" ፍትህ የለም እንጂ ፍትህ ካለ እኔ ነጻ ሰው ነኝ። ፍርድ ቤት በነጻ ለቆ ለደረሰብኝ በደል ሁሉ ካሳ ሊያሰጠኝ በቻለ ነበር " - አቶ ዮሐንስ ቧያለው
እነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው እና አቶ ክርስቲያን ታደለ ዛሬ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህገ መንግስትና የሽብር ወንጀል ችሎት በረበባቸው ክስ የእምነት ክህደት ቃል መስጠታቸውን ቲክቫህ ኢትዮጵያ ከደረሰው የሰነድ ማስረጃ ለማወቅ ችሏል።
አቶ ዮሐንስ ቧያለው በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል፣ " የቀረበብኝን ውንጀላና አሉባልታ አልቀበልም። ወንጀልም አልፈጸምኩም " ማለታቸውን ሰነዱ ያወሳል።
አክለው፣ " ፍትህ የለም እንጂ ፍትህ ካለ እኔ ነጻ ሰው ነኝ። ፍርድ ቤት በነጻ ለቆ ለደረሰብኝ በደል ሁሉ ካሳ ሊያሰጠኝ በቻለ ነበር። ግን እንዴት ሆኖ/ ራሱ ነጻ ያልሆነ ማንን ሊያደርግ ይችላል " ነው ያሉት።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ በ18/07/2016 ዓ/ም በስማቸው በሚጠራው መዝገብ ላይ ያቀረበውን ክስ " ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት የለውም " ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
የተቃውሟቸውን ምክንያት የገለጹበት ሰነድ፣ " ሁሉም የክስ ጭብጦች በፈጠራ ተሞሉ ናቸው " ይላል።
የክስ ጭብጡ፣ " ‘የሽብር ቡድን አመራር በመሆን፣ አባል በመሆን፣ ራሱን በመሰየም፣ በማደረጃት፣ የሰራተኛ ሰነድ በማዘጋጀትና ጽንፈኛ ፋኖን በመምራት የሽብር ወንጀል ፈፅሟል’ ይላል " ሲሉ አስረድተዋል በሰነዳቸው።
ዮሐንስ በሰጡት የእምነት ክህደት ቃል፣ " የተጠቀሰው ሀሳብ በአንድ በኩል መረጃ አልባና ከእውነት የራቀ ሲሆን፣ በሌላ መልኩ ደግሞ የአንድን የህዝብ ባህላዊ ተቋም ለመክሰስ የሞከረ ሆኖ አግኝቼዋለሁ " ሲሉ ወንጅለዋል።
" መረጃ አልባነቱን " ጭምር በገለጹበት ሰነድ አቶ ዮሐንስ ምን አሉ ?
“ በኢፌድሪ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሰየመ አሸባሪ ቡድን ማን እንደሆነ፣ በዚህ ቡድን ላይ የእኔ ኃላፊነትና የፈጸምኩት ወንጀል ምን እንደሆነ ከመግለጽ ይልቅ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ራሱ በጭንቅላቱ የፈጠረው ‘አሸባሪና ጽንፈኛ ቡድን አመራርና አባል ነው’ የሚል የፈጠራ ድርሰት መቅረቡ ነው።
በአንጻሩ አንድን የህዝብ ባህላዊ ተቋም ፍትህ ሚኒስቴር (ጠቅላይ አቃቢ ህግ) በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን በመተላለፍና በደመኝነት መንፈስ ‘አሸባሪ’ ብሎ መሰየሙ ነው።
ፋኖ የአማራ ህዝብ ተቋም ሆኖ እያለ የፋኖ አመራርና አባል የሆኑ ሰዎች አሸባሪ ናቸው ብሎ መክሰስ ህዝቡን እንደ ህዝብ ከመክሰሱም በላይ ለአማራ ህዝብ ተቋሙ ያሳየውን ንቀት የሚያረጋግጥ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
የአማራ ጠላት የሆነው ዘረኛው ስርዓትም ይሁን በመሳሪያነት እያገለገለ ያለው ጠቅላይ አቅቢ ህግ ሊያውቁት የሚገባ ጉዳይ ቢኖር ሁሉም አማራ ፋኖ መሆኑን ነው። የእኔ ‘ፋኖ’ መሆንም በቀጥታ ከአማራነቴ ጋር የተያያዘ ነው።
ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው መላው የአማራ ህዝብ እስካሁን ድረስ ምናአልባትም በጉዲፈቻና በሞጋሳ ከተሸጡት ጥቂት የአብይ አህመድ ቡድን የሆኑ የካቢኔ አባላት ውጪ ሁሉም አማራ ፋኖ እንደሆነ ሁሉ እኔም በፋኖነቴ አላፍርም። እኮራለሁ እንጂ !
ቄሮነትና አባገዳነት ወንጀል እንዳልሆነው ሁሉ ፋኖነትን መንካት በአንድ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ከመሆኑም በላይ ምንጊዜም ቢሆን በማንነቴ ላይ የሚመጣን ጥቃት እንደ ባንዳዎችና በጉዲፈቻ እንደተሸጡ የስራዓቱ (የብልጽግና ቡድን) አባላት ዝም ብዩ ልቀበለው እንደማልችል በድጋሚ ላረጋግጥ እወዳለሁ።
ፋኖነት ወንጀል ሳይሆይን በክብር የሚሰውለት አማራዊነት ነው "
ብለዋል።አቶ ዮሐንስ ቧያለው ሙሉ የእምነት ክህደት ቃል ገለጻ የያዘው ሰነድ ከላይ የተያያዘ ሲሆን የአቶ ክርስቲያን ታደለ የእምነት ክህደት ቃል ደግሞ በቀጣይ ይቀርባል።
@tikvahethiopia