዬ በድጋሚ ፈለኩት ግን አላገኘሁትም፡፡ ማመን ስላልቻልኩ አይኑን ተሳስቼ ይሆናል ብዬ ሌላኛው ደህነኛው አይኑ ላይ መፈለግ ጀምርኩ፤ እሱም ንጹህ ነበር፡፡ በደስታም በድንጋጤም ሆኜ ልጆቼን መታጠብያው ላይ ጥዬ እየሮጥኩ ወደ ቤት ገባሁ፤ ተመልሼም በፍጥነት እየወጣሁ ተመላለስኩ፡፡
ከዛም ወደቤት ገብቼ ለአላህ ሱጁድ ወድቄ አለቀስኩ፡፡ "ለካ ከሃኪሞች ሁሉ በላጭ ሀኪም አንተ ከቅርቤ ነው ያለኸው!" እያልኩ ከእንባ ጋር እየተደነቅኩም እያመሰገንኩም ሰገድኩለት፡፡
ምን እንደተፈጠረ ለኔ ግልጽ ሳይሆን አላህ ልጄን ፈወሰልኝ፡፡
ሰኞ ሆስፒታል ልሄድ ጁምዓ ሰድቄ፣ ዱዓ አስደርጌና አድርጌ አላህ በጥበቡ ቅዳሜ ጠዋት ላይ ልጄ ተፈውሶ እንዳየው አደረገ፡፡
ከዛማ በቃ በደስታ ለእናቴና ለወንድሜ ደውዬ አኒ እኮ ተሻለው፤ ያ ነገር ጠፋለት አልኳቸው፡፡ ሆስፒታል እንዳልወሰድኩት ስነግራቸው በጣም ተገረሙ፡፡ በተለይ ወንድሜ አሁን ድረስ ከአመታት በኋላም "እንዴት?" እያለ ይጠይቃል፡፡..."
___\\
የታሪኩ ጭብጥ፥ ሶደቃ የአላህን ቁጣ ታበርዳለች፤ በላእንም ታነሳለችና በሶደቃ እንበርታ እንሰድቅ ነው፡፡
@Abu_Mussaab