ኬንያ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላይ ያነጣጠረ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን አስታወቀች!ኬንያ ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት የድንበር ግዛቶቿ ላይ ባሉ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላይ ያነጣጠረ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሯን አስታወቀች።የኬንያ መንግሥት የጦሩ አባላት ተደብቀውባቸዋል ባላቸው የማርሳቤት እና ኢሲዮሎ ግዛቶች ላይ "ወንጀለኞችን የማስወገድ" የተሰኘ ከፍተኛ የጸጥታ ዘመቻ ባለፈው ወር ጥር፣ 25/ 2017 ዓ.ም መጀመሩን ገልጿል።
እነዚህ ግዛቶችን "ድንበር ዘለል የወንጀል ድርጊቶችን ለማሳለጥ የሚጠቀምባቸው ናቸው" ሲል የኬንያ መንግሥት ብሔራዊ የፖሊስ አገልግሎት ሰኞ ጥር፣ 26/ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ቡድኑን ወንጅሎታል።የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ ጥሰቶች የሚወነጅለው "ሸኔ" እያለ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በኬንያ ግዛቶች ውስጥም ህገወጥ የማዕድን ማውጣትን ጨምሮ ሌሎች ጥሰቶች እየፈጸመ ነው ኬንያ ወንጅላለች።
የኬንያ ብሔራዊ ፖሊስ ቡድኑ "በተለያዩ ህገወጥ የጦር መሳሪያ፣ አደንዛዥ ዕጾች ዝውውር፣ ህገወጥ የማዕድን ማውጣት ህገወጥ የሰዎች ዝውውር ንግድ ተሰማርቶ ይገኛል" ብሎታል በመግለጫው።የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት "ለገንዘብ ሲል እገታዎችን በመፈጸም እንዲሁም ድንበር ዘለል ወረራዎችን በማካሄድ እና በጎሳዎች መካከል ግጭቶች እንዲቀሰቀሱ በማድረግ ለኬንያ የብሔራዊ ደህንነት ከፍተኛ ስጋት" ሆኗል ሲል መግለጫው አስፍሯል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በበኩሉ ቡድኑን መወንጀል አዲስ ነገር እንዳልሆነ ጠቅሶ በዘረፋዎችም ሆነ በህገወጥ ተግባራት እንዳልተሳተፈ እና "ለፍትህ" የሚታገል ድርጅት መሆኑን ለቢቢሲ ገልጿል።"እንዲህ አይነት ጥሰቶችን የሚፈጽሙ አካላትን ከኬንያ መንግሥት ጋር በመተባባር እንደሚዋጉ" የጦሩ ዋና አዛዥ አማካሪ ጂሬኛ ጉዴታ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኬንያ በታጣቂዎቹ ላይ የጀመረችው ዘመቻ ባለፈው ወር የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ወደ ኬንያ ተጉዘው ከአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው።በውይይቱ ላይ የኬንያው የብሔራዊ መረጃ አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል ኑረዲን ሐጂ ተገኝተው ነበር።
ታጣቂው ቡድን "በኬንያ ቦረና እና በኢትዮጵያ ኦሮሞ መካከል ያለውን የባህል ትስስር እንዲሁም ቅርብ ዝምድና በመጠቀም በማርሳቤት እና ኢሶዮሎ ግዛቶች ውስጥ ባሉ ህዝቦች መካከል ሰርጎ በመግባት በድንበር አካባቢ በሚኖሩ ማህበረሰቦች ላይ ጥሰቶችን" እየፈጸመ ይገኛል ብሎታል የኬንያ ፖሊስ መግለጫ።
መግለጫው አክሎም "ቡድኑ በሴቶች እና በታዳጊዎች ላይ ወሲባዊ ጥቃቶችን ጨምሮ ማስፈራራት፣ በኃይል ንብረትን መውሰድ በአካባቢው በመፈጸሙ ማህበረሰቡን ለሰቆቃ ዳርጎታል" ብሏል።
ህይወትን፣ ንብረትን እንዲሁም ሰላምን ለማስጠበቅ በግዛቲቱ ተደብቀው የሚገኙ "የኦሮሞ ነጻነት ወንጀለኞችን ለማስወገድ" የኬንያ ብሔራዊ የፖሊስ አገልግሎት የወታደራዊ የመጀመሪያ ምዕራፍ ዘመቻ በይፋ መጀመሩን የአገሪቱ ፖሊስ ምክትል ዋና አዛዥ ጊልበርት ማንጊሲ እንዲሁም የወንጀል ምርመራ አገልግሎት ዳይሬክተር መሀመድ አሚን በትናንትናው ዕለት ገልጸዋል።
https://t.me/voa_amharic1https://t.me/voa_amharic1