Postlar filtri


የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ያሻሻለው ህገ መንግስት “ተፈጻሚ እንዳይሆን”፤ ለሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታ ቀረበ 

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የዛሬ ሁለት ሳምንት ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው ላይ ያጸደቀው የክልሉ ህገ መንግስት ማሻሻያ፤ “የኢፌዲሪን ህገ መንግስት የሚቃረን ነው” ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት “ተፈጻሚ እንዳይሆን” አቤቱታ አቀረቡ።

የምክር ቤት አባላቱ አቤቱታቸውን ያቀረቡት ለፌደራል የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ነው። የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ፤ በተለያዩ አካላት የሚቀርቡለትን ሕገ መንግስታዊ ጉዳዮችን የማጣራት ስልጣን ያለው ነው።

ጉባኤው በሚያደርገው ማጣራት መሰረት ህገ መንግስቱን መተርጎም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለፌደሬሽን ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ ያቀርባል። አጣሪ ጉባኤው፤ በተሻሻለው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት ላይ ትርጓሜ የሚጠይቅ አቤቱታ እንደቀረበለት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል።

ይህን አቤቱታ በትላንትናው ዕለት ያቀረቡት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የቦሮ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ተመራጭ የሆኑት አቶ አመንቴ ገሺ፣ አቶ ዮሐንስ ተሰማ እና ተስፋሁን ኪሉ ናቸው። ሶስቱ የቦዴፓ የክልል ምክር ቤት ተመራጮች የህገ መንግስት ትርጉም ከጠየቁባቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ የክልሉን ምክር ቤት መቀመጫ ቁጥር ማደግን የተመለከተው ይገኝበታል።

በ1995 ዓ.ም የወጣው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህገ መንግስት፤ የክልሉ ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ100 እንደማይበልጥ ይደነግጋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት የካቲት 11 ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው፤ የመቀመጫ ብዛቱን ከ99 ወደ 165 ከፍ አድርጓል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15236/

@EthiopiaInsiderNews


በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ተጥሎ የነበረው እገዳ ተነሳ

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን “ህግን ተላልፈው ተገኝተዋል” በሚል በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ ጥሎት የነበረውን የእግድ እርምጃ’፤ “ማስጠንቀቂያ” በመስጠት ከዛሬ ጀምሮ ማንሳቱን አስታወቀ። ባለስልጣኑ እገዳውን ያነሳው፤ ከታገዱት ድርጅቶች ጋር ባደረገው ውይይት “በተፈጠረ መግባባት” እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበውን ምክረ ሃሳብ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ አስታውቋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የዛሬውን ውሳኔ ያስተላለፈው “በታገዱት ሁሉም ድርጅቶች” ላይ መሆኑን ዛሬ ሰኞ የካቲት 24፤ 2017 ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል። ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱ ባለፈው መንፈቅ ዓመት ብቻ በሰባት ድርጅቶች ላይ የእግድ ውሳኔ ማስተላለፉን ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ በፓርላማ በተካሄደው የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ መግለጹ ይታወሳል።

በዚሁ ጊዜ ውስጥ ከታገዱት መካከል አራቱ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ናቸው። “ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጭ ተንቀሳቅሰዋል” በሚል ባለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽ የታገዱት እነዚህ ድርጅቶች፤ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ)፣ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)፣ የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD) እና የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች (LHR) ናቸው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ▶️ https://ethiopiainsider.com/2025/15215/

@EthiopiaInsiderNews


ከአዲግራት ከተማ አቅራቢያ በሬክተር ስኬል 5.2 የተለካ ርዕደ መሬት ተከሰተ

ዛሬ እሁድ ከአዲግራት ከተማ 46 ኪሎ ሜትር በስተምስራቅ ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ ላይ በሬክተር ስኬል 5.2 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት ገለጸ። ርዕደ መሬቱ የተከሰተው ከቀኑ 5 ሰዓት ከ14 ደቂቃ ላይ መሆኑንም መስሪያ ቤቱ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ በአፋር ክልል ባሉ አካባቢዎች ካለፈው መስከረም ወር ጀምሮ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ቢከሰትም፤ በትግራይ ክልል ከተሞች አቅራቢያ ርዕደ መሬት ሲመዘገብ ግን በዚህ ዓመት የመጀመሪያው ነው። የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር ቀጠና የተከሰተ መሆኑን የጠቆመው የአውሮፓ ሜዲትራንያን ሴይስሞሎጂ ማዕከል (EMSC)፤ መጠኑም በሬክተር ስኬል 5.3 የተለካ እንደሆነ አስታውቋል።

በኤርትራ ከአንድ ሳምንት በፊት የደረሰ ርዕደ መሬት በሬክተር ስኬል 4.6 ሆኖ ተመዝግቧል። የመሬት መንቀጥቀጡ የተከሰተው በቀይ ባህር ሰሜናዊ አቅጣጫ ከአስመራ 24 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ባለ አካባቢ ነበር። በሀገሪቱ ባለፈው ታህሳስ ወር አጋማሽም እንዲሁ ተመሳሳይ ርዕደ መሬት ተመዝግቧል።

በሐምሌ 2015 ዓ.ም. በኤርትራ ባህር ዳርቻ ዳህላክ ደሴት አካባቢ የተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ፤ በትግራይ ክልል የተለያዩ ከተሞች ተደጋጋሚ ንዝረቶች አስከትሎ እንደነበር ይታወሳል። ንዝረቱን በሽሬ፣ አዲግራት፣ አድዋ፣ አክሱም እና መቐለ ከተማ ያሉ ነዋሪዎች መስማታቸውን በወቅቱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews


ወንዞችን በቆሻሻ የሚበክሉ ግለሰቦችን እና ተቋማትን እስከ አንድ ሚሊዮን ብር የሚያስቀጣ ደንብ ተግባራዊ ሊደረግ ነው

በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ ወንዞችን፤ በባህሪያቸው “አደገኛነት” ባላቸው ደረቅም ይሁን ፈሳሽ ቆሻሻ የሚበክሉ ድርጅቶችን አንድ ሚሊዮን ብር ቅጣት የሚጥል ደንብ ተግባራዊ ሊደረግ ነው።

ከመኖሪያ ቤቶች የሽንት ቤት አሊያም ማንኛውንም ያልተጣራ ፍሳሽ ቆሻሻ ወደ ወንዝ መልቀቅ እስከ 300 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ደንቡ ይደነግጋል። የወንዞችን ብክለት ለመከላከል የሚያስችለውን ይህ ደንብ የጸደቀው፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ባለፈው ታህሳስ ወር ባደረገው ስብሰባ ላይ ነው።

በደንቡ ላይ የሰፈሩ ድንጋጌዎች ከታህሳስ 2፤ 2017 ጀምሮ ተፈጻሚ እንደሚሆኑ በሰነዱ ላይ ቢገልጽም፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን በዚህ መሰረት ገና መቅጣት አለመጀመሩን የመስሪያ ቤቱ ስራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከከተማይቱ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን እና የውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ጋር በመሆን፤ ደንቡን የተመለከተ ስልጠና እና የግንዛቤ ማስጨበጫ በትላንትናው እና በዛሬው ዕለት አካሄዷል።

ስልጠናው የተመረኮዘበት “የወንዞች ዳርቻ ልማት እና ብክለት መከላከል ደንብ”፤ በሰባት ክፍሎች እና በ21 አንቀጾች የተከፋፈለ ነው። በደንቡ መጨረሻ በአባሪነት የተካተተው ሰንጠረዥ፤ በወንዝ እና በወንዝ ዳርቻ ላይ ብክለት በሚፈጸሙ ድርጅቶች እና ግለሰቦች ላይ የሚጣሉ አስተዳደራዊ የገንዘብ ቅጣቶችን ዘርዝሯል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15201/

@EthiopiaInsiderNews


በኢትዮጵያ ከሚከሰተው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የ47 በመቶው መንስኤ “ዛፎች የሚፈጥሩት ንክኪ ነው” ተባለ 

በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚከሰት የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ 47 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው፤ ዛፎች እና ቅርንጫፎች በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ የሚፈጥሩት ንኪኪ መሆኑ ተገለጸ።

በመሰረተ ልማት ላይ የሚደርሱ ስርቆቶች እና ጉዳቶች የኃይል መቆራረጥ እንዲከሰት የሚያደርጉ ሌሎች ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውንም ተነግሯል።

ይህ የተገለጸው፤ የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ መስመሮችን የማስተዳደር እና የኤሌክትሪክ ኃይልን በጅምላ ገዝቶ ለደንበኞች የመሸጥ ኃላፊነት ያለፈበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት፤ ዛሬ ሐሙስ የካቲት 20፤ 2017 በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል አቅርቦት እና ጥራትን ለማሻሻል በአጭር ጊዜ ለመተግበር ካቀዳቸው ተግባራት መካከል፤ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ውስጥ የገቡ ዛፎች እና ቅርንጫፎችን መቁረጥ አንዱ እንደሆነ የተቋሙ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጌቱ ገረመው በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

በኤሌክትሪክ መስመሮች ላይ አደጋ የሚፈጥሩ ዛፎች እና ቅርንጫፎችን የመቁረጥ ተግባር ከሁለት ወር በፊት እንደተጀመረ የገለጹት አቶ ጌቱ፤ የስራው አፈጻጸም በአዲስ አበባ 50 በመቶ እንዲሁም በሀገር አቀፍ ደረጃ 30 በመቶ እንደደረሰ አስረድተዋል።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15194/

@EthiopiaInsiderNews


በመሬት መንቀጥቀጥ “ከፍተኛ ጉዳት” የደረሰበት የከሰም ስኳር ፋብሪካ፤ ሰራተኞቹን በመጪዎቹ ወራት ሊያሰናብት ነው 

ባለፉት ወራት በተደጋጋሚ በተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጦች “ከፍተኛ ጉዳት” የደረሰበት የከሰም ስኳር ፋብሪካ፤ ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞቹን እስከ መጪው ግንቦት ወር ባለው ጊዜ ውስጥ ለማሰናበት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሰጠ።

የስኳር ፋብሪካው የሰራተኞች ማህበር በበኩሉ ሰራተኞቹ ሳይሰናብቱ ወደ ሌሎች ፋብሪካዎች እንዲበተኑ ለማድረግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል።

በስሩ ከአራት ሺህ በላይ ሰራተኞችን የሚያስተዳድረው የከሰም ስኳር ፋብሪካ፤ የቅድመ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የሰራተኞቹን የስራ ውል ያቋረጠው ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ የካቲት 11 ዓ.ም ባወጣው ማስታወቂያ ነው።

በፋብሪካው የማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ የተለጠፈው እና “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው ይህ ማስታወቂያ፤ የስራ ውላቸው የተቋረጠ ከአንድ ሺህ በላይ ሰራተኞችን ስም ዝርዝር የያዘ ነው።

ይኸው ማስታወቂያ፤ ፋብሪካው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ከታህሳስ 20 ጀምሮ በተደጋጋሚ የተከሰተው ርዕደ መሬት ባስከተለበት “ከፍተኛ ጉዳት” መሆኑን ያስረዳል።

የስኳር ፋብሪካው በዚህ ምክንያት “ስራውን ሙሉ ለሙሉ ያቆመ በመሆኑ”፤ በማስታወቂያው ስማቸው የተዘረዘረ ሰራተኞቹ የስራ ውል ከየካቲት 10፤ 2017 ጀምሮ “በቅደመ ማስጠንቀቂያ” መቋረጡንም አትቷል።

ይሁንና በዚያው ዕለት ፋብሪካው ማስተካከያ በማድረግ በለጠፈው ማስታወቂያ፤ ሰራተኞቹ ከየካቲት 10 ቀን ጀምሮ መሰናበታቸውን በማስቀረት ከዚሁ ቀን ጀምሮ እንደ የአገልግሎት ቆይታቸው ቅድመ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን ገልጿል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15186/

@EthiopiaInsiderNews


በአማራ ክልል ታስረው የነበሩ ሁሉም ዳኞች መለቀቃቸውን የክልሉ የዳኞች ማህበር አስታወቀ 

በአማራ ክልል እስከ ትላንት ድረስ በእስር ላይ የነበሩ ዳኞች ሙሉ ለሙሉ መለቀቃቸውን የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር አስታወቀ። ካለፈው ሁለት ወር ወዲህ እስከ አርብ የካቲት 14፤ 2017 ድረስ ባሉት ጊዜያት ከእስር የተለቀቁት ዳኞች ብዛት 36 እንደሆነ የማህበሩ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ አሰፋ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በክልሉ ታስረው የነበሩ ሁሉም ዳኞች መፈታታቸው የተገለጸው፤ የአማራ ክልል ምክር ቤት የዳኞች ያለመከሰስ መብትን ያካተተ የህግ ማሻሻያ ካጸደቀ ከአስር ቀናት በኋላ ነው።

በአማራ በተለያየ እርከን በሚገኙ ፍርድ ቤቶች የሚሰሩ ዳኞች ለእስር ይዳረጉ የነበረው፤ በሚይዟቸው መዝገቦች ላይ በሚሰጧቸው ውሳኔዎች ምክንያት እንደሆነ አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል።

“አብዛኞቹ ከስራ ጋር የተገናኘ ነው። ምክንያቱ ‘ዋስትና ጋር ተያይዞ ለምን ፈቀዳችሁ? ለምን ትዕዛዝ ሰጣችሁ? ለምን እግድ ሰጣችሁ?’ [የሚል ነው]። ያው በፍርድ ቤት ዳኞች በህግ የተሰጣቸውን ስልጣን መሰረት አድርገው ሲሰሩ፤ ከአስፈጻሚው ጋር የሚገናኙ አለመግባባቶች ጋር መነሻ በማድረግ የታሰሩ ናቸው” ሲሉ የአማራ ክልል ዳኞች ማህበር ምክትል ፕሬዝዳንት የእስሮቹን መንስኤ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15176/

@EthiopiaInsiderNews


በኢትዮጵያ በሬክተር ስኬል 5.0 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ዛሬ እሁድ ለሊት 8 ሰዓት ከ44 ደቂቃ ላይ መከሰቱን የአውሮፓ ሜዲትራንያን ሴይስሞሎጂ ማዕከል (EMSC) አስታወቀ። ዘለግ ላሉ ሰከንዶች የቆየው የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከለው ንዝረት መዲናዋ አዲስ አበባ ድረስ ተሰምቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews


ቪዲዮ፦ የስራ ዘመኑ ለተጨማሪ አንድ ዓመት በፓርላማ የተራዘመለት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ ወቅታዊ የስራ እንቅስቃሴዎቹን በተመለከተ በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል። በጋዜጣዊ መግለጫው ለተገኙ የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች መካከል፤ “በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መሳሪያ አንግበው ከሚፋለሙ ታጣቂዎች ጋር ንግግር ለማድረግ ሞክራችኋል?” የሚለው ይገኝበታል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ የኮሚሽኑ ዋና አላማ “ሁሉም በምክክር ሂደቱ ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ ነው” ብለዋል። ዋና ኮሚሽነሩ በዚሁ ምላሻቸው ከአንድ የታጣቂ ቡድን አመራር ጋር መነጋገራቸውን፤ ሆኖም ግን “ፋኖ መሆናቸውን እንደማያውቁ” ተናግረዋል።

“አንድ ታጣቂ ቡድን ራሳቸው ደውለውልኝ፤ አነጋግረውኝ ‘የምክክር ኮሚሽኑን ስራ ተገንዝበናል። ገለልተኛ መሆኑን ተገንዝበናል። በዚህ መሰረት ቀጥታ አጀንዳችንን ለእናንተ አቅርበን፤ ወደ ዱር የገባንበትን አጀንዳ ለእናንተ አምጥተን፤ ወደ ውይይት የሚቀርብ ከሆነ መሳሪያችንን ለማስቀመጥ ዝግጁ ነን’ የሚል ጥያቄ በቀጥታ ለእኔ ቀርቦልኛል” ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን ለጋዜጠኞች አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ከሚያደርገው የምክክር ሂደት ጋር በተያያዘም፤ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ጥያቄ ቀርቧል። የምክክር ኮሚሽኑ በአማራ ክልል በሚያደርገው እንቅስቃሴ “በህዝቡ ዘንድ ያለው አመኔታ እና ተቀባይነትን ምን ያህል ነው?” ለሚለው ጥያቄ፤ ከአስራ አንዱ የተቋሙ ኮሚሽነሮች አንዱ የሆኑት አቶ መላኩ ወልደማርያም ምላሽ ሰጥተዋል።

🔴 በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች የተሰጠውን ሙሉ ምላሽ ይህን ሊንክ ተጭነው ይመልከቱ ▶️ https://youtu.be/C5Q9ITR45qk

@EthiopiaInsiderNews


በአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተ የእሳት አደጋ፤ ከሁለት ሳምንት በኋላም “መቆጣጠር አልተቻለም” ተባለ

በአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ከሁለት ሳምንት በፊት የተቀሰቀሰ የእሳት አደጋ፤ እስከዛሬ ሐሙስ የካቲት 13፤ 2017 ድረስ በቁጥጥር ስር አለመዋሉን የአርሲ ዞን እና የፓርኩ ጽህፈት ቤት ኃላፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ለእሳት ቃጠሎው መከሰት መንስኤ ናቸው በሚል የተጠረጠሩ 30 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም የአርሲ ዞን አስታውቋል። 

በኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ ስድስት ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ አንዱ የሆነው የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚገኙት የምኒልክ ድኩላ፣ የደጋ አጋዘን፣ ቀይ ቀበሮ እንዲሁም የሌሎች እንስሳት መኖሪያ ነው። በ2003 ዓ.ም በብሔራዊ ደረጃ የተመዘገበው ፓርኩ፤ 84,340 ሄክታር የሚሸፍን ቦታን የሚያካልል ነው።

በፓርኩ ይዞታ ውስጥ በሚገኝ ኢቾ በተባለ ወረዳ ከሳምንት በፊት የተከሰተው የእሳት አደጋ፤ በአሁኑ ወቅት በ11 ወረዳዎች ላይ መስፋፋቱን የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መሀመድ ቲፎ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በሰደድ እሳቱ “በከፍተኛ ሁኔታ” ጉዳት የደረሰበት ጭላሎ ጋለማ የተሰኘው የፓርኩ “ብሎክ” እንደሆነም ኃላፊው አስረድተዋል። 

የአርሲ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጭላሎ ጋለማ፣ ካካ፣ ሆንቆሎ እና ዴራ ዲልፈከር በተባሉ አራት “ብሎኮች” የተከፋፈለ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ሰፊውን ቦታ የሚይዘው ጭላሎ ጋለማ 70,486 ሄክታር ስፋት አለው።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15166/

@EthiopiaInsiderNews


ለአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት የሚውለው ገንዘብ ምንጭ፤ የከተማይቱ “ግብር ከፋዮች” መሆናቸውን ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ 

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በአንድ ጊዜ በርካታ ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የሚያወጣው ገንዘብ ምንጭ፤ በከተማይቱ ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ አነገጋረ። የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ “የበጀታችን ምንጩ ግብር ነው። የከተማይቱ ግብር ከፋዮች ናቸው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

የከተማይቱ ምክር ቤት አባላት ካለፈው ዓመት ጀምሮ በአዲስ አበባ እየተተገበረ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት የተመለከቱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችን የሰነዘሩት፤ ዛሬ ረቡዕ የካቲት 12፤ 2017 በተካሄደ የምክር ቤቱ መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው።

አቶ ጋትዌች ዎርዲየው የተባሉ የከተማይቱ ምክር ቤት አባል “የኮሪደር ልማት በጀት ምንጩ ከየት ነው?” ሲሉ ለምክር ቤቱ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቀዋል። ይህ የእርሳቸው ጥያቄ፤ በሌላኛው የምክር ቤት አባል አቶ ፍቃዱ ታምራት በተሰጠ አስተያየት ላይም ተንጸባርቋል።

የኮሪደር ልማት ስራው “ከስፋቱ አንጻር ሲታይ፣ ምን ያህል በጀት የወሰደ እንደሆነ ሲታይ፣ ምን ያህል ለውጥ ከተማዋ ላይ እያመጣ እንደሆነ ሲታይ፣ ብቻውን በቂ ነበር” ያሉት አቶ ፍቃዱ፤ ይህንኑ አስመልክቶ ብዙ ሰዎች “በግርምት” የሚጠይቁት ጥያቄ “የከተማ አስተዳደሩ ይሄን ያህል ገንዘብ ከየት ሊያመጣ ቻለ?” የሚል እንደሆነ አመልክተዋል። 

ዶ/ር ወርቅነሽ ምትኩ የተባሉ የምክር ቤት አባል፤ “አንድ ከተማ በነበረው ሁኔታ፣ ከነበረው ገቢ፣ ይሄን ሁሉ ስኬት ማሳለጥ የሚችል ከሆነ፤ የት ነበርን? ይህ ገንዘብ ገንዘቡ ፈልቆ ነበር?” ሲሉ በገረሜታ ጠይቀዋል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15161/

@EthiopiaInsiderNews


የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ100 በላይ ሰራተኞቹ በአንድ ጊዜ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው ደመወዝ ይከፈላቸው እንደነበር ደርሼባቸዋለሁ አለ   
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰራተኞች “በሁለት እና በሶስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው” ደመወዝ ሲከፈላቸው እንደነበር የከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናገሩ። የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ሰራተኞች “ተጠያቂ ማድረጉንም” ከንቲባዋ ገልጸዋል።

አዳነች ይህንን የገለጹት፤ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ዛሬ ረቡዕ የካቲት 12፤ 2017 እያካሄደ ባለው መደበኛ ጉባኤ ላይ ባቀረቡት የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ነው።

ከንቲባዋ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ የተቀናጀ የሲቪል ሰርቪስ መረጃ አያያዝ ስርዓት ተግባራዊ በማድረጉ፤ በስሩ ምን ያህል ሰራተኞች እንዳሉት ለማወቅ እንደቻለ ገልጸዋል።

የከተማ አስተዳደሩ 168 ሺህ ያህል ሰራተኞቹን ፋይል “ስካን አድርጎ” ወደ ስርዓቱ እንዲገባ ካደረገ በኋላ በተደረገው ማጣራት፤ ከ100 በላይ የሚሆኑ ሰራተኞች “ያለአግባብ በሁለት እና በሶስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥረው” ደመወዝ እንደሚከፈላቸው እንደተደረሰበት አብራርተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ እነዚህን ሰራተኞች “ተጠያቂ” ማድረጉን አዳነች በሪፖርታቸው ቢጠቅሱም፤ የተወሰደባቸው እርምጃ ምን እንደሆነ ግን በዝርዝር ሳይገልጹ ቀርተዋል።

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15155/

@EthiopiaInsiderNews


የኢትዮጵያ እና ሶማሊያ “ቴክኒካዊ ድርድር” በመጪው መጋቢት ወር ይቀጥላል ተባለ

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ከፍተኛ ባለስልጣናት የተሳተፉበት የመጀመሪያው ዙር ቴክኒካዊ ድርድር ተጠናቀቀ። በቱርክ አንካራ ከተማ በተካሄደው ድርድር፤ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ እና የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አሊ ሞሐመድ ዑመር ተገኝተዋል።

በቱርክ በኩል በድርድሩ የተገኙት፤ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች በታህሳስ ወር መጀመሪያ ፊት ለፊት ከመገናኘታቸው በፊት በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ ተመላልሰው ውይይቱን ያመቻቹት የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሐካን ፊዳን ናቸው።

በዛሬው ድርድር ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ የሁለቱን ሀገራት ልዑካን ቡድን በተናጠል እና በጋራ ማነጋገራቸውን መስሪያ ቤታቸው አስታውቋል።

ሐካን ፊደን በተናጠል እና በጋራ በተደረጉት ውይይቶች፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ ልዩነት በበረታበት ዓለም ውስጥ ቀጠናዊ ትብብር ወሳኝ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በአጽንኦት መናገራቸውን የቱርክ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አመልክቷል።

ፊዳን በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተጀመረው ድርድር “የአፍሪካን ቀንድ መጻኢ ጊዜ ታሪካዊ ዕድል ይወክላል” በማለት ፋይዳውን ገልጸዋል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15146/

@EthiopiaInsiderNews


የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “ደካማ የሆነ አፈጻጸም አሳይቷል ብለን እናስባለን” - ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ

ቪዲዮ፦ በዛሬው ዕለት በተካሄደው የፓርላማ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የስራ ሪፖርት ያቀረቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ኮሚሽኑ በአዋጅ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ የምክክር፣ የአጀንዳ መለየት እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ስራዎችን ማከናወኑን ተናግረዋል። እነዚህ ሂደቶች በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ሙሉ ለሙሉ መጠናቀቃቸውንም ገልጸዋል።

እርሳቸው ይህን ቢሉም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ግን ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ “ደካማ የሆነ አፈጻጸም አሳይቷል ብለን እናስባለን” ሲሉ ተደምጠዋል። እንደ ዶ/ር ደሳለኝ ሁሉ፤ ሁለት የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ ተወካዮችም በኮሚሽኑ የስራ አፈጻጸም ያላቸውን አስተያየት እና ጥያቄ ሰንዝረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

🔴 ሶስቱ የፓርላማ አባላት በዛሬው ስብሰባ ላይ የተናገሩትን ለመመልከት ይህን ሊንክ ይጫኑ ➡️ https://youtu.be/xkJymS2kYOY

@EthiopiaInsiderNews


የቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ በፌደራል ፍርድ ቤት ከቀረቡባቸው ክሶች በነጻ እንዲሰናበቱ ተፈረደላቸው

🔴 አቶ ጸጋዬ ቱኬ በሌላ ፍርድ ቤት ክሶች ያለባቸው በመሆኑ በእስር ላይ ይቆያሉ ተብሏል

ቀድሞው የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ አቶ ጸጋዬ ቱኬ ከቀረቡባቸው ሁለት ክሶች በነጻ እንዲሰናበቱ በዛሬው ዕለት የፍርድ ውሳኔ እንደተሰጣቸው ከተከላካይ ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ ገብረመድህን ተክላይ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ።

ከቀድሞው ከንቲባ ጋር በአንድ መዝገብ የተከሰሱት የሲዳማ ክልል የቀድሞ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ አበራ አሬራ እና የአቶ ጸጋዬ የእህት ልጅ የሆኑት አቶ አብርሃም አመሎም በተመሳሳይ በነጻ መሰናበታቸውን ጠበቃው ገልጸዋል።

በሶስቱ ተከሳሾች ላይ የፍርድ ውሳኔውን የሰጠው፤ ጉዳዩን ሲመረምር የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል ነው። ፍርድ ቤቱ ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 11፤ 2017 በዋለው ችሎት፤ “ሶስቱም ተከሳሾች የቀረበባቸውን ሁለቱንም የወንጀል ክሶች ያልፈጸሙና በሚገባ የተከላከሉ መሆናቸው በነጻ ተሰናብተዋል” ሲል ውሳኔ ማስተላለፉን ጠበቃ ገብረመድህን ገልጸዋል።

የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ በአቶ ጸጋዬ እና በሁለቱ ተከሳሾች ላይ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር ክስ የመሰረተው፤ “የማይገባ ጥቅም በመቀበል የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል” እንዲሁም “በወንጀል ድርጊት የተገኘን ገንዘብ ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስለው አቅርበዋል” በሚል ነበር።

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሀዋሳ ማዕከል፤ ሶስቱም ተከሳሾች የቀረቡባቸውን ክሶች እንዲከላከሉ ባለፈው ጥቅምት ወር አጋማሽ ገደማ ብይን ሰጥቷል።

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15139/

@EthiopiaInsiderNews


የተወካዮች ምክር ቤት የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ለአንድ ዓመት አራዘመ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ማክሰኞ የካቲት 11፤ 2017 ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ለአንድ አመት አራዘመ።

የኮሚሽኑን የስራ ዘመን ለማራዘም የቀረበው የውሳኔ ሀሳብ፤ በሶስት የፓርላማ አባላት ተቃውሞ በአብላጫ ጽምጽ ጸድቋል። 

መሰረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች “ወሳኝ ምክንያቶችን የመለየት” እና ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች በመለየት “ምክክር እንዲደረግባቸው የማመቻቸት” ዓላማ ይዞ የተቋቋመው ኮሚሽኑ፤ በአዋጅ የተቀመጠለት የስራ ዘመን ሶስት ዓመት ነው።

የተወካዮች ምክር ቤት በእረፍት ላይ ያሉትን የፓርላማ አባላት አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው፤ የኮሚሽኑ የስራ ዘመን ከማለቁ ሁለት ቀን አስቀድሞ ነው።

ፓርላማው ኮሚሽኑ ለተጨማሪ አንድ ዓመት በስራ ላይ እንዲቆይ ውሳኔ ከማሳለፉ አስቀድሞ፤ የተቋሙን የሶስት ዓመታት የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አዳምጧል።

ሪፖርቱን ለፓርላማ አባላት በንባብ ያቀረቡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ፤ ኮሚሽኑ በዚህ ጊዜ ውስጥ የምክክር፣ የአጀንዳ መለየት እና ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተወካዮችን የማስመረጥ ስራዎችን በ10 ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ማጠናቀቁን አስታውቀዋል። 

🔴 ለዝርዝሩ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15130/

@EthiopiaInsiderNews


የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ “ቴክኒካዊ ድርድር” ዛሬ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አመቻችነት የሚያካሄዱት “ቴክኒካዊ ድርድር” ዛሬ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።
በሶማሊያ
የማስታወቂያ፣ ባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትር ዳውድ አዌይስ የተመራ የልዑካን ቡድን ዛሬ ሰኞ ወደ አንካራ አቅንቷል። 

ሚኒስትሩ በኤክስ ይፋዊ ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ የሁለቱን ሀገራት የመጀመሪያ ዙር ቴክኒካዊ ውይይት ለማስጀመር በአንካራ የሶማሊያ ልዑካንን መቀላቀላቸውን አስታውቀዋል።

ዳውድ አዌይስ በዚሁ መልዕክታቸው፤ ውይይቱ “የአንካራ ቃል ኪዳንን ተግባራዊ ለማድረግ መንገዶች ለማፈላለግ” ያለመ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ “ልዩነቶቻቸውን እና አወዛጋቢ ጉዳዮችን ወደ ኋላ ለመተው” እና “ትብብር ለማበጀት” በአንካራ ስምምነት የተፈራረሙት ባለፈው ታህሳስ ወር መጀመሪያ ላይ ነበር።

ሁለቱ ሀገራት በቱርክ አመቻችነት በተፈራረሙትን በዚሁ ስምምነታቸው፤ “አንዳቸው ለሌላው ሉዓላዊነት፣ አንድነት፣ ነጻነት እና የግዛት አንድነት ያላቸውን ክብር እና ቁርጠኝነት” መግለጻቸው ይታወሳል።   

🔴 ሙሉ ዘገባውን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15123/

@EthiopiaInsiderNews


በጋምቤላ ክልል በተከሰተ የአተት ወረርሽኝ፤ ዘጠኝ ሰዎች ሲሞቱ 136 ሰዎች በበሽታው ተይዘዋል

በጋምቤላ ክልል ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ በተከሰተ የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት (አተት) ወረርሽኝ የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ በአራት ወረዳዎች ላይ የተከሰተው ወረርሽኝ፤ መነሻው በአጎራባች ከሚገኙት የደቡብ ሱዳን አካባቢዎች መሆኑንም የጤና ቢሮው ገልጿል።

የክልሉ ጤና ቢሮ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ ወንድማገኝ በላይነህ፤ ወረርሽኙ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው ከአንድ ሳምንት ገደማ በፊት በአኮቦ ወረዳ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በአተት ወረሽኝ ለመጀመሪያ ጊዜ መያዛቸው በምርመራ የተረጋገጠው በዘጠኝ ሰዎች ላይ ቢሆንም፤ ከአንድ ሳምንት በኋላ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 136 መድረሱን ኃላፊው አስረድተዋል። 

በወረርሽኙ የተጠቁ ሰዎች በአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት የሚያጋጥማቸው በመሆኑ በአተት መጠቃታቸው ይገልጽ እንጂ፤ የበሽታው ምልክቶች የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) ትንታኔ በኮሌራ መያዛቸውን የሚያመለክት መሆኑን አቶ ወንድማገኝ አብራርተዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ወረርሽኙ ኮሌራ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ናሙና ወደ አዲስ አበባ አበባ መላኩንም አክለዋል።   
“እኛ ከዚህ ወደ ኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ናሙና ልከናል። ትክክለኛ ኮሌራ ነው ብሎ ማረጋገጫ አላከልንም” ሲሉ አቶ ወንድማገኝ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ኮሌራ አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት በማስከትል፣ በሰውነት ውስጥ የሚገኝን ፈሳሽ አሟጥጦ በማስወጣት፣  አቅምን በማዳክም፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለሞት የሚዳርግ በሽታ ነው።  

🔴 ለዝርዘሩ ▶️ https://ethiopiainsider.com/2025/15099/

@EthiopiaInsiderNews


ፓርላማው በመጪው ማክሰኞ በሚያካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽንን የስራ ዘመን ያራዝማል ተብሎ ይጠበቃል

የሶስት አመት የስራ ዘመኑን እያገባደደ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን፤ አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን በመጪው ማክሰኞ በሚካሄድ አስቸኳይ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ሊያቀርብ ነው።

በዚሁ ስብሰባ ላይ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ “የስራ ዘመን ይራዘማል” ተብሎ እንደሚጠበቅ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

በታህሳስ 2014 ዓ.ም የጸደቀው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ፤ የኮሚሽኑ የስራ ዘመን ሶስት ዓመት እንደሆነ ይደነግጋል።

የኮሚሽኑ የስራ ዘመን የሚቆጠረው፤ በአዋጁ መሰረት የሚመረጡ ኮሚሽነሮች በፓርላማ ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ በድንጋጌው ላይ ሰፍሯል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በዕጩነት የቀረቡ 11 ኮሚሽነሮችን ሹመት ያጸደቀው የካቲት 14፤ 2014 ዓ.ም. ነው።

ፓርላማው ለአንድ ወር እረፍት የተበተኑ አባላቱን ለመጪው ማክሰኞ አስቸኳይ ስብሰባ የጠራው፤ የኮሚሽኑ የስራ ዘመን ድፍን ሶስት ዓመት ከሚሞላበት ዕለት ሁለት ቀናት አስቀድሞ ነው።

የተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ረቡዕ ለአባላቱ ባሰራጨው የስብሰባ ጥሪ፤ ለኮሚሽኑ ጥያቄ ማቅረብ የሚፈልጉ አባላት እስከ ዛሬ ቅዳሜ የካቲት 8፤ 2017 ድረስ እንዲመዘገቡ አሳስቦ ነበር።

🔴 ዝርዝሩን ለማንበብ ➡️ https://ethiopiainsider.com/2025/15089/

@EthiopiaInsiderNews


ከመተሐራ ከተማ አቅራቢያ በሬክተር ስኬል 6.0 የተለካ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከሰተ

ከመተሐራ ከተማ ስድስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ አካባቢ ላይ በሬክተር ስኬል 6.0 የደረሰ የመሬት መንቀጥቀጥ መከሰቱን የአሜሪካ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ መስሪያ ቤት አስታወቀ። ከምሽቱ 5:28 ደቂቃ ላይ የደረሰው ርዕደ መሬት፤ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ ከተመዘገቡት ሁሉ በመጠን ከፍተኛው ነው።

የዛሬው የመሬት መንቀጥቀጥ ያስከተለው ንዝረት “በጣም ጠንካራ” ሆኖ የተሰማው በመተሐራ ከተማ ይሁን እንጂ መዲናይቱን አዲስ አበባን ጨምሮ በርካታ ከተሞችን ማዳረሱን የአሜሪካው የምርምር ተቋም ገልጿል። የርዕደ መሬቱ ንዝረት በአዋሽ ከተማ “መጠነኛ” እንደነበር ያመለከተው ተቋም፤ በአዳማ፣ ሞጆ፣ ቢሾፍቱ እና ደብረ ብርሃን ከተሞችም በተመሳሳይ መጠን መከሰቱን ጠቁሟል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

@EthiopiaInsiderNews

20 ta oxirgi post ko‘rsatilgan.