የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በዲላ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ገበታቸው የተነጠሉና ወደ ዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ የተከለከሉ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች በአፋጣኝ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡
ጠቅላይ ምክር ቤቱ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዲላ ዩኒቨርሲቲ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሒጃብ በመልበሳቸው ከትምህርት እንደታገዱ ትናንት ምሽት ባወጣው መግለጫ ገልጿል።
ጠቅላይ ምክር ቤቱ ከኢስላማዊ አለባበስ ጋር በተያያዘ ሙስሊም ሴት ተማሪዎች የሚደርስባቸውን ከፍተኛ ጫናና ከትምህርት መፈናቀል በዘላቂነት መፍትሔ እንዲያገኝ በዚህ ወር ብቻ ሦስት ጊዜ ለትምህርት ሚኒስቴር ደብዳቤ ቢፅፍም እስካሁን ተገቢ ምላሽ አለማግኘቱን አስታውሷል፡፡
ይልቁንም "ከጥር 11/2017 ዓ.ም ጀምሮ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ኢስላማዊ አለባበስ ስለለበሱ ብቻ ትምህርት እንዳይማሩ እንደተከለከሉ" የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጥር 14 ቀን 2017 ዓ.ም ለጠቅላይ ምክር ቤቱ በጻፈው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡
በመሆኑም እነኚህ በዲላ ዩኒቨርሲቲ ከትምህርት ገበታቸው የተነጠሉና ወደ ዩኒቨርስቲው ቅጥር ግቢ እንዳይገቡ የተከለከሉ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች በአፋጣኝ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ትምህርት ሚኒስቴር አስተዳደራዊ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
ዲላ ዩኒቨርሲቲ እንዲሁም ትምህርት ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ የሚሉትን የምናደርሳችሁ ይሆናል፡፡
@tikvahuniversity