በመካ ከተማ አንድ ሰው ግራ ቀኙን እየቃኘ በመንገድ ሲያልፍ አንዲት አሮጊት እርጅና ባጎበጠው እድሜ ባሰለላቸው እጆቻቸው እየተንቀጠቀጠቀጡ ምግብ የሚያበስሉበትን እንጨት ተሸክመው ወደቤታቸው ሊሄድ ሲያጣጥሩ ይመለከታል። በአሮጊቷ ተግባር ልቡ የተነካው ይህ ሰውም በቀስታ ወደሴትየዋ ተጠግቶ « ቤትዎን ያሳዩኝ እኔ ተሸክሜ አደርስልዎታለሁ» አላቸው።
የሴትየዋ ቤት እጅግ እሩቅ ከመሆኑ ባሻገር ጸሀዩ ሲጠብሰው የዋለው አሸዋ ልክ በጋለ ፍም ላይ የመራመድ ያክል እግርን ክፉኛ ይለበልብ ነበር! ጸሀዩዋም መካ ብቻ ጓዟን ጠቅላ የሰፈረች ይመስል እንደእሳት ትፋጃለች። በነፋሱ እየተንሳፈፈ የሚመጣው የአሸዋ ብናኝም ፊትን በሀይል ይጋረፋል! እንግዲህ ይህን ፈተና ችሎ ነው ሰውየው የአሮጊቷን የደረቁ እንጨቶች ለመሸከም የወሰነው
በሰውዬው ድርጊት እየተገረሙና እየተደነቁ ቤታቸው የደረሱት ምስኪኗ አሮጊትም መልካሙን ሰውዬ ትኩር ብለው እየተመለከቱ እንዲህ አሉት ..
«ልጄ ሆይ እንዲያው ባሮጊት አንደበቴ እመርቅሀለሁ እንጂ ላደረግህልኝ ነገር መካሻ ይሆን ዘንድ የምሰጥህ አንዳች የሌለኝ ምስኪን ደሀ ነኝ ልጄ እባክህ ከሰማኸኝ አንድ ምክር ልለግስህ። ወደህዝቦችህ ወደመካ ስትመለስ እዚያ አንድ ነብይ ነኝ የሚል ሙሀመድ የሚሉት ደጋሚ ሰው አለ። በፍጹም እሱን እንዳትከተል እንዳታምነውም!» አሉት።
ሰውዬውም ረጋ ብሎ «ለምን?» ብሎ ጠየቀ!
አሮጊቷም «ልጄ እርሱ መጥፎ ስነምባር ነው ያለው ሲሉ ሰምቻለሁ» ብለው መለሱ።ሰውዬው በሴትየዋ ንግግር ተገርሞ «እኔስ ሙሀመድ ብሆን?» አላቸው። ሴትየዋም የሰሙት ነገር በጣም አስገርማቸው ለካስ ይህ ደግ ሰው ራሳቸው ነብዩ ሙሀመድ (ሰ.አ.ወ) ነበሩ። አስተውሉ ... ነብዩ ለአሮጊቷ ቸርነትን ሲያደርጉ ሀይማኖታቸውን ፈፅሞ አልጠየቁም። ፍቅር የሀይማኖትን ድንበር፣ የዘርና የጎሳን አጥር እንደሚያልፍ ያውቁ ነበርና። ስብከት ያልሰበረውን ልብና ትምህርት ያላንበረከከውን ማንነት ፍቅር ብቻ ትህትናና በጎ ምግባር ብቻ ያንበረክከዋል!
ያማረ ጁምኣ!💚
@ourworl_d